በኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል የተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚነት ምን ይመስላል?

ሦስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቀ ጳጳሳት ጥር 14/2015 ዓ.ም ፈጽመውታል የተባለውን የ25 ጳጳሳት ሹመትን ተከሎ የመጣው ውዝግብ ለሳምንታት የቆየ ውጥረትን ፈጥሮ ነበር።

ሹመቱን የፈጸሙት ሦስቱ ሊቀነ ጳጳሳት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ በአፍ መፍቻ ቋንቋ አገልግሎትን ማስፋፋት አልተቻለም እንዲሁም ቅዱስ ሲኖዶሱ ከአንድ አከባቢ በመጡ የበላይነት ስር ወድቋል በሚል ምክንያት ሹመት እንደሰጡ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

ክስተቱ ቀኖናና ስርዓትን የጣሰ ነው በሚል በቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛ ተቃውሞም ገጥሞታል። ሹመቱ ከተፈጸመ ከቀናት በኃላ ሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ ሹመት የሰጡና የተቀበሉ አባቶችን በሙሉ አውግዞ ስልጣነ ክህነታቸውን ሽሯል።

ክስተቱ በወቅቱ ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሮ የነበረ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች የሰዎች ሕይወት አልፏል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረትም እንዲወድም ምክንያት ሆኗል።

ጉዳዩም ወደፍርድ ቤት አምርቷል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተገኙበት በጽህፈት ቤታቸቸው በውግዘት ተለይተዋል በተባሉትና በቅዱስ ሲኖዶስ በተወከሉት አባቶች መካከል ውይይት ከተደረገ በኃላ ቸግሩ በስምምነት መቋጨቱ ተገልጿል።

ስምምነቱ አስር ነጥቦች ያሉት ሲሆን የቋንቋ አገልግሎትን ማስፋት፣ ለኦሮሚያ ክልል ቋንቋውን የሚያውቁ ጳጳሳት መሾምና የተላለፈውን ውግዘት ማንሳት ከስምምነቶቹ መካከል ይገኙበታል።

ከተወገዙት አባቶች መካከል አንዱ የሆኑት አቡነ ሳዊሮስ ስምምነቱን ያለመሸራረፍ እንፈጽማለን ሲሉ ቃል ገብተው ነበር።

ከስምምነቱ በኋላ ምን ተፈጠረ?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ትናንት መጋቢት 6/2015 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ በጥር ወር አጋማሽ ተሹመዋል የተባሉት አባቶች ከስምምነቱ በተቃራኒ “በህገ-ወጥ አድራጎታቸው ቀጥለዋል” ብሏል።

መግለጫው አክሎም “ግለሰቦቹ. . . በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠውን እግድ በመጣስ የአህጉረ ስብከትን ጽ/ቤት እየሰበሩ በመግባት በሌላቸው ሥልጣን ክህነት በመስጠት፣ በመዋቅራችን ላይ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞችን በመመደብ” ይገኛሉ ሲል ገልጿል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አያሌው ቢታኔ “ህገ ወጥ ድርጊቱ እሰከ ትላንትና ወዲያ [መጋቢት 4/2015] ድረስ ቀጥሎ ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህም ጉዳይ ላይ ለመምከር የቅዱስ ሲኖዶስ ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚገኙና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳትን በመጥራት መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጉን አመላክቷል።

በስብሰባው ላይ ሹመት ሰጥተዋል የተባሉት “ሦስቱ የቀድሞ ብፁዓን አባቶች በአካል ቀርበው በሰጡት ቃል በተከናወነው ድርጊትና ድርጊቱን ተከትሎ በተፈጸሙት ክስተቶች ማዘናቸውንና በቀጣይ ሕገ-ወጥ ድርጊቱን እንደሚቃወሙና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶሱን መመሪያ አክብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን” መግለጻቸው ተጠቁሟል።

“25ቱ ግለሰቦች” [ሹመት እንደተሰጣቸው የተገለጸው] በስምምነቱ መሰረት ከመጋቢት 6/2015 እሰከ 11 ባሉት አምስት ቀናት ውስጥ “የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በጽሑፍ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉና በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀኖናቸውን ተቀብለው እንዲፈጽሙ” ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

በመግለጫው ቤተ ክርስቲያኗ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር ውይይት መደረጉና እሳቸውም “ሃያ አምስቱንም ግለሰቦች ‘አጠቃልዬ ወደ አዲስ አበባ አመጣቸዋለሁ’ ” ማለታቸውን መግለጫው አትቷል።

ርዕሰ መስተዳደሩ “በገቡት ቃል መሰረት” ‘ግለሰቦቹ’ ወደ አዲስ አበባ እየገቡ እንደሆነ ሰምተናል ሲልም አክሏል።

በሌላ በኩል ሶስቱ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና አቡነ ዜና ማርቆስ ላይ ስምምነቱን በማክበራቸው ደሞዛቸው መከፈል እንዲጥል መወሰኑን አስረድተዋል።

ሀኖም ውግዘታቸው የሚነሳው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዕተ ጉባኤ በመሆኑ የሲኖዶሱ አባላት በሙሉ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም. ለስብሰባ እንዲገኙ ወስኗል።

መግለጫው መንግሥት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ድርሻውን እንዲወጣና የታሰሩ የቤተክስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምዕመናን እንዲፈቱም ጥሪውን አቅርቧል።

የቤተክርስቲያኗ የፍርድ ቤት ክስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አያሌው ቢታኔ ስምምነቱ ባለመከበሩ ምክንያት በቤተክርስቲያኗ የተጀመረው የፍርድ ቤት ክስ መቀጠሉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ህገ ወጥ ድርጊቶቹ ሲቆሙ ነው ስምምነቱ ተፈጻሚ ሆነ የሚባለው። የፍርድ ቤት ሂደትን በተመለከተ ይቋረጣል አይቋረጥም የሚለውን የሚወስነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው” ብለዋል።

ሰብሳቢው “25ቱ ግለሰቦች” ላይ የተጣለው ዕግድ አሁንም እንደጸና የገለጹ ሲሆን ለስምምነቱ ተገዢ የሚሆኑ ከሆኑ “ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጠን አቅጣጫ መሰረት ወደፊት የሚቀጥል ይሆናል” ሲሉ አክለዋል።

እስከ መጋቢት 18/2015 ዓ.ም ድረስ ክስ በማደራጀትና ተከሳሾችን በመለየት ክስ እንዲቀርብ ፍርድ ቤት ማዘዙን የገለጹ ሲሆን የጠበቆች ቡድንም ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቀሰዋል። ይህ የሚሆነው ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ የተለየ ትዕዛዝ እስካልመጣ ድረስ ብቻ መሆኑንም አንስተዋል።

“ቤተ ክርስቲያን የአምስት ቀን ጊዜ ሰጥታለች እነኚህ ሰዎች አሁንም ተመልሰው መጥተው፣ የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብለው ምላሽ እስካልሰጡ ድረስ የህጉ ስርዓት እንደቀጠለ ነው የሚቀረው” ብለዋል።

በተጨማሪም ከክሰተቱ ጋር በተያያዘ “በተለይ በኦሮሚያ ክልል ላይ አሁን የታሰሩ አሉ” ያሉት ሰብሳቢው በሻሸመኔና አርሲ ኔጌሌ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ያላቸውና ጉዳያቸው ታይቶ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የተሰጠባቸው አገልጋዮችና ምዕመናን እንዳሉም ጠቁመዋል።