ከኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና ኦነግ ሸኔ ጭፍጨፋ የተረፉ የአማራ ተወላጆች ባሕር ዳር ገቡ

ከምስራቅ ወለጋ ኪራሞ ወረዳን ጨምሮ ከተለያዩ አከባቢዎች ከኦሮሚያ ልዩ ሃይል እና ግብረአበሮቻቸው ጭፍጨፋ የተረፉ የአማራ ተወላጆች ከሳምንት በላይ በእግራቸው ተጉዘው ጥር 15/2015 ዓ/ም ባህርዳር ከተማ ገብተናል ሲሉ ለአሻራ ሚዲያ ተናገሩ።

በመንግስት ትዕዛዝ በሚንቀሳቀሰው የኦሮሚያ ልዩ ሃይል እና በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ጥምረት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት አማራዎች ነፍሳቸውን ለማትረፍ በጫካ እያደሩ ከብዙ ድካም እና ሲቃይ በኋላ ባህርዳር መግባታቸውን ተፈናቃዮች ተናገሩ። መታረድን በመፍራት የለበስናትን ልብስ እንደለበስ ነው የወጣን ብለዋል። ማምለጥ ያልቻሉት ህፃና፣ አዛውንት እና ነፍሰጡር ሴቶች በርካቶች ቤት እንደተዘጋባቸው ተቃጥለዋል ነው ያሉት ተፈናቃዮቹ። ከየቀሩት ደግሞ እንደበግ ታርደዋል ሲሉ በፀፀት ተናግረዋል።

አሸባሪው ሃይል ወልደን ያሳደግንበትን ቤታችንን እና ለበርካታ አመታት ያፈራነውን ሃብት ንብረታችንን የቻሉትን ዘርፈው ያልቻሉትን ደግሞ አቃጥለው እና አውድመው ሜዳ ላይ ጥለውናል። ቤተሰቦቻችንን በግፍ ገድሎብናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደን ሲሉ ገልፀዋል።

አክለውም አሁንም በወለጋ ምድር የአማራ ሞት አልቆመም። እኛ እድለኛ ሁነን እዚህ ደርሰናል። በየቀኑ አማራው በግፍ እየተገደለ ነው ። ይህ ድርጊት በቃ ሊባል ይገባል። መንግስት በህይወት ላሉት ይድረስላቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግስትም ድጋፍ እንዲያደርግላቸው መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ምግብ እና ውሃ በማቀበል አቀባበል ያደረገላቸውን የባህርዳር ህዝብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አሻራ ሚዲያ