ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብ ላይ የነበራትን 19 ፐርሰንት ድርሻዋን ማጣቷ ተዘግቧል… ቀጣዩ ምን ይሆን?

ኤሊያስ መሰረት ፡ የአሁኑ የሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የዛሬ ስድስት አመት ገደማ ስልጣን ከመያዛቸው ወራት በፊት ሀርጌሳ ውስጥ የማግኘት እድል አግኝቼ ነበር። በወቅቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሲገልፁ “ታላቅ ወንድማችን” እና “የሰላማችን ጠባቂ” በማለት ይገልፁት ነበር። ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስሩ ብዙ ፕሮጀክቶችን እንደሚያልሙ እና እውን እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ነበሩ።

ፕሬዝደንቱ ይህንን ባሉ በሁለት አመት ውስጥ ከፍተኛ የስትራቴጂ እና የንግድ ጥቅም ያለው በርበራ ወደብ ላይ ኢትዮጵያ የ19 ፐርሰንት ድርሻ እንዲኖራት ስምምነት ላይ ተደረሰ። እንደማስታውሰው በወቅቱ ሌላኛው ባለድርሻ የሆነው የኤምሬትሱ DP World ደስተኛ ባይሆንም የሱማሌላንድ መንግስት በወደብ አስተዳደር ባለስልጣኑ በኩል ባደረገው ጫና ኢትዮጵያ ድርሻ እንዲኖራት ተደርጎ ነበር፣ ለዚህ ደግሞ ለወደቡ ልማት የሚውል ወጪ ላይ ኢትዮጵያ ገንዘብ እንድታዋጣ ይጠባቅባት ነበር።

ይሁንና የሶማሌላንድ መንግስት በበርበራ ወደብ ላይ የባለቤትነት መብትን አስመልክቶ ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ኢትዮጵያ ማሟላት ባለመቻሏ በወደቡ ላይ የነበራትን የ19 በመቶ ድርሻዋን ማጣቷን ካፒታል እና ሪፖርተር ዘግበዋል። ከቅድመ-ሁኔታዎቹ አንዱ ከላይ የጠቀስኩት ለወደቡ ግንባታ የገንዘብ መዋጮ ሲሆን ኢትዮጵያ ይህን ማድረግ ሳትችል ቀርታለች ተብሏል።

ይህ በራሱ ትልቅ ችግር ነው።

የጅቡቲ ኮሪዶር ከአመት አመት እየተወደደ ይገኛል፣ የሱዳን ፖርትን እንዳንጠቀም ያለው ፍጥጫ አላስቻለም፣ የኤርትራ ወደቦች እንደታሰበው አገልግሎት ሊሰጡ አልቻለም። በአጠቃላይ የበርበራ ወደብን ድርሻ ማጣታችን ትልቅ ክስረት ነው፣ እንደራሳችን ቆጥረን በጥሩ ሁኔታ ልንጠቀምበት የምንችለውን እድል አጥተናል። ምናልባት መንግስት ይህን ጉዳይ ቀደም ብሎ ለህዝብ ይፋ አድርጎ ቢሆንና ገንዘብ እንኳን ባይኖረው ሁሉም ዜጋ ተሳትፎ የወደቡ ድርሻችን እንዳይቀር ማድረግ ሊሞከር ይችል ነበር።

የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ አሁንም ሶማሌላንድ ላይም ሆነ ሶማልያ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አላት፣ ከአዲሱ የሶማልያ ፕሬዝደንት መምጣት ጋር ተያይዞ አዳዲስ እድሎችን ማማተር ያስፈልጋል።

እንዴት?

ኢትዮጵያ ከሶማልያዋ ጁባላንድ ግዛት ውጪ ባሉ የፌደራል አስተዳደሮች ከፍ ያለ ተፅእኖ አላት፣ ተሰሚነትንም ይዛ ቆይታለች፣ ሶማሌላንድ ላይም እንደዛው (ጁባላንድ ላይ የአዋሳኟ የኬንያ ተፅእኖ ከፍ ያለ ነው)። ስለዚህ በጥሩ ዲፕሎማሲ ከአዲሱ ፕሬዝደንት ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ሰላም ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም ሊያስጠብቅ ይችላል።

አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ጠ/ሚር አብይ አህመድ ከቀድሞው የሶማልያ ፕሬዝደንት መሐመድ ፋርማጆ ጋር የመሰረቱት ጥብቅ ግንኙነት ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ተሰሚነት እንዲኖራት አድርጓል፣ በዛ ላይ በጌዴ እና ኪስማዮ አካባቢዎች ጠንከር ያለ ወታደራዊ አሰላለፍ አሁን ድረስ አላት። ሲቀጥል የኢትዮጵያ መንግስት የፋርማጆ ድጋፍ አለው፣ ፋርማጆ ደግሞ አሁን ድረስ በሶማልያ ፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አካል መሪ ናቸው።

እነዚህን ነጥቦች ያነሳሁት አዲሱ የሶማልያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሙሐሙድ ወደ ኬንያ እያማተሩ እንደሆነ ምልክቶች እየታዩ ስለሆነ ነው። እንደ በርበራ ወደብ ሶማልያንም እንዳናጣት ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦችን ተጠቅሞ ከፍ ያለ ስራ መስራት ይጠይቃል። ኤሊያስ መሰረት