በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከ እናት_ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ካህናትን በጠራራ ፀሐይ ወግሮ መግደል የሃይማኖታዊ ጥቃቱ የቀጠለው ምዕራፍ ነው!
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያ‘ንና ሕዝቧን ይጠብቅ መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም

መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ፉሪ አካባቢ ቀሲስ ዓባይ መለሰ የተባሉ ካህን ቅዳሴ ጨርሰው ወደ ቤታቸው በመሄድ ላይ እያሉ በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል። ይህንን አስነዋሪ ድርጊት ለማጋለጥ በሰዓቱ የነበረውን ኹኔታ በምስልና ቪዲዮ ለማስረጃ ለመያዝ የሞከሩ ሰዎች ቢኖሩም በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ሞባይል በመሰብሰብ የቀረጹትን ምስልና የቪዲዮ ማስረጃ እንዳጠፉባቸው ታማኝ ምንጮች ዘግበውታል። ጉዳዩ ቀደም ብሎ ከፍ ባለ ዛቻና ማስፈራሪያ የታጀበ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን በዚህ ኹኔታ ግን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ያደርጉታል የሚል እምነት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል፡፡
ፓርቲያችን ድርጊቱን የፈጸሙት አካላት ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ መረጃ እንዳይደርስ ያደረጉ አካላት እኩል የድርጊቱ አባሪና ተባባሪ በመሆናቸው ይዘገይ እንደሆነ እንጂ ከሕግ ተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ሥርዓት መር የሆነውና ሃይማኖትን ማዕከል ያደረገው ጥቃትና ጭፍጨፋ በአስቸኳይ እንዲቆም ያገባኛል የሚል አካል ኹሉ እንዲረባረብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም ፓርቲያችን ድርጊቱን በጽኑ እያወገዘ በአሰቃቂ ኹኔታ ለተገደሉት አባት እርፍተ ነፍስን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ደግሞ መጽናናትን ይመኛል።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ
እናት ፓርቲ
መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ