አዲሱ የንብረት ታክስ ረቂቅ ሕግ ከግብር ነጻ የሚሆን ቤተሰብን እንዴት ይለያል?

የገንዘብ ሚኒስቴር የንብረት ታክስ የሚጣልበትን እና የሚሰበሰብበትን መንገድ በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘ “ሞዴል” ረቂቅ ሕግ በታኅሣሥ 2018 ዓ.ም. መጀመሪያ ወደ ክልል እና ከተማ አስተዳደሮች ልኳል።

የንብረት ታክስን የመጣል እና የመሰብሰብ መብት የክልሎች ቢሆንም ከግብሩ ጋር ለሚያወጡት ሕግ “መነሻ የሚሆን ሞዴል” ረቂቅ ሕግ የሚዘጋጀው በፌደራል መንግሥት እንደሆነ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደብዳቤ ያስረዳል።

ገንዘብ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ባለ 60 ገጽ ሞዴል ሕግ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ባወጣው የንብረት ታክስ አዋጅ ላይ ለተቀመጡ ነጥቦች ዝርዝር ድንጋጌዎችን ያስቀመጠ ነው።

ገንዘብ ሚኒስቴር ለክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በጻፈው ደብዳቤ “ሞዴል ሕጉን እንደ ክልላዊ አዋጅ” እንዲያወጡት ጠይቋል።

“ክልላዊ ልዩ ሁኔታን የማካተት ጉዳይ ሙሉ በሙሉ የሚከበር እና የሚበረታታ” እንደሆነ የጠቀሰው ሚኒስቴሩ፤ ቢሆንም ግን “ለአገራዊ ወጥነት እና ለሥርዓቱ ጥንካሬ ሲባል” የሚያደርጓቸው ማሻሻያዎች ከሞዴሉ ጋር የሚጣጣሙ እንዲሆኑ አሳስቧል።

ጨምሮም “በሞዴል አዋጁ ስር ከተቀመጡት የታክስ መሠረቶች፣ ምጣኔዎች፣ የነጻ መብቶች እና ከሌሎች መሠረታዊ መመዘኛዎች ጋር የሚጣጣሙ ሆነው እንዲቀጥሉ [እናሳስባለን]” ሲል በደብዳቤው ላይ አስፍሯል።

የንብረት ታክስ የሚጣለው ምን ዓይነት ንብረቶች ላይ ነው?

ሞዴል ሕጉ እንደሚስረዳው፤ የንብረት ታክስ በክልሎቹ ውስጥ በሚገኙ “ከተሞች ውስጥ በሚገኙ” ንብረቶች ላይ ይጣላል። በከተማዎች የሚገኙ የመኖሪያ፣ የኢንዱስትሪ፣ የቢዝነስ እና ንግድ እንዲሁም የቅይጥ ወይም ባለብዙ ዘርፍ ቦታዎች እና ሕንጻዎች ታክሱ እንደሚጣልባቸው ከተዘረዘሩት መካከል ናቸው።

እነዚህ ቦታዎች በሊዝ ወይም “ከሊዝ ይዞታ ስሪት ውጪ በሆነ ነባር” መንገድ የተያዙ ሊሆኑ እንደሚችሉም በሞዴሉ ላይ ተቀምጧል

ከዚህም ባሻገር የይዞታ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው ቦታዎችን የያዙ ሰዎችን የንብረት ታክስ የመክፈል ግዴታ ተጥሎባቸዋል። ሞዴል ሕጉ እነዚህ አካላት የሚገልጻቸው “የተመዘገበ የባለቤትነት መብት በሌለበት ጊዜ ማንኛውም ታክስ የሚከፈልበትን ንብረት ይዞ የሚገኝ ሰው ወይም በይዞታው ጥቅም እያገኘ ያለ ሰው” በሚል ነው።

የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው ሰዎች የንብረት ታክስ መክፈላቸው “ብቻውን በንብረቱ የመጠቀም ወይም የባለቤትነት መብት” እንደማያስገኝላቸው ተቀምጧል። “በሌሎች ሕጎች መሠረት የሚወሰዱ እርምጃዎችን እንደማያስቀርም” አስፍሯል።

በረቂቁ መሠረት የንብረት ታክስ የሚከፈለው ጥቅም እየሰጠ ባለ ንብረት ላይ ብቻ አይደለም። ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎች እና ሕንጻዎችም ታክሱ ከሚከፈልባቸው የንብረት ዓይነቶች ውስጥ ተካትተዋል።

ሕጉ “ጥቅም ላይ ያልዋለ ቦታ” በማለት የሚገልጸው “ማንኛውም ሕንጻ ወይም ቋሚ ማሻሻያ ያልተሠራበት” እንዲሁም በተወሰነለት ጊዜ ውስጥ “በሕጋዊ መንገድ ጥቅም ላይ ያልዋለ” የከተማ ቦታን ነው።

በተሰጠው “የግብር ዘመን ውስጥ” አገልግሎት መስጠት ያልጀመረ ሕንጻ ደግሞ “ጥቅም ላይ ያልዋለ ሕንጻ” የሚባለው ምድብ ውስጥ ይገባል።

ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ጥቅም ላይ ባልዋሉ ቦታዎች እና ሕንጻዎች ላይ “ከፍተኛውን” የንብረት ታክስ ተመን መጣል እንዳለባቸው ሞዴል ሕጉ አስፍሯል።

ይሁን እንጂ ሁሉም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎች እና ሕንጻዎች የንብረት ታክስ እንደማይጣልባቸው ረቂቁ ያስረዳል።

ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሕንጻዎች እና ቦታዎችን ከግብሩ ነጻ የሚያደርጉ “ተቀባይነት ያላቸው ምክንያቶችን” የሚዘረዝር መመሪያ በየከተሞቹ ይወጣል።

ገንዘብ የሚቆጥር እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከንብረት ታክስ ነጻ የመሆን መብት ለማን ይሰጣል?

የገንዘብ ሚኒስቴር ሞዴል ሕግ “ዝቅተኛ ገቢ ላለው አንድ ቤተሰብ በመኖሪያነት የሚያገለግል የከተማ ቦታ፣ ሕንጻ እና የቦታ ማሻሻያ” የንብረት ታክስ እንዳይከፈልበት የሚያደርግ ድንጋጌ ይዟል። ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ ከግብር ነጻ የሚሆኑ አካላትን ለመወሰን የሚውሉ ሁለት ዓይነት መስፈርቶች ተቀምጠዋል።

አንደኛው መስፈርት “ዝቅተኛ ገቢ ያለው” የሚባለው ቤተሰብ የቱ እንደሆነ ለመሰን የሚውል ነው። በሞዴል ሕጉ መሠረት “ዝቅተኛ ገቢ ያለው ቤተሰብ” የሚባለው “ከባድ የተረጋገጠ የኢኮኖሚ ችግር ያለበት” ሲሆን ነው።

በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገባ ቤተሰብ “ዓመታዊ ገቢው ከአገራዊው አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ50 በመቶ የማይበልጥ” መሆን አለበት።

የዓለም ባንክ የ2024 መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ዓመታዊው የነፍስ ወከፍ ገቢ 1,020 የአሜሪካ ዶላር ወይም በወቅታዊው የንግድ ባንክ የምንዛሬ ዋጋ 154,640 ብር ገደማ ነው።

አንድ ቤተሰብ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ምድብ ውስጥ የሚገባው “በከተማው የማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ” ሲረጋገጥ ነው። ይህ መረጋገጡ ብቻውን ግን ቤተሰቦችን ከግብር ነጻ አያደርጋቸውም። በባለቤትነት የያዙት ንብረት ዋጋም ከግምት ውስጥ ይገባል።

በሞዴል ሕጉ መሠረት የዝቅተኛ ገቢ ያለው ቤተሰብ የያዘው ንብረት እንደ አዲስ አበባ ባሉ የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ዋጋው “ከአንድ ሚሊዮን ብር” መብለጥ የለበትም።

አዲስ አበባ አውቶብስ መጠበቂያ ላይ የተቀመጡ እና የቆሙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa Transport Bureau

“ማዘጋጃ ቤት” በሚል ምድብ ውስጥ በሚካተቱ ከተሞች ውስጥ የሚገኝ ንብረት ከሆነ ደግሞ ዋጋው ከ250,000 ብር በታች መሆን አለበት።

“ታዳጊ ከተሞች” ውስጥ የሚገኝ ንብረት የያዙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ከግብሩ ነጻ የሚሆኑት የንብረቱ ዋጋ “ከ100,000 ብር ያነሰ” ሲሆን ነው።

የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ ሕግ ከንብረት ታክስ ነጻ ካደረጋቸው ሌሎች ቦታዎች እና ሕንጻዎች መካከል የሃይማኖት ተቋማት የአምልኮ እና የመካነ መቃብር ስፍራዎች ይገኙበታል።

“በከተማ ክልል ውስጥ ያሉ ለአንድ ቤተሰብ ፍጆታ ለግብርና ሥራ የሚለውሉ” ንብረቶችን ከታክሱ ነጻ ተደርገዋል። “ለሕብረተሰቡ ነጻ የማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ለዚሁ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው ንብረቶችም” ታክሱን እንዲከፍሉ አይደረጉም።

ቅርሶች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ፓርኮች፣ የጋራ ክፍት ቦታዎች እንዲሁም ዋና እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችም ከንብረት ታክስ ውጪ ከተደረጉ ይዞታዎች መካከል ተካትተዋል።

ከዚህ ባሻገር የተፈጥሮ አደጋ፣ የትጥቅ ግጭት፣ የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ በሚፈጠርበት ወቅት ባለ ንብረቶች “ታክስ የመክፈል ግዴታቸውን የሚወጡበት ጊዜ እንዲዘገይ ሊፈቀድ ይችላል።”

የአዲስ አበባ ከተማ ሕንጻዎች ከሰማይ ላይ የተነሳ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister

የምስሉ መግለጫ, የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ የንብረት ታክስን በአዲስ መልኩ መሰብሰብ ጀምሯል

የንብረት ታክስ ክፍያ መጠን እንዴት ይሰላል?

በሕጉ ላይ የንብረት ታክስ ምጣኔን የመወሰን እና የማሻሻል ሥልጣን የተሰጠው ለከተማ አስተዳደሮች ነው። ይሁን እንጂ ከዝርዝር የታክስ ምጣኔ ውጪ ያሉ ተያያዥ መሠረታዊ የስሌት ድንጋጌዎች አስቀድሞ በአዋጁ ተወስነዋል።

አንድ ንብረት ታክስ የሚከፈለው ገበያ ውስጥ ያለውን ዋጋ መነሻ በማድረግ ነው። ንብረቱ ገበያው ውስጥ ያለው ሙሉ ዋጋ የታክስ ስሌት ውስጥ ይገባል ማለት ግን አይደለም። ታክስ የሚሰለው ከንብረቱ ዋጋ 25 በመቶ ላይ ብቻ ነው።

ለምሳሌ አንድ ሕንጻ ዋጋው 4 ሚሊዮን ብር ከሆነ ታክሱ የሚታሰበው አንድ ሚሊዮን ብሩ ላይ ይሆናል። አንድ ሚሊዮን ብሩ ላይ የሚጣለው ታክስ ደግሞ ከአንድ በመቶ እንደማይበልጥ ባለፈው ዓመት በወጣው የፌደራል መንግሥት አዋጅ ላይ ተደንግጓል።

የከተሞች ይህንን ሕግ ወጥቶ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ በቀጥታ ከፍተኛ የሆነውን አንድ በመቶ ታክስ ማስከፈል አይችሉም። ከፍተኛ የሆነው ምጣኔ ላይ የሚደርሱት በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ሞዴል ሕጉ ያስረዳል።

ሞዴል አዋጁ ታዳጊ ከተሞች፣ የማዘጋጃ ቤት ከተሞች እና የከተማ አስተዳደሮች በአራቱ ዓመታት ውስጥ ማስከፈል የሚችሉትን ዝቅተኛ እና ከፍተኛ የታክስ ተመንን አስቀምጧል።

“ለከተማ ቦታ” እና “ለሕንጻ እና/ወይም የቦታ ማሻሻያ” ንብረቶች የተቀመጠው የተለያየ የታክስ ምጣኔም ተደንግጓል።

የሁሉም የከተማ ዓይነቶች የመጀመሪያው ዓመት ላይ “ከሕንጻ እና/ወይም የቦታ ማሻሻያ” ባለቤቶች መጠየቅ የሚችሉት ዝቅተኛ ታክስ 0.10 በመቶ ነው። በዚሁ ዓመት ላይ ታዳጊ ከተሞች እስከ 0.25 በመቶ ማስከፈል የሚችሉ ሲሆን፣ የማዘጋጃ ቤት ከተሞች እስከ 0.35 በመቶ መጠየቅ ተፈቅዶላቸዋል።

የከተማ አስተዳደሮች የመጀመሪያው ዓመት ላይ መጠየቅ የሚችሉት ከፍተኛ የታክስ መጠን 0.50 ነው።

በዚህ መልኩ ለአራቱም ዓመታት የታክስ ምጣኔ ወሰን ያስቀመጠው ሞዴል ሕጉ፤ ሁሉም የከተማ ዓይነቶች አራተኛው ዓመት ላይ እስከ 1 በመቶ መጠየቅ እንዲችሉ ፈቅዷል።

ሞዴል ሕጉ ላይ የተቀመጠው ዝቅተኛ እና ከፍተኛ የታክስ ምጣኔ በመሆኑ እያንዳንዱ የከተማ አስተዳደር፤ ከተቀመጠው ማዕቀፍ ሳይወጣ የራሱን የግብር መጠን የመወሰን ሥልጣን አለው።