በቀን አንድ ዶላር ሳይሆን በሁለት ወር አምሳ ሳንቲም ብቻ ? መሆን የለበትም። #ግርማካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

ዶ/ር አብይ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በሁለት ወር ጊዜ ግማሽ ሚሊዮን ብር ብቻ በመሰብሰቡ ማዘኑን ገልጿል። ማዘኑም ተገቢ ነው።

ከአንድ ወር በፊት ” በ 3 ሳምንታት $250000 ብቻ? ከዚህ በላይ ማድረግ እንችላለን” ብዬ ችግሮች እንዳሉ በመግለጽ የማሻሻያ ሃሳቦችን አቅርቤ ነበር።

የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ላለፉት ሁለት ወራት ፣ ከኦክቶበር 22 2018 ጀምሮ ለልማት ባሰባሰበው ገንዘብ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ገንዘብ እንደተሰበሰበ በድህረ ገጹ አሳውቋል። ገንዘብ ላዋጡ 2819 ዜጎችንም እናመሰግናለን ብሏል።

ይህ ገንዘብ እጅግ፣ እጅግ በጣም ትንሽ ገንዘብ ነው። ለምን እንደሆነ ላስረዳ። የተባለው አንድ ዶላር በቀን ነው። ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ ተብሎ ነው የሚገመተው። ሆኖም በዚህ ጽሁፍ ላይ አንድ ሚሊዮን ነው ያለው ብለን እንውሰድ። በቀን አንድ ዶላር ከወሰድን በሁለት ወር ፣ በስድሳ ፣ ስድሳ ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ ነበረበት። ግን የተሰበሰበው መሰብሰብ ከነበረበት ከአንድ በመቶ በታች ነው።

በሌላ መልኩ ላስቀምጠው፣ አንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ አባል በሁለት ወር አምሳ ሳንቲም እንዳዋጣ ማለት ነው።

ያለ ምንም ጥርጥር ዳያስፖራ በአመት ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ዶላር ማዋጣት ይችላል። አቅሙ አለው።

እንግዲህ ጥያቂዎች መጠየቅና መሰረታዊ ግምገማዎች ማድረግ ያስፈለጋል። ይሄንን ሃይል ለምን በብቃት ማንቀሳቀስ አልተቻለም? ምንድን ነው ችግሩ? አሰራራችን እንዴት ብንቀየር ነው የበለጠ ዉጤት የምናመጣው? ብለን መጠየቅ አለብን።

ከወር በፊት የጻፍኩትን እንደገና ከልሼ የሚከተሉትስ አራት ነጥቦች እንደሚከተለው አቅርባለሁ፡

፩. የትረስት ፈንዱ ግሩማ ፕሮፌሽናል ድህረ ገጽ አዘጋጅቷል። ሆኖም ድህረ ገጹ በእንግሊዘኛ ብቻ ነው። ድህረ ገጹ ላይ በአማርኛም መረጃዎች፣ ሪፖርቶች ቢቀርቡ ጥሩ ነው። እንግሊዘኛ የማያውቅ፣ ወይንም እንግሊዘኛ በቀላሉ አንብቦ መረዳት የማችይል ብዙ ወገኖⶭ እንዳሉ መርሳት የለብንም።

፪. የትረስት ፈንድ ኮሚቴ ወደ ታች ወርዶ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እስከ አሁን የቻለ፣ ኮሚቴዉን ለማገዝ ኢትዮጵያዊያን በበቂ ሁኔታ የተነሱ አይመስልም ። ለዚህ ስራ ትልቅ ድርጅታዊ መዋቅር ያስፈለጋል። አስር ሰዎች ሁሉንም ነገር ሊያደርጉ አይችሉም። ኮሚቴውም ሌሎችን ማሳተፍና ማሰራት መቻል አለበት። ሌሎችም በራሳቸው አነሳሽነት ለመስራት የሚፈለጉትን ማበረታታት አስፈላጊ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ ነው። ዳያስፖራዉን በቀጠና በመክፈል፣ የቀጠና አደራጆችና አስተባባሪዎች ማሰማራቱ አስፈላጊ ነው። ጉዳዩ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነዉና !!!!!

፫. . ገንዘብ አዋጡ ብቻ ማለት በራሱ በቂ አይደለም። ኮሚቴው ቢያንስ ፕሮጀክቶችን ነድፎ፣ “በዚህ አመት እነዚህን ፕሮጀክቶችን ነው የምናስፈጽመው፣ ይሄን ያህል ገንዘብ ነው የሚያስፈልግን ..” ብሎ ቢቀርብ፣ በጣም ይረዳል። ለምሳሌ፣ አንደኛ – በዚህ አመት በቆቦ፣ በራያና አዘቦ ፣ በነገሌ ቦረና፣ በአፋር (ብዙ ጊዜ በድርቅ የሚጎዱ አካባቢዎች) ድርቅ ሲመጣ ለአደጋ እንዳይጋለጡ መቶ የዉሃ ጉድጓዶችን የማስቆፈር፤ ሁለተኛ – በጂንካ፣ አሰላ፣ ጂጂጋ፣ ሸዋሮቢት፣ ሽሬ ላሉ ሆስፒታሎች አንዳንድ አንድ የ MRI ማሽን የመግዛት እቅድ ነው ያለን፣ ወጭዉን ይሄን ያህል ነው” ብለው ቢገልጹ ገንዘቡ የት እንደሚዉል ሰው ስለሚያውቅ የበለጠ ይነሳሳል። እንደምሳሌ እነዚህን አቀርብኩ እንጂ ሌሎች ፕሮጀክቶችም ሊሆኑ ይችላሉ።

ገንዘቡ ለምን እንደሚውል ሳይታወቅ፣ አዋጡ ማለት፣ ትንሽ ሰው በስሜት እንዳይነሳሳ ያደርገዋል። በዚህ ረገድ ኮሚቴው ሰዎች ለዚህ ታላቅ ተልእኮ እንዲነሳሱ creative በሆነ መልኩ መቅረብ ያለበት መሰለኝ።

፬.. የዶ/ር አብይ አስተዳደር ላይ ብዙዎች ጥያቄ ምልክት ማድረግ መጀመራቸውም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽኖ ነበረው፣ አለውምም። ዶ/ር አብይ በቂ ገንዘብ ባለመሰብሰቡ አዝኖ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን መዉደዳቸው በተግባር እንዲያሳዩ ጠይቋል። ትክክል ነው።

ግን ደግሞ እርሳቸው በቃል የሚናገረውን የመደመርና የኢትዮዮጵያዊ ፖለቲካን በተግባር በፖሊሲ፣ በሕግ መተግበር እርሱም እንደ አገር መሪነቱ ይጠበቅበታል። በተለይም የዘር ፖለቲካው አሁንም መቀጠሉ፣ በዜጎች ላይ የሚደርሰው መፈናቀል ፣ በአዲስ አበባ ልጆች ላይ የተፈጸመው ግፍ ፣ የዶ/ር አብይ አመራርም ዝምታን መምረጡ፣ ብዙዎችን ግራ ያጋባበት ሁኔታ ነው የነበረው። ለዚህም ነው በአማራ ክልል የተቃዉሞ ሰልፎችም የተደረጉት።

አንድ ዶ/ር አብይ መዘንጋት የሌለበት ነገር ልማት ፣ ኢኮኖሚ፣ ኢንቨስትመንት ….ከፖለቲካ ጋር የተገናኘ ነው። ዜጎች ተስፋ ሊኖራቸው ይገባል። ለምሳሌ በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ፣ ቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ ያሉ ፣ አሁን በኦሮሞ ክልል ባለው ነገር ተስፋ አይታያቸውም። ዶ/ር አብይ ሕዝቡ ለርሱ ያለውን ድጋፍ ፎር ግራንትድ መቁጠርና ሁልጊዜ የሚኖር አድርጎ መውሰድ የለበትም።

የዶ/ር አብይ አስተዳደር፣ ፖለቲካው ከተበላሸ ሌሎች ነገሮችን ሊበላሹ እንደሚችሉ በመረዳት በተቻለ መጠን የሕዝብን ጥያቄ በመመለስና ፣ ለሕዝብ የተገባውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ዙሪያ ትልቅ ትኩረት ቢሰጥበት ጥሩ ነው እላለሁ።

ይሄን ብዬ ለኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ ይሄን እላለሁ። የለማ ቲምን ( እነ ገዱን ጨምሮ) ገና ስልጣን ሳይዙ አደጋ ላይ የነበሩም ጊዜ ስደግፋቸው ነበር። አሁንም ለነርሱ ትልቅ ድጋፍ አለኝ። ሆኖም የጭፍን ደጋፊ አይደለሁም። ጠንካራ ተቃዉሞዎችና ትችቶችን ያቀረብኩባቸው ጊዚያቶች ቀላል አይደሉም። የዶ/ር አብይ አስተዳደር ላይ ችግር የለብኝም ማለት አይደለም።

ሆኖም ግን በዚህ በትረስት ፈንዱ ዙሪያ ግን ያሉን የፖለቲካ ችግሮች ለአገራችንና ለሕዝባችን ድጋፍ እንዳንሰጥ ሊያግዱን በጭራሽ አይገባም። የዶ/ር አብይ አስተዳደር መቃወም ካለብን በምክንያት እየተቃወመን፣ መደገፍ ያለብንን ደግሞ በምክንያት መደገፍ አለብን። ይሄ የትራስት ፈንድ ጉዳይ መደገፍ ብቻ አይደለም ሌሎች እንዲደገፉት የራሳችን ጉዳይ አድርገን ነው መስራት ያለብን።

ወገኖች አንድ ዶላር በቀን፣ አንድ ቢሊዮን ዶላር በአመት ነው መሆን ያለበት !!!! እንችላለን !!!!!!!!!

በመጨረሻ ማዋጣት ለምንፈለግ እዚህ ጋር በመጫን – በቢጫ ሳጥን “Donate” የሚለውን በመጫን ማዋጣት እንችላለን።

https://www.ethiopiatrustfund.org/