የአማራ ክልል የሚባለው መፍረሱ ጥቅም አለው- ቅማንትን በተመለከተ – ግርማ ካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አንድ የሆነውን ሕዝብ በጎጥ ለመክፋፈል፣ የአማራ ክልል መንግስት በሕወሃት አዛዥነት የቅማንት ብሄረሰብ አስተዳደርን እንፍጠር በሚል ከስድሳ በላይ የሰሜን ጎንደር ቀበሌዎችን ወደ ቅማንት አስተዳደር አካቷል።

ወደ አርባ ሁለት ቀበሌዎች ከጅምሩ ነው ያለ ህዝብ ዉሳኔ መሬቱ የቅማንት ነው በሚል ከነባሩ የጎንደር ዞን የተለዩት ። በአስራ ሁለት ቀበሌዎች ሕዝብ ዉሳኔ ይደረግ ተብሎ ተወሰነ። በስምንቱ ህዝብ ዉሳኔ ተደረገ። በአራቱ ምርጫው ተላለፈ።

ምርጫ ከተደረጋባቸው ስምንት ቀበሌዎች ሰባቱ “እኛ አንድ ነን” ብለው በነበረው የጎንደር ዞን ስር ለመቀጠል ድምጽ ሰጡ። ኳቤር ሎምየ በተባለው ቀበሌ ግን፣ የቀበሌው ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ድምፅ በመስጠታቸው፣ ወደ ቅማንት አስተዳደር የሚለው አዘነበለና ቀበሌው ወደ ቅማንት አስተዳደር ዞረ። ሆኖም ከሌላ ቦታ የመጡ ሰዎች ናቸው የመረጡት በሚል ተቃወሞ በመነሳቱ ጉዳዩ እስከአሁን እልባት አላገኝም።

ወደፊት ምርጫ ይደረግባቸዋል የተባሉ ላዛ ሹምየ፣ አንከራ አዳዛ፣ ገለድባና ናራ አውዳርዳ በተባሉ አራት ቀበሌዎች እንደተባለው ምርጫ ሳይደረግ፣ ህዝብ ሳይጠየቅ ዉሳኔ ተላለፈባቸው። ላዛ ሹምዬና አንከራ አዳዛ የተባሉት ቀበሌዎችን ለሁለት ከፍለው ግማሹ ወደ ነባሩ የጎንደር ዞን ግማሹን ወደ ቅማንት ሸነሸኑ። ሶስተኛውን የናራ አውዳርዳ ቀበሌ ወደ ቅማንት ፣ አራተኛው የገለድባና ቀበሌ ደግሞ በነባሩ አስተዳደር እንዲቀጥል አደረጉ። እንግዲህ እነዚህ አራት ቀበሌዎች ምርጫ ይደረግባቸዋል ተብሎ ነው ፣ ያ ታጥፎ፣ ህዝብ ሳይጠየቅ ዉሳኔ የተላለፈባቸው።

መጀመሪያ ወደ ቅማንት እንዲገቡ ከተወሰኑት አርባ ሁለት ቀበሌዎች በተጨማሪ ከሃያ በላይ ወደ ቅማንት እንዲገቡ የተደረጉ ቀበሌዎች እንዳሉ ይነገራል። ሆኖም የትኞቹ እንደሆኑም በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም።ተሸፋፍኖና ተደባብቆ ነው ያለው።

እንግዲህ የቅማንትን ብሄረሰብ አስተዳደር የሚባለውን ስንመለከት፣ ከአንድ ቀበሌ በቀር፣ ምርጫ ተደርጎ ወደ ቅማንት አስተዳደር የተጠቃለለ ቀበሌ የለም። ይሄም አንዱ ቀበሌ፣ ከሌላ ቦታ የቀበሌው ነዋሪዎች ያልሆኑ በማጭበርበር እንዲመርጡ በመደረጉ ነው ቅማንት ወደሚለው ያዘነበው። የዚህም ቀበሌ ጉዳይ አሁን ድረስ በእንጥልጥል ነው ያለው።

በመጨረሻ በጭልጋ ወረዳ የምትገኘው የአይከል ከተማን በተመለከተ በአንድ በኩል በጣም የሚገርምና የሚያስቅ በሌላ በኩል ደግሞ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነጥብ ላካፍላችሁ። ምን ያህል መዉረዳችንን ከዚህ ማየት እንችላለን።

የአይከል ከተማ እንደ ሌሎቹ ቦታዎች ቅማንት አማራ ሳይባባል ሕዝብ ለዘመናት ኖሯል። አህን ግን ቅማንት አማራ ብለው መለየት ጀምረው ከተማዋን ምን ያድርጓት? ወደ ቅማንት አስተዳደር ቢወስዷት አማራው ሊቆጣ ነው። በነበረው አስተዳደር ብትቀጥል በቅማንት አስተዳደር ትልቅ ከተማ አይኖርም። ስለዚህ ከተማዋ የሁለት መንግስታት መቀመጫ እንድትሆን ነው የተስማሙት። የቅማንት ብሄረሰብ አስተዳደር መቀመጫና በመራብ ጎንደር ዞን የጭልጋ ወረዳ አስተዳደር።

ምርጫ ተብሎ በነበረ ጊዜ ሁለት የቅማንት አባቶች እየሆነ የነበረውን አጥበቀው በመቃወም በወቅቱ ለሪፖርተር የሰጡትን አስተያየት በመጥቀስ ወደ ጽሁፌ መደምደሚያ ልዉሰዳችሁ።

‹‹ለዘመናት ተዋልደንና በደም ተሳስረን እንደዚህ ዓይነት ጉድ በመጨረሻ መጣብን” ሲሉ አንድ አባት ሌላው አባት ደግሞ “እኔ ዘጠኝ ልጆች አሉኝ፡፡ እኔ ቅማንት ነኝ፡፡ ሚስቴ አማራ ናት፡፡ ሁላችንም አማራን (በነባሩ አስተዳደር መቀጠል) ነው የመረጥነው” ነበር ያሉት።

ቅማንትና አማራ አንድ ህዝብ ነው። አብዛኛው ቅማንት አማርኛ ነው የሚናገረው። በ’እድሜ ገፋ ያሉ ቅማንተኛ የሚናገሩ ጥቂቶች አሉ። እንደዚያም ቢሆን ቅማንተኛ ከአማርኛ ጋር በጣም የተቀራረበ ነው። ሕዝቡ ተዋልዷል። ቅምናትም አማራም የጎንደር ትልቃ ታሪክ ባለቤት ነው። መይሳው ካሳ ፣ አጼ ቴዎድሮስ እንደውም ቅማንት ነበሩም ነው የሚባለው። ሕዝቡ እንደ ጎንደሬ ነው በስላም ለዘመናት ይኖረው።

አሁን የአማራ ክልል መንግስት አማራ፣ ቅማንናት፣ አገው..የሚለውን የዘር ፖለቲካ አስወገዶ፣ የአማራ ክልል በማፍረስ፣ አራት ታሪካዊ የፊዴራል መስተዳደሮች እንዲያቋቁሙ በአክብሮት እጠይቃለሁ። አማራ፣ ቅምናት ፣ አገው ..መባባል አያዋጣም። የጎንደር፣ የጎጃም፣ የወሎ፣ የሸዋ ፌዴራል መስተዳድሮችን በማቋቋም ፣ ዘርንና ማንነት ከአስተዳደር በማወጣት ዜጎች በጎጥ መፋተጋቸውን ትተው ወደ ጋራ ልማታቸው እንዲያተኩሩ መደረግ አለበት። እንደ አይከል ያሉ ያላደጉ ከተሞች፣ ቅማንት፣ አማራ ከሚል ትርምስ መውጣጥ አለባቸው። ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንገዶች ነው የሚያስፈልጋቸው።

ያ ካልሆነ ግን የአማራ ክልል ዕተባለ፣ አማራ፣ አማራ ብቻ እየተባለ፣ በክልሉ የሚኖሩ አማራ ያልሆኑ ወገኖች ግን የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም።በመሆኑ አማራ ነን የሚሉ አማራነታቸው በግለሰብ ደረጃ ይዘ መቀጥል መብታቸው ነው። ግን አማራነት ከአስተዳደር ሙሉ ለሙሉ መዉጣት አለበት። የአማራ ክልል አያስፈልግም !!!

በምትኩ ፡

– የአማራ ክልል የሰሜንና ደቡብ ጎድነር ዞኖች፣ አሁን ቅማንት አስተዳደር የተባለውን፣ ውልቃይት ጠገዴን ያካተተ የጎንደር ፌዴራል መስተዳደር

– የአማራ ክልል የዋግመራ፣ የሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ የከሚሴ/ኦሮሚያ ፣ የትግራይ ክልል ራያና አላማጣን ያካተተ የወሎ ፌዴራል መስተዳደር

– የአማራው ክልል የምስራቅና የምእራብ ጎጃም፣ የባህር ዳር ልዩ፣ የአዋኢ ዞኖች እና የቤኔሻንጉል ክልል ያካተተ የጎጃም ፌዴራል መስተዳደር

– የአማራ ክልል አርጎባ ወርዳን፣ የስሜን ሸዋ ዞን፣ የኦሮሞ ክልል የሸዋ ዞኖችን በሙሉ፣ የቡራዩና የአዳማ ልዩ ዞኖች የአዲስ አበባ ከተማን፣ ከደቡብ ክልል የጉራጐ፣ የሃዲያ፣ የከንባትና ጥምባሮ የየምና የስልጤ ዞኖች ያከተተ የሸዋ ፌዴራል መስተዳደር

መኖሩ በጣም ይረዳል።