አሜሪካ ከ30 አገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶቿ ወደ ዋሺንግተን እንዲመለሱ አዘዘች

የትራምፕ አስተዳደር ያለ ምንም ማብራሪያ በተለያዩ የዓለም አገራት ውስጥ የሚገኙ ወደ 30 የሚጠጉ አምባሳደሮችን እና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ሥራቸውን አቁመው ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ አዘዘ።

“ቅድሚያ ለአሜሪካ” ከሚለው የዶናልድ ትራምፕ መርህ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ለውጥ ማድረግ በፈለገባቸው እና ከፍተኛ ሚና የላቸውም ከተባሉ አገራት ዲፕሎማቶቹ እንዲወጡ ተደርጓል።

ለአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ወደ 30 የሚጠጉት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ያለምንም ማብራሪያ የተመደቡባቸውን አገራት ለቅቀው ወደ ዋሺንግተን እንዲመለሱ በስልክ ተነግሯቸዋል።

ይህ የማሰናበት የሚመስለው መልዕክት ለአምባሳደሮቹ መድረስ የጀመረው ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከተመደቡባቸው አገራት እንዲመለሱ የተነገራቸው የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ውስጥ የሚሆናቸውን አዲስ የሥራ መደብ እንዲፈልጉ መመከራቸውን አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

በዚህ ውሳኔ ከተመደቡባቸው የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ለቅቀው ወደ ዋሺንግተን እንዲመለሱ ከተነገራቸው ዲፕሎማቶች መካከል አብዛኞቹ ከአፍሪካ አገራት ሲሆኑ፣ አምባሳደሮቹ ግን በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ አገራት ነው።

የአሜሪካ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች እንዲወጡ የተደረጉባቸው ናቸው ብሎ ኤፒ ባወጣው ዝርዝር ውስጥ 28 አገራት የተጠቀሱ ሲሆን፣ ግማሾቹ የአፍሪካ አገራት ናቸው።

ከእነዚህም ውስጥ የአሜሪካ ወዳጅ የሆነችው ግብፅ እና በአፍሪካ ቀንድ የአልቃይዳ አጋር የሆነው አልሻባብ የሚንቀሳቀስባት ሶማሊያ ተጠቅሰዋል። https://www.bbc.com/amharic/articles/c709gye00r5o