( መሳይ መኮንን ) ጃዋር መሀመድ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ውስጥ ለውስጥ በትኗል። በኦሮምኛ ቋንቋ ያዘጋጀው ባለ 76 ገጽ ጽሁፍ ዋና ዋና ሀሳቦች ተጨምቀው በአንድ ወዳጄ ተልኮልኝ አነበብኩት። የኦሮምኛው ጽሁፍ ረጅም ነው። ጃዋር ዘለግ አድርጎ ያዘጋጀው ፍኖተ ካርታ የኦሮ
ሞ የበላይነትን ማስፈንን በተመለከተ ዝርዝር አፈጻጸም የሚያሳይ እንደሆነ ተረድቼአለሁ። 76ቱ ገጽ በአጭሩ ሲቀመጥ አራት ነጥቦችን ይይዛል። የመጀመሪያው፡ አሁን የኦሮሞ ትግል ያስገኘውን ድል በሚገባ መረዳት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የሚያትተው ክፍል ነው። ኦሮሞ ስልጣን የያዘው በ70ዓመታት ትግል ውጤት መሆኑን የሚገልጸው የጃዋር ጽሁፍ በተሳካ ሁኔታ የኢትዮጵያን ስርዓተ መንግስት ተቆጣጥረናል ሲል ይደመድማል። ቀጣዩ ስራ ይህን የተቆጣጠርነውን ስልጣን ወደ አንድ መሰብሰብና ቅቡልነት እንዲኖረው ማድረግ ነው ይላል።
ሁለተኛው የጃዋር ፍኖተ ካርታ አንኳር ጉዳይ አሁን ያለውን ትርክት መቀየር ስለሚቻልበት ሁኔታ የሚያትተው ነው። በዘዴና በስልት የራሳችንን ትርክት የበላይነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባልናል ይላል አቶ ጃዋር። በየትም ይሁን በየት፡ በማንኛውም አይነት መስዋዕትነት፡ የሚከፈለው ዋጋም ቢሆን ተከፍሎ አሁን የያዝነው ስልጣን ከእጅ እንዳይወጣ ማድረግ ቁልፍ ተግባር እንዲሆን በሚል መንፈስ በፍኖተ ካርታው ተቀምጧል። ሶስተኛው ትልቁ የፍኖተ ካርታው ሀሳብ የ70 ዓመቱ ትግል በኦሮሞ ስም የነበረውን በመቀየር ”ኢትዮጵያ” ወደሚል ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት ይገልጻል። በጃዋር ፍኖተ ካርታ ልትፈጠር የታለመችው ”ኢትዮጵያ” አሁን ያለችዋ አይደለችም። በግልጽም እንደተቀመጠው ”ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም ወስደን የኦሮሞ ማንነት እናለብሰዋለን ይላል። አገላለጹን ቀየርኩት እንጂ ሀሳቡን አለወጥኩትም።
ከአንድ ዓመት በፊት የብልጽግና አመራር አባል የሆኑትና የኦሮሞ ብልጽግና መሀንዲስ ተብለው ከሚጠሩት አንዱ ከዶ/ር ቢቂላ ሁሪሶ ጋር በዋትስ አፕ የተመላለስነው መልዕክት ትዝ አለኝ። ”ብልጽግና የሚታገልላት ኢትዮጵያ እናንተ ፍሬም ካደረጋችኋት ኢትዮጵያ የሰማይና የምድርን ያህል ትራራቃለች” የሚል ነበር የዶ/ር ቢቂላ የዋትስ አፕ መልዕክት። በእርግጥ ገብቶኛል። አሁን የጃዋር ፍኖተ ካርታ ደግሞ የበለጠ ግልጽ አደረገልኝ። አረ እንደውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሞ ብልጽግና የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና የሚያቀነቅናቸው ትርክቶች የምትገነባው ”ኢትዮጵያ” ምን ልትመስል እንደምትችል ፍንትው አድርገው አሳይተውኛል።
ወደ ጃዋር ፍኖተ ካርታ ልመለስ። አራተኛው የፍኖተ ካርታው ቁልፍ ሀሳብ በስልጣን ላይ የሚገኙትን ጠ/ሚር አብይ አህመድን የሚቃወም የኦሮሞ የፖለቲካ ሃይል ለጊዜው እጁን ከእሳቸው ላይ እንዲሰበስብ ጠብሰቅ አድርጎ የሚመክር ነው። የጃዋርን ስጋት በአረፍተነገሮቹ መሀል ማንበብ ይቻላል። አማራ ስልጣኑን ሊነጥቀን አድብቷል፡ የኦሮሞ የፖለቲካ ሀይሎች ልዩነታቸውን ለጊዜው ወደጎን አድርገው አራት ኪሎ ከእጃችን እንዳይወጣ በማድረጉ ላይ እናተኩር ሲል አጥብቆ ይማጸናል። ጠ/ሚሩን አሁን ላይ እግራቸውን ለመስበር የሚደረግ ትግል የሚጎዳው ኦሮሞን ነው። በ70ዓመት ትግል የተገኘውን ድል ሊያሳጣን ስለሚችል ዶ/ር አብይ ላይ ነፍጥ ያነሳችሁ አውርዱትና ከጎቸው እንሁን የሚል ግልጽ መልዕክት የተላለፈበት ፍኖተ ካርታ ነው። አመላችንንና ጠባችንን በቤታችን ይዘን፡ ስልጣናችን ዘለቄታዊ እስኪሆን በአንድ ላይ እንቁም በሚልም ሊገለጽ የሚችል ነው።

እየሆነ ያለውን ገጣጥሞ መረዳት ቀላል ነው። አዲስ አበባ መሀሏ እየፈራረሰ ነው። ነባር መንደሮች እየጠፉ ነው። ሲጠፉ ታዲያ ጣሪያና ግድግዳቸው ብቻ አይደለም። በዘመናት የተገነባው ኢትዮጵያዊ መስተጋብሩም ጭምር ነው። አይናችንን ካልጨፈንን፡ ልቦናችንን ጥርቅም አድርገን ካልዘጋን በቀር የሚሆነው ግልጽ ሆኖ ይታየናል። የጃዋር ፍኖተ ካርታ እንደውም ዘግይቶ የመጣ ይመስላል። አሁን ይህን እየጻፍኩኝ ስልኬ ቅጭልል የሚል ድምጽ አሰማችኝ። ፈረሳው ጦፏል፡ ማፈናቀሉ ተጠናክሯል። ምን እስክንሆን ነው የሚጠበቀው? ይሉኛል አንድ አባት በቀጭኗ ሽቦ ከአዲስ አበባ።