የኢትዮጵያ ብር ዋጋ በተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት ብቻ ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ዋጋው በ15 በመቶ አሽቆለቆለ

የኢትዮጵያ ብር ዋጋ በተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት ብቻ ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ዋጋው በ15 በመቶ ማሽቆልቆሉን ብሉምበርግ ዘገበ። ብር ባሁኑ ወቅት ከአርጀንቲናው ፔሶ እና ከቱርኩ ሊሬ ቀጥሎ በዓለም ደካማው መገበያያ ገንዘብ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል። የብር ዋጋ ወደፊትም ኢትዮጵያ የውጭ እዳዋን ማሸጋሸግ ከመቻሏ ጋር የተሳሰረ ሆኖ እንደሚቀጥል ዘገባው አመልክቷል። መንግሥት የአገሪቱን 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር መልሶ ለማዋቀር ከወራት በፊት ከአበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ላይ መድርሱ ይታወሳል። ኾኖም የአገሪቱ የወጪ ገቢ ማደግ፣ የመንግሥት የበጀት ክፍተት መቀነስ እንዲሁም መንግሥት ከ1 ቢሊዮን ዶላር የዩሮቦንድ ያዥ ዓለማቀፍ ኢንቨስተሮች ጋር በቦንዱ አከፋፈል ላይ ስምምነት ሊደርስ ይችላል የሚለው ተስፋ፣ በብር ላይ ያለውን ጫና ሊያቃልለው እንደሚችል ባለሙያዎች እምነታቸውን ገልጸዋል ተብሏል። ባኹኑ ወቅት መደበኛው የ1 ዶላር መግዣ ዋጋ 151 ብር ሲሆን፣ በትይዩ ገበያ ደሞ ወደ 180 ብር አሻቅቧል።