የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ጎንደር የገቡት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የፊታችን ጥር 11 በድምቀት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ የዓለም አገራት እና ከአገር ውስጥ ወደ ጎንደር ከተማ የገቡት ሰዎች ቁጥር ከዚህ ቀደሙ በተለየ መልኩ ብዛት ያለው መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከትልልቅ ሆቴሎችን እስከ አነስተኛ አልጋ ቤቶች ቀድመው ተይዘዋል ተብሏል፡፡ በዛሬው ዕለት በከተማዋ አልጋ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆሙት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ገና በዋዜማው ከተማዋ በከፍተኛ ሰው ብዛት መጨናነቋንም ገልጸዋል፡፡

በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማወ የገቡ እንግዶችን በጎንደር ዩንቨርስቲ የተማሪዎች ዶርም እና በባዶ ቦታዎች ላይ ድንኳን በመጣል ለማስተናገድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ አልጋ እንዲይዙላቸው ለጠየቋቸው ሰዎች ማግኘት ባለመቻላቸው እቤታቸው ተቀብለው ማስተናገድን እንደ አማራጭ እየጠጠቀሙ ነው፡፡

የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ ለማክበር ወደ ከተማዋ ያቀናው ሰው ብዛት፣ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተገናኘ ያለው የሰላም ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱ አንዱ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ ጦርነት በነበረበት ወቅት የተከበረው የባለፈው ዓመት የጎንደር ጥምቀት በዓል ቀዝቀዝ ያለ እንደበር ነዋሪዎች አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንግድ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር የሚያደርገውን ዕለታዊ የበረራ ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩ ተስምቷል፡፡ በዚህም፤ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ጎንደር የሚሄዱ መንገደኞችን ለማጓጓዝ በአንድ ቀን ብቻ 22 በረራዎች ማድረጉን አስታውቋል፡፡

አዲስ ማለዳም ከአየር መንገዱ የትኬት መሸጫ ድህረ ገጽ ላይ መመለክት እንደቻለችው በዛሬው ዕለት ወደ ጎንደር የሚደረጉ የበረራ ትኬቶች ሙሉ በሙሉ ተሸጠው አልቀዋል፡፡
__