
የፎቶው ባለመብት, FB
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ዘገባ አንባቢዎችን ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው
ከአዲስ አበባ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ሰንዳፋ ውስጥ አዳነች ኩምሳ የተባለች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛን የገደለው ግለሰብ በፖሊስ እየተፈለገ እንደሆነ ተገለጸ።
የንግድ ባንክ አለልቱ ቅርንጫፍ ሠራተኛዋን ገድሎ፣ አስከሬኗን ጥሎ የተሰወረው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር እንዳልዋለ የሰንዳፋ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ንጋቱ ዓለሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ግድያው የተፈጸመው ሰኞ ታኅሣሥ 6/2018 ዓ. ም. መሆኑን ገልጸዋል።
“በሰንዳፋ በኬ ከተማ፣ ጎማጣ ወደተባለ ሥፍራ ተወስዳ ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ ነው ግድያው የተፈጸመው” ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገረው የሟች አዳነች አብሮ አደግ እና ቤተሰቧን የሚያውቅ አንድ ግለሰብ፤ ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም ወደምትሠራበት እየሄደ ሲያስፈራራት እንደነበር ተናግሯል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው የአዳነች አብሮ አደግ፤ ሟች ዛቻ እየደረሰባት እንደሆነ ለቤተሰቧ መግለጿንም አክሏል።
“በተገደለችበት ዕለት አዲስ አበባ፣ ሜክሲኮ አካባቢ የንግድ ባንክ ሥልጠና ላይ ውላ ወደ ሰንዳፋ ተመልሳለች” ብሏል።
የዚያኑ ዕለት ምሽት ላይ “ከአንድ ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ለሰዎች እየደወለች ነበር” ሲልም ተናግሯል።
አዳነች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አለልቱ ቅርንጫፍ ለሦስት ዓመታት የሠራች ሲሆን፤ ለዓመታት በትውልድ ቀዬዋ ምዕራብ ወለጋ አካባቢ በመንግሥት ሥራ ላይ እንደቆየች አብሮ አደጓ ተናግሯል።
“የተገኘው የአስከሬኗ ክፍል ብዙ አይደለም። የተገኘው ብቻ በፌስታል ተጠቅልሎ ተቀብራለች። የሬሳ ሳጥኑ ክብደት እንዲኖረው ግማሽ ያህሉን በአሸዋ ሞልተነው ነው የተቀበረችው” ብሏል።
ቢቢሲ ያነጋገረው የአዳነች አብሮ አደግ “ግለሰቡ የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደሆነ እና ቤተሰብ ያለው” እንደሆነ ጠቅሶ እሷ የምትሠራበት አካባቢ የግንባታ ፕሮጀክት ስላለው ይመላለስ እንደነበር ገልጿል።
ከግድያው በፊት “ራሱን በማስክ እና በጥቁር መነጽር እየሸፈነ ‘አገባሻለሁ’ እያለ ያስፈራራት ነበር” ሲልም አክሏል።
የሰንዳፋ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ንጋቱ፤ ተጠርጣሪው ፀጋዬ አሳልፈው እና አዳነች “በፍቅር ግንኙነት ውስጥ” እንደነበሩ የፖሊስ ምርመራ “እንደሚጠቁም” ገልጸዋል።
አዳነችን እንዲሁም ቤተሰቧን በቅርብ የሚያውቀው የቢቢሲ ምንጭ ግን ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጿል። በተደጋጋሚ ‘አገባሻለሁ’ በሚል ሲያስፈራራት እንደቆየም አስረግጦ ተናግሯል።
ኮማንደር ንጋቱ በበኩላቸው፤ ግድያው በተፈጸመበት ዕለት ተጠርጣሪው እና አዳነች “ሆቴል ምግብ አዝዘው” እንደነበር ተናግረዋል።
“የሮሰን ሆቴል ምግብ አዝዘው ነበር። [አዳነች] ምግቡን ሳትበላ ሆቴሉን ጥላ ስትሄድ ተጠርጣሪው በመኪና ተከትሏታል። ከዚያም ወደ ጎማጣ ሰፈር ወስዶ በጥይት ገድሏታል” ብለዋል።
ጎማጣ የሚባለው አካባቢ ከሰንዳፋ ከተማ ወጣ ያለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, FB
ቢቢሲ ያነጋገረው የአዳነች አብሮ አደግ እንደተናገረው አዳነች “እጄን ልታጠብ” ብላ “ከሆቴሉ ለማምለጥ” ሞክራለች። ተጠርጣሪው ግን እንደተከተላት አክሏል።
የሰንዳፋ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ንጋቱ “ተጠርጣሪው ግድያውን ከፈጸመ በኋላ በአለልቱ ከተማ መኪናውን እና መሣሪያውን ጥሎ” መሰወሩን ገልጸዋል።
“መኪናውን እና ለግድያ የተጠቀመውን መሣሪያ በአለልቱ ከተማ ጥሎት ሄዷል። መኪናው ውስጥ ደም እና መሣሪያ ተገኝቷል። ይህም ግድያው የተፈጸመው መኪና ውስጥ መሆኑን ይጠቁማል” ሲሉ አስረድተዋል።
ተጠርጣሪው አዳነችን በጥይት ከገደለ በኋላ አስከሬኗን ጥሎ እንደሄደ እና አስከሬኗ በጅብ እንደተበላም ገልጸዋል።
በአካባቢው የተኩስ ድምጽ የሰሙ ሰዎች ጥቆማ እንደሰጡ የተናገሩት ኮማንደር ንጋቱ፤ ፖሊስ ያገኘው መኪና ማኅበረሰቡ ከሰጠው ጥቆማ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነም አስረድተዋል።
ከጅብ የተረፈው የአዳነች አስከሬን ለምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተወስዶ የነበረ ሲሆን፤ ሥርዓተ ቀብሯም ተፈጽሟል።
ተጠርጣሪው መሣሪያውን እና መኪናውን ጥሎ ከአካባቢው ከሸሸ በኋላ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ፍለጋውን መቀጠሉን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ያለፈው ኅዳር መባቻ ላይ ለፀረ የሴቶች ጥቃት ቀን ያወጣው ሪፖርት፤ በዓለም ዙሪያ በየ10 ደቂቃው አንዲት ሴት በምታውቀው ሰው እንደምትገደል ይጠቁማል።
ገዳዩ የፍቅር አጋሯ፣ ባለቤቷ ወይም ቤተሰቧ ሊሆን እንደሚችል ሪፖርቱ ያሳያል።
በተመድ ሪፖርት መሠረት በየቀኑ 137 ሴቶች ይገደላሉ። ይህም በመላው ዓለም በአዋቂ ሴቶች እና በታዳጊ ሴቶች ላይ ከሚፈጸም ግድያ 60 በመቶ ነው።