መንግሥት ገለልተኛ ተቋማትን በገዢው ፓርቲ አባሎች ጠፍሮ በመያዝ ሚናቸውን እንዳይወጡ እና በሕግ አግባብ እንዳይሠሩ ማድረጉን ቀጥሏል!

May be a doodle of textመንግሥት ገለልተኛ ተቋማትን በገዢው ፓርቲ አባሎች ጠፍሮ በመያዝ ሚናቸውን እንዳይወጡ እና በሕግ አግባብ እንዳይሠሩ ማድረጉን ቀጥሏል!
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከግጭት አዙሪት እንድንወጣ እና የሀሳብ የበላይነት አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ የመገናኛ ብዙኀን ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በጽኑ ያምናል።
መገናኛ ብዙኀኑ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በማጋለጥ፣ ዜጎች በመረጃ የበለፀጉ እንዲሆኑ በማድረግ በሥልጣን መባለግ እንዳይኖር እና መንግሥታዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን አይተኬ ሚና አላቸው።
መገናኛ ብዙኀን ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ፤ ነፃ ገለልተኛና የመረጃ ብዝኀነትን የሚያስተናግዱ ሊሆኑ ይገባል። ይህ በማይሆንበት ጊዜ አሰራራቸውን ሊቆጣጠር የሚገባው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሠጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የተለያዩ የእርምት እርምጃዎችን የመውሠድ ኃላፊነት እንዳለበት ይታወቃል።
ይሁን እንጂ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣኑም ሆነ የሕዝብ መገናኛ ብሮድካስቶች ሃቀኛ የህዝብ ድምጽ የመሆን ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የተሞሉ በመሆናቸው ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ባሻገር ሲያልሙ መመልከት አልተቻለም።
ኢዜማ እነዚህን በህዝብ መገናኛ ብዙኀን ስም በየዘመኑ ለሥልጣን የበቁ ገዢዎችን ፍላጎት ለማስፈፀም ከመሯሯጥ ውጪ የድሃን በደል እና የተዛነፈውን ፍርድ የማጋለጥ ስራ የዘነጉ መገናኛ ብዙኀኖች ከድርጊታቸውም እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ እንደከረመ የሚታወቅ ነው፡፡
ለዚህም ማሣያ ፓርቲያችን በተደጋጋሚ በጥቁር እና ነጭ የተፃፉ ሕጎች ተጥሰው ለመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣንም ሆነ ለሕዝብ መገናኛ ብሮድካስት የተሾሙ የገዢው ፓርቲ አባላት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ፣ ባለቤትነታቸው ከዚህ ቀደም የኢህአዴግ የልማት ድርጅቶች የነበሩና ይህ ፓርቲ ሕጋዊ ማንነቱን ካጣ በኋላ በየትኛው አካል ባለቤትነትና አስተዳደር ሥር እንደሚገኙ በይፉ እንዲገለጽ ታህሣሥ 20/2015 ዓ.ም. “በመንግስት የጎበጡት የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ነጻ ይውጡ” እንዲሁም መጋቢት 21/2015ዓ.ም. “እድል የተነፈጉ የተሻሉ ሃሳቦቻችን” በሚሉ ርእሶች ጥያቄ ያቀረብንባቸውን መግለጫዎች የመገናኛ ብዙኅን ባለሥልጣኑ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ዝምታን መምረጡ ይታወሳል።
ይኸው የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ከተልዕኳቸው ውጪ የገዢው ፓርቲ ልሳን ሆነው የህዝብን በደል እና የመንግሥትን ብልሹ አሰራር ጆሯቸውን ደፍነው ዘወትር የውዳሴ ዘገባ ለገዢው ፓርቲ እና መንግሥት በማቅረብ ለተጠመዱት የህዝብ መገናኛ ብዙኋን ምንም አይነት ተግሳጽ እንኳ ሳያቀርብ ባለፈው እሁድ ግንቦት 13/2015 ዓ.ም ለማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት በፃፈው ደብዳቤ ብሮድካስት ባለፍቃዱን በጊዜያዊነት ማገዱን ገልጿል። ይህ የእግድ ውሳኔ ምክንያቱ ሕጋዊ ሆነም አልሆነ በመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1238/2021 አንቀጽ 73፣ 76 እና 81(2) የተጠቀሱትን በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የመስጠትም ሆነ የሚዲያ ተቋሙ ራሱን እንዲከላከል ቀድሞ እድል የመስጠት ሕጋዊ ግዴታውን የጣሰ መሆኑን ኢዜማ ተረድቷል።
ተቋማት የሚወስዷቸው እርምጃዎች በእርግጥም ሕግን ከማስከበር መነሻነት ይልቅ በማን አለብኝነት ድርጅታዊ ፍላጎትን ብቻ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ከዚህ በላይ ፓርቲያችን በተደጋጋሚ ባነሣቸው ጥያቄዎች እና የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣኑ በማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ላይ በወሰደው ግብታዊ እርምጃ በግልፅ መረዳት ይቻላል።
“በመሆኑም ተቋማቱ ከእንደዚህ አይነት ወጥነት እና ገለልተኝነት የጎደለው ተግባር እንዲወጡ ብሎም የሚጠበቅባቸውን ዴሞክራሲ የማንበር ሚና እንዲጫወቱ አስቻይ ሁኔታን ለማንበር ይረዳ ዘንድ ከዚህ መሰል ተግባራቸው በአስቸኳይ እንዲወጡ እያሳሰበ፤
1) የመገናኛ ብዙኀንን ጨምሮ ገለልተኛ ሊሆኑ የሚገባቸው ተቋማት ከገዢው ፓርቲ አባላት ተጽዕኖ ነፃ ማውጣት፤
2) የመንግሥት እና የፓርቲ አሠራር የተለያዩ መሆናቸውን በሕግም በተግባርም ማረጋገጥ፤
3) የሚወሰዱ እርምጃዎች ሕግ እና ሕግ ላይ ብቻ መሠረት ያደረጉ ሲሆን ብቻ መሆኑን እናሳውቃለን።
ስለዚህ የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣን ወሰን ተላልፎ የወሰደውን ይህን ሕገ ወጥ ውሳኔ እንዲሽር፤ ብሎም ይህን ውሳኔ ያሳለፉትን አካላት ተጠያቂ በማድረግ ለሕዝብ እንዲያሳውቅ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡