የአማራ ክልል የልዩ ኃይል የብርጌድ አዛዥ እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰላም እና ደህንነት ኃላፊ በጥይት ተመቱ

የአማራ ክልል የልዩ ኃይል የብርጌድ አዛዥ እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰላም እና ደህንነት ኃላፊ በጥይት በመቁሰላቸው ሆስፒታል መግባታቸው ተሰማ።
የአማራ ክልል የልዩ ኃይል የብርጌድ አዛዥ ኮሚሽነር ዋኘው አዘዘው እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰላም እና ደህንነት ኃላፊ ዳኛቸው በለጠ በጥይት ተመተው መቁሰላቸውን ተከትሎ ሆስፒታል መግባታቸውን የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ምንጭ ተናግረዋል።
ምንጫችን ጥቃቱ በሽጉጥ እንደተፈጸመ ቢገልጹም ድርጊቱን የፈጸመውን አካልም ሆነ መነሻ ምክንያቱን ለጊዜው እንዳላወቁት ገልጸዋል።
ሁለቱም በጥይት የተመቱት ጥር 10/2015 ከምሽቱ 5:30 ገደማ በጎንደር ከተማ ቀበሌ 1 ብሉኮ በተባለ አካባቢ መሆኑን ነግረውናል። በሽጉጥ ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል ያሉት ምንጫችን ስለጉዳቱ መጠን ሲናገሩም አንደኛው አንገቱ ላይ ሌላኛው ደግሞ ደረቱ አካባቢ የተመታ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።