እውነት በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት አልተካሄደምን? (አቻምየለህ ታምሩ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


እውነት በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት አልተካሄደምን? (አቻምየለህ ታምሩ)

የወያኔ ፖለቲካና የመለስ ዜናዊ ርዕዮተ ዓለም የሆነው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ማዕከል በአማራ ላይ የሚፈጸም የዘር ማጥፋት ወይንም በእግሊዝኛው አጠራር Genocide (of the Amharas) ነው። ከጅምሩ ጀምሮ ወያኔዎች በረሀ የገቡት የአማራን ዘር አጥፍተው መቃብር ላይ የታላቋ ትግራይን ሪፑብሊክ የመመስረት ፕሮግራም ይዘው ነበር። ለአስራ አስምት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ጠላቶች እየታገዙ በኤርትራና በትግራይ በረሀ ከቆዩ በኋላ በተፈጠረው አለማቀፋዊ ለውጥና በደርግ አረመኔነት የተነሳ ሻዕብያን ተከትለው አዲስ አበባ እንደሚገቡ ሲያውቁት፤ ሲጀምሩ በፕሮግራም የያዙትን የዐማራን ዘር የማጥፋት ፕሮዠ በመንግሥትነት ከተሰየመው በኋላ ለማስፈጸም በግንቦት ወር 1981 ዓ.ም. «ኢሕአዴግ» የሚባለውን የማታለያ ጭንብል ሲመሰርቱ ወደ ርዕዮተ አለም ደረጃ ከፍ አድርገውታል። ይህንን ርዕዮተ ዓለማቸውን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ብለው የጠሩት ሲሆን የፈጠሯቸው ድርጅቶች ሁሉ አማራን ለማጥፋት ይሰሩ ዘንድ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር የፈጠሩትን ግንባርም በዚሁ ርዕዮተ ዓለማቸው ሰይመውታል።

አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባለውን የወያኔ ርዕዮተ ዓለም ዋና ማዕከሉ የዐማራን የዘር የማጥፋት ፕሮግራም ነው። ባለፉት ሀያ ሰባት የፋሽስት ወያኔ የአገዛዝ አመታት ውስጥ በዐማራ ላይ የተፈጸመው ግፍና በደል ባጋጣሚ የተከሰተ፤ የዐማራ የአይን ቀለም ስላላማረ የተፈጸመ አይደለም። ባለፉት ሀያ ሰባት የፋሽስት ወያኔ የአገዛዝ አመታት በዐማራ ላይ የተፈጸመው ግፍና በደል ታሪካዊ መነሻ ያለው፤ ተቋማዊ ቅርጽ የተሰጠውና በርዕዮት ዓለም የታገዘ ግፍና በደል ነው። የዚህ ጽሁፍ አላማ የኢትዮጵያ ጠቅላ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ «በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት አልተፈጸመም» በሚል ያቀረበው ንግግር ከድርጊትና ከሕግ አንጻር ምን ያህል የተሳሳተና አደገኛ እንደሆነ ማሳየት ነው። ስለሆነም ወረድ ብለን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሊመራው የተሰየመበት አብዮታዊ ዲሞክራሲው ግንባር የሚመራበትን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንነትና በዐማራ ላይ ያስከተለውን የዘር ማጥፋት ዘርዘር አድርገን ልንገልጸው እንፈልጋለሁ።

አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባለው የወያኔ ርዕዮተ ዓለም የሌሊኒን ፍልስፍና ሲሆን በባህሪው ያዳላል። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዲሞክራሲያዊ አይደለም። አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚነሳው ዲሞክራሲ የሚገባቸውና የማይገባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ ብሎ በማሰብ ነው። ዲሞክራሲ የሚገባቸውና የማይገባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ የሚለው የ «ያ ትውልድ» የግራ ፖለቲከኞች ሁሉ የፖለቲካ ሃይማኖት ቢሆንም ቅሉ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ግን ዋነኛ መነሻና ማጠንጠኛ ሀሳብ ነው።
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና ዲሞክራሲ አያስፈልጋቸው ተብለው እንዲጠፉ የሚፈለጉና የሚዘመትባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ወይንም ቡድኖች አንድም «በዘር» አልያም «በመደብ» ይለያሉ።

የወያኔ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ደርግ በሚያዚያ ወር 1968 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የብሔራዊ አብዮት ፕሮግራም ወይንም National Democratic Revolution (NDR) program ጋር አንድ አይነት ነው። የሁለቱ አገዛዞች ርዕዮተ ዓለም ማኅደር የካርል ማርክስ «Dictatorship of the Proletariat» ወይንም «የወዝ አደሩ አምባገነንነት» የሚለው ፍልስፍና ነው። የሁለቱ አገዛዞች አብዮታዊ ዲሞክራሲ ልዩነት በደርጉ የብሔራዊ አብዮት ፕሮግራም «ዲሞክራሲ አይገባውም» የተባለው የኅብረተሰብ ክፍል በመደብ የተለየ ሲሆን እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በ «ያ ትውልድ» እሳቤ «ፊውዳል፣ ባላባት፣ በዝባዥ፣ አብዮት ቀልባሽ፣ ወዘተ» ተብለው የማጥፋት ዘመቻ የተከፈተባቸው ናቸው።

ፋሽስት ወያኔ «ኢሕአዴግ» የሚባለውን የማታለያ ጭንብል ከመሰረተና በመንግሥትነት ከተሰየመ በኋላ ሃይማኖት ባደረገው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለሙ «ዲሞክራሲ አያስፈልገው» በሚል እንዲጠፉ የተፈረደባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በኮድ ስም ትምክህተኛ፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ ወዘተ ተብለው የተለየ ሲሆን ወያኔ ግን እነዚህን የኮድ ስሞች የሚጠቀመው ዲሞክራሲ አይገባውም የሚለውን ክፍል በቀጥታ ዐማራ ላለማለት ነው። ይህንንም ግልጽ የሚያደርግልን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ግንባሩ ርዕዮተ ዓለም ፋሽስት ወያኔ በ1967 ዓ.ም. ጫካ ሲገባ ትግሉ የፀረ ዐማራ አብዮታዊ ትግል እንደሆነ ካስቀመጠው የተቀዳ መሆኑና የዘር ማጥፋት ያወጀበት የኅብረተሰብ ክፍል በዘር የተለየ ሲሆን ይህም ዘር ወያኔ ከምስረታው ጀምሮ ሊያጠፋው የተነሳው የዐማራ ዘር ነው።

በዚህም የተነሳ ደርግ ከ1967—1983 ዓ.ም. «ፊውዳል፣ ባላባት፣ በዝባዥ፣ አብዮት ቀልባሽ» በሚላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ሽብር አውጆ ካካሄደው ጅምላ ግድያ የከፋ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ፋሽስት ወያኔ ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት በዐማራ ላይ ፈጽሟል። በዘመነ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዐማራው ዲሞክራሲ አያስፈልገውምና እንዲጠፋ ስለተፈለገ በአገሩ አገርህ ሂድ ተብሎ ከተራራ ላይ ተወርውሯል፤ ቤት ተዘግቶበት በእሳት እንዲቃጠል ተደርጓል፤ ከነሰፍሱ በማይሞላ ገደል ውስጥ ተጨምሯል ዘሩን እንዳይተካ የዐማራ ሴቶች የሚያመክን መርፌ ተወግተዋል፤ የሕግ ጥበቃ፣ ስራ የማግኘትና የትምህርት እድል ተነፍጓል፤ የንብረት መብት፣ ያለመፈናቀልና የመኖር መብቱ በግላጭ በአገዛዙ ተቋማት ተገፏል።

ዐማራው በፋሽስት ወያኔ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ አያስፈልገውም ተብሎ እንዲጠፋ ስለተፈለገ ግብር ከፍሎ በሚያስተዳድረው በራሱ መገናኛ ብዙሀን ሳይቀር ሀያ ሰባት አመት ሙሉ በሕዝብ ተመረጥን በሚሉ፤ ኃላፊነት ሊሰማቸው በሚገባ የፖለቲካ መሪዎች፤ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛና በዝባዥ በሚሉ የኮድ ስሞች እንደ አደገኛ ርዕዮተ ዓለም ሁሉም እንዲፋለሙት ተዘምቶበታል። ይህ ዘመቻ ዛሬም በትግራይ ቴሌቭዥን በተለያዩ ቋንቋዎች እየተካሄደ ነው። በያዝነው አመት አጋማሽ አካባቢ የትግራዩ ገዢ በትግርኛ ባደረገው ንግግር «ጎንደር ላይ የተፈጸመውና በትግሬዎች ላይ የተካሄደው ተግባር ምንጩ ትምክህተኝነት ነው። ይህንን ትምክህት ከስሩ ለመንቀል ያቺን ተንለሲስ እያመረተች የምትልክ ጉድጓድ መድፈን አለብን።» ሲል በይፋ በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት ያወጀው በዚሁ በትግራይ ቴሌቭዥን ነው። ዛሬ ዛሬ ድምጸ ወያኔና ትግራይ ቴሌቭዥን እንደ ሩዋንዳው ሬዲዮ ሚሌ ኮሊንስ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ዝቅተኛውን የጋዜጠኝነት መስፈርትን በማያሟላ መልኩ በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲካሄድ ቤንዚን እያርከፈከፈ ይገኛል።

በፋሽስት ወያኔ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አማራው እንዲጠፋ ስለተወሰነበት በአገሩ ውስጥ ለንብረቱም ሆነ ለሕይወቱ ጥበቃ በማጣቱ ወያኔ ባመነው እንኳ 2.40 ሚሊዮን ዐማራ እንዲጠፋ ተደርጓል። በፋሽስት ወያኔ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዐማራው አጥፊ ተደርጎ የውሸት ታሪክ ተፈጥሮበት እንዲጠፋ በመደረጉ በርዕዮተ አለም የታገዘ፣ ስልታዊ [systematic] የሆነ፤ በተለያዩ ነገሮች ወደፊት እንዳይሄድ እልቆ መሳፍርት በደልና ግፍ ተፈጽሞበታል። ተቃለለ ካልተባለ በስተቀር ባለፉት ሀያ ሰባት የፋሽስት ወያኔ የጭካኔ የአገዛዝ አመታው በሕይወት ያለው ያልጠፋው አማራ ሲኖር የነበረው ወያኔ ባበጀለት የቁም መቃብር ውስጥ ነው።

መለስ ዜናዊ የዐማራ ማጥፊያ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም መሰረት የሆነውን አብዮታዊ ዲሞክራሲን ሲተቹበት፤ ለሁሉም እኩል የንብረት መብት የሚሰጠውን፤ በየትም ቦታ የመወከልና የመወከል መብትን የሚያጎናጽፈውን፤ የመምረጥና የመመረጥ፣ ድምጽን የማሰማት፣ ባጠቃላይ ሁሉንም መብቶች ለሁሉም በእኩል መጠን የሚሰጠውን ሊብራሊዝምን ስድብ አድርግት አስተሳሰቡን የሚከተሉትንና የሚጠላቸውን ሰዎች «ኒዮ ሊብራል ኃይሎች» እያለ ያንጓጥጥና ያሸማቅቅ ነበር። ከሰሞኑም በመለስ ዜናዊ ወንበር የተቀመጠው አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር በዐማራ ላይ ስለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ጥያቄ ቀርቦለት ወያኔና ርዕዮተ ዓለም አጋሮቹ የፈጸሙትን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመካድ ከመለስ ዜናዊ ያልተናነሰ መልስ ሰጥቷል። በርግጥ በዐማራ ላይ የተካሄደውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚክዱና ለመቀበል የሚቸገሩ ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ሲጽፉና ሲናገሩ እንመለከታለን።

እስቲ የዘር ማጥፋት ወይንም Genocideን አለማቀፋዊና አሕጉራዊ ፍቺውን ትተን ዐቢይ አሕመድ ራሱ ለማስከበር በቃለ መሐላ የተቀበለው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ውስጥ በምን አኳኋን እንደተቀመጠ እንመልከት። የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 ስለ ዘር ማጥፋት ወንጀሎች ምንነት የተብራሩ ዝርዝሮችን አካቷል። አንቀጹን እንደሚከተለው እናቀርባለን፤

አንቀጽ 269፡ የዘር ማጥፋት፤
ማንም ሰው በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጎሳ፣ በዘር፣ በዜግነት፣ በቀለም፣ በኃይማኖት ወይንም በፖለቲካ አንድ የሆነን ቡድን በመላ ወይንም በከፊል ለማጥፋት ማሰብ፣ የጥፋቱን ድርጊት ማደራጀት፣ ትዕዛዝ መስጠት ወይንም ድርጊቱን የመፈጸመ እንደሆነ፤ ወይንም
ሀ) በማንኛውም ሁኔታ የማህበረሰቡን አባሎች የገደለ፣ አካላዊ ወይንም የአካል ጉዳት ያደረሰ ወይንም ያጠፋ እንደሆነ፤ ወይንም
ለ) የማህበረሰቡ አባላት በዘር እንዳይራቡ ወይንም በሕይወት እንዳይኖሩ ለማድረግ ማንኛውንም ዘዴ በስራ ላይ ያዋለ እንደሆነ፤
ሐ) የማህበረሰቡን አባላት ወይንም ህጻናት በግዴታ ከስፍራ ወደ ስፍራ ያዛወረ ወይንም የበተነ ወይንም ሊሞቱ ወይንም ሊጠፉ በሚችሉበት የኑሮ ሁኔታ እንዲኖሩ ያደረገ እደሆነ የዘር ማጥፋት ፈጸመ ይባላል።

ከዚህ በተጨማሪ የተሻሻለው የወያኔ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 269 የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት ሶስት ነገሮች መሟላት እንዳለባቸው በማያሻማ ሁኔታ በግልጽ አስቀምጦታል። እነርሱም:-
1) መግደል፣ በሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስ ወይም ደግሞ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ጉዳት ማድረስ ወይም ደግሞ በቡድን አባላት ላይ የስነ ልቦና ጉዳት ማድረስ፣ በማንኛውም መንገድ ወይም ደግሞ ምንም ይሁን ምን ሰውሮ ማጥፋት፣

2) በአባላት ወይም ደግሞ በልጆቻቸው ላይ ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ መኖር እንዳይችሉ ተከታታነት ያለው ቅስቀሳ ማድረግ እና ይህንን መከላከል ያለመቻል፣ ወይም ደግሞ፣

3) በግዴታ ማፈናቀል ወይም ደግሞ ሰዎችን ወይም ልጆቻቸውን ከቦታዎቻቸው ለሞት በሚያበቃ መልኩ ተገቢ ያልሆኑ ተግባራትን መፈጸም ወይም መሰወር፣ ወይም ደግሞ ሆን ተብሎ በጅምላ ወይም በከፊል ብሄርን፣ ብሄረሰብን፣ ጎሳን፣ ዘርን፣ ዜግነትን፣ ቀለምን፣ ኃማኖትን ወይም ደግሞ የፖለቲካ ቡድንን ማጥፋት።

ፋሽስት ወያኔ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የተቀመጠውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ዝርዝሮችም ሆነ የሚፈጸምን አንድ ወንጀል «የዘር ማጥፋት ወንጀል» ለማለት መሟላት አለባቸውን የሚላቸውን ሶስት ነገሮች ሁሉ ከምስረታው ከ1967 ዓ.ም. እስከ ዛሬ ድረስ ፈጽሟቸዋል፤ እየፈጸማቸውም ይገኛል። ወያኔ በ1968 ዓ.ም. በፕሮግራም ደረጃ የያዘውን አማራ የማጥፋት ፕሮጀክት ወደ ታች ለማውረድ በዘፈኖቻቸው «ገረብ ገረብ ትግራይ፣ መቓብር ኣምሐራይ፤» ብለው ዘፈውነዋል። ይህ በአማርኛ «ገረብ ገረብ ትግራይ፣ መቓብር ኣምሐራይ፤» በማለት የትግራይ ተራሮች የአማራ መቃብር ይሆናሉ ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ትግል ማለት ምን ማለት ሲገልጹ «ገድሊ ማለት አምሓራይ ምቅታል ማለት እዩ’» ብለውም ነበር። ይህ ወደ አማርኛ ሲመለስ፤«ትግል ማለት አማራን መግደል ነው» ማለት ነው።

በነዚህና መሰል ተቋማዊ ያደረጓቸው የርዕዮተ ዓለም ጡንቻዎቻቸው እየተመሩ አማራ እንዳይራባ የሚያመክን መርፌ ወግተውታል፤ በአገሩ ተረጋግቶ እንዳይኖር በአገሩ አገርህ ሂድ ብለው አሳደውታል፤ በግፍ ረሽነውታል፤ የወንድ አማሮችን የዘር ፍሬ አኮላሽተዋል፤ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ አማራ በአስራ አምስት አመት ውስጥ አጥፍተዋል፤ በአንጡራ ሀብቱ የፈጠረው ሀብቱ ተነቅሎ ወደ ትግራይ በመወሰዱና ሊሞት ወይንም ሊጠፉ የሚችልበት የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖር በመገደዱ ወያኔ «አማራ ክልል» ብሎ የፈጠረው «ቀጠና» በአለም ላይ የመጨረሻ ድሀ «ክልል» እንዲሆን አድርገውታል።

ከዚህ በላይ የዘር ማጥፋት ምንድን ነው? በወያኔዋ ኢትዮጵያ በፕሮግራም ደረጃ ታቅዶ፣ ተቋማዊ በሆነ መልኩ የዘር ማጥፋት ዘመቻ የተካሄደበት ነገድ ከአማራ ውጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛልን? ሌላው ቢቀር በኦፊሴል የቀረበውና ጠፋ የተባለው 2.4 ሚሊዮን አማራ ሰው አይደለም እንዴ? ይህን ያህል ቁጥር የጠፋ ሕዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ? ለምድን ነው በዐማራ ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ለመካድ ሲባል በእገሌ ነገዳ ላይምኮ እንዲህ ሆኗል፤ እንዲያ ሆኗል የሚባለው? በዚህ ወይንም በዚያ ነገድ ላይ የዘር ማጥፋት መፈጸሙ በአማራ ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ሊያቃልለውስ ይችላልን??

አንዳንድ ሰዎች የወያኔው የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ 2.40 ሚሊዮን አማራ ጠፋ ያለውን ማስረጃ አንቀበልም ይሉና በአማራ ላይ ተፈጸመ የምንለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ላለመቀበል ሊሟገቱ ይሞክራሉ። አላስተዋሉትም እንጂ የአማራ ቁጥር በ2.40 ሚሊዮን ጎድሏል የሚለውን «ኦፊሲያላዊ» መረጃ በራሱ «የሞተ ሰው ቁጥር» አይደለም ብለን እንኳ ብንወስድ የአማራ ቁጥር በ2.40 ሚሊዮን ያህል እንዲቀንስ መደረጉ በአማራው ላይ የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሆነ ማየት ይችሉ ነበር። የአማራ ቁጥር በ2.40 ሚሊዮን ጎደለ ማለት ለአስር አመት [ድጋሚ የቤትና የህዝብ ቆጠራ እስኪካሄድ ድረስ፤ ያውም ድጋሜ ቆጠራ ሲካሄድ ጠፋ የተባለው 2.40 ሚሊዮን የሚካተት ከሆነ ነው] ያህል 2.40 ሚሊዮን የሚሆን አማራ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የመሰረተ ልማቶች ዝርጋታ፤ለገጠርና ከተማ ልማት እንዲሁም ለዴሞክራሲና ሰላም ግንባታ የሚውል አመታዊ ባጀት ለአስር አመታት ያህል አልተመደበለትም ማለት ነው። ይህ ማለት 2.40 ሚሊዮን አማራ ለአስር አመት መሰረታዊ የሆኑ ፍላጎቶች ሳይሟሉለት እንዲኖር ተደርጓል ማለት ነው።

መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ያልተሟሉለት ህዝብ ደግሞ በድህነት፣ በርሀብና በችጋር ተጎሳቁሎ ይጠፋል። ስልታዊ በሆነ መልኩ 2.40 ሚሊዮን አማራ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ሳይሟሉለት ቀርተው በድህነት፣ በርሀብና በችጋር ተጎሳቁሎ ሊሞት ወይንም ሊጠፉ የሚችልበትን የኑሮ ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ ደግሞ ከፍ ብሎ በቀረበው የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ አንቀጽ 289 መሰረት የዘር ማጥፋት ነው። ስለዚህ 2.40 ሚሊዮን አማራ ጠፋ የሚለውን ኦፊሴላዊ ማስረጃ መቀበል የሚቸግራቸው ሰዎች በቆጠራ ወቅት 2.40 ሚሊዮን አማራ እንዲጎድል መሆኑና ላለፉት አስር አመታት 2.40 ሚሊዮን አማራ ስልታዊ በመሆነ መልኩ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የመሰረተ ልማቶች ዝርጋታ፤የገጠርና ከተማ ልማት እንዲሁም የዴሞክራሲና ሰላም ግንባታ ተጠቃሚ እንዳይሆን መደረጉ በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት እና የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀሎች መፈጸማቸው ማረጋገጫ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የዘር ማጥፋት የዘር ማጽዳት ወንጀልን ይጀምራል። ላለፉት ሀያ አምስት አመታት ወያኔ «ከአማራ የጸዳ አካባቢ መፍጠር» የሚለውን ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም ሲል አማራ በመሆናቸው ብቻ ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እንዲፈናቀሉና ሜዳ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል። ይህ የግፍ ተግባር ዛሬም ቀጥሎ ንብረታቸው የተዘረፈ፤ ደማቸው የፈሰሰ የአማራ አርሶአደሮችን ቁጥር በሚሊዮኖች የሚቆጠር አድርጎታል። ባጠቃላይ ላለፉት ሀያ አምስት አመታት በአማራ ላይ የተፈጸመው ግድና፣ ሰቆቃ፣ መከራ፣ የዘር ማጥፋትና ተያያዥ በደሎች ምድሪቷ ከምትሸከመው በላይ ሆኗል።

ዐቢይ አሕመድ በዐማራ ልይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲክድ ፋሽስት ወያኔ በደርግ ላይ የመሰረተውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የዘነጋው ይመስላል። እንደሚታወቀው ፋሽስት ወያኔ የደርግን አገዛዝ በዘር ማጥፋት የከሰሰው «የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ» በሚል ስም ደርግ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ባስነረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በአዋጁ ስም መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና የወንጀል ግብረ አበሮቹ በፈጸሙት ግፍና ግድያ ነበር። ደርግ የ108 አካባቢ የበታች መኮንኖች ስብስብ ነው። መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ጊዜያዊ ወታደራዊ «መንግሥት» የሆነው ደርግ 108 የደርግና አባላትን ይዞ በደርግ ስም በመሰየም ነው።

መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገውም «የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አዋጅ» ብሎ የ108ቱን የደርግ አባላት አዋጅ አድርጎ ነው። ይህንን ያወቀው ፋሽስት ወያኔም በደርግ ላይ ክስ ሲመሰርት በመንግሥቱ ኃይለ መርያም ወንጀል ተጠያቂ ያደረገው መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ብቻ ሳይሆን ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ብለው «መንግሥት» የሆኑትን 120ውን የደርግ አባላት ሁሉ በእኩል ወንጀል ነው።

108ቱ የደርግ አባላትም የተከሰሱት ደርግ በመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. «የኢትዮጵያ ትቅደምን ዓላማን በመቃወም፣ የሥራ ማቆም አድማ፣ የተቃውሞ ሰልፍ የሚያደርግ… ጥብቅ እርምጃ ይወሰድበታል!» በሚል ባወጁት አዋጅና አዋጁን ተከትሎ በተቃወሟቸው ላይ በወሰዱት እርምጃ ነው።

የዘር ማጥፋት የሚባል ወንጀል ባለም ላይ ከሌለ በስተቀር መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና የወንጀል አጋሮቹ መስከረም 2፣ 1967 ዓ.ም. ባወጁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አዋጁን ተከትሎ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በቡድኖችና በእስር ላይ ባሉ ሰዎች ላይ የተፈጸሙት ግፍና ግድያ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 መሰረት የዘር ማጥፋት ተደርጎ ቀርቦና በፍርድ ቤትም ወንጀለኛ ሆነው የተገኙት እነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ለፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል የሞት ቅጣት እንዲፈጸምባቸው ተወስኖባቸው ሳለ ወያኔዎች ከጅምሩ ጀምሮ ዐማራን ማጥፋትን እንደ ትግል አላማቸው በመውሰድ መጀመሪያ በፕሮግራማቸው፤ ቆይተው ደግሞ ወደ ርዕዮተ ዓለም ደረጃ አሳድገው ዐማራውን ሲገድሉ፣ ሲያፈናቅሉ፣ በእስር የሚገኘውን በዘሩ እየጠሩ ብልቱ ላይ ውሃ የሞላ ጠርሙስ እያንጠለጠሉ ሲያኮላሹትና ምድሪቷ ከምትችለው በላይ ስቃይ የፈጸሙበት ግፍና በደል የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊሆን የማይችልበት ምክንያት የለም።

በደርግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ የሆነው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ብቻ ሳይሆን 108ቱም የደርግ አባላት ሁሉ ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም እኩል የመስከረም 2ቱን አዋጅ ተከትሎ በተካሄደውና በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 መሰረት የዘር ማጥፋት ተደርጎ በቀረበው ግፍና ግድያ ተጠያቂ ሆነዋል። ዐቢይ አሕመድም ላለፉት ሀያ ሰባት አመታት የኢሕአዴግ አባልና አመራር እንደመሆኑ መጠን በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 መሰረት የዘር ማጥፋት ተደርጎ የቀረበውንና ላለፉት 27 ዓመታት በዐማራ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊመለከተኝ ይችላል በሚል ስጋት ከሆነ በዐማራ ላይ በፋሽስት ወያኔ የአገዛዝ ዓመታት የተፈጸመውን ወንጀል እየካደ ያለው ዐማራን ለማጥፋት ፕሮግራም ቀርጸው ያፈጸሙና በዐማራ ዘር ማጥፋት ክብረ ወሰን የተቀዳጁ የሕወሓት ነውረኞች ይርጋ ከሌለው ወንጀል ነጻ እንዲሆኑ እየተከላከለ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል።

ባጭሩ ወያኔ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 መሰረት በደርግ ባለስልጣናት ላይ ያቀረበው የዘር ማጥፋት ወንጀልና በሞትና በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ያደረገው ስህተት ነው ካልተባለ በስተቀር ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ሙሉ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 መሰረት የዘር ማጥፋት ተደርጎ የቀረበውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሁሉ በዐማራ ላይ የፈጸመው ፋሽስት ወያኔ የዘር ማጥፋት ያልፈጸመና ሕግ ያልጣሰ ሥርዓት ተደርጎ ሊቀርብ አይችልም። ዐቢይ አሕመድ በዐማራ ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ሲክድ ደርግ በፍድር ቤት የተፈረደበትን የዘር ማጥፋት ወንጀል መካዱ መሆኑ የተገለጠለት አይመስልም።

እንግዲህ! ዐቢይ አሕመድ ለማስከበር በቃለ መሐላ የተቀበለው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ስለ ዘር ማጥፋት እንዲህ ካለን፤ ዐብይ በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት አልተካሄደም የሚለን ለማስከበር በቃለ መሐላ የተቀበለው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ እየጣሰ ነው ማለት ነው። ለምን ቢባል በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የተቀመጠውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ዝርዝሮችም ሆነ የሚፈጸምን አንድ ወንጀል «የዘር ማጥፋት ወንጀል» ለማለት መሟላት አለባቸውን የሚላቸውን ሶስት ነገሮች ሁሉ ወያኔ ከምስረታው ከ1967 ዓ.ም. እስከ ዛሬ ድረስ በአማራ ላይ ፈጽሟቸዋል፤ እየፈጸማቸውም ይገኛልና።