ዓለማቀፉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን በጋምቤላ የተቀሠቀሠው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉን አስታወቀ።

ዓለማቀፉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን (ኤም ኤስ ኤፍ)፣ በጋምቤላ የተቀሠቀሠው ግጭት በትናንትናው ዕለት ተባብሶ መቀጠሉን አስታወቀ።

ቡድኑ፣ ትናንት ረቡዕ ብቻ ከ100 በላይ “በመሳሪያ የቆሠሉ” ሰዎችን ተቀብሎ ማከሙን ባወጣው መግለጫ ገልጧል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በግጭቱ ለቆሠሉ ታካሚዎች ኩሌ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሕክምና እርዳታ መስጠት በጀመረ በ48 ሰዓት ውስጥ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሠባቸውን 19 ሰዎች ጨምሮ 50 ቁስለኞችን ማከሙን የገለጠው ቡድኑ፣ ባለፉት 7 ቀናት ከ150 በላይ ቁስለኞችን ተቀብያለሁ ብሏል።

ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ የበርካቶች ሕይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱንና ግጭቱ በዚሁ ከቀጠለ ወደ ሕክምና ጣቢያው የሚገቡ ቁስለኛ ታካሚዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ቡድኑ ገልጧል።

ቡድኑ፣ በቁስለኞች ብዛት ሳቢያ የጋምቤላ ከተማ ሆስፒታል ሳምንቱን ሙሉ የተመላላሽ ሕክምና አገልግሎት ማቆሙንና ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችም መስተጓጎላቸውን ጠቅሷል።

የሲቪሎች ደኅንነት “በጥልቅ” እንዳሳሰበው ቡድኑ የገለጠ ሲሆን፣ የታካሚዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና የሕክምና ተቋማት ከጥቃት እንዲጠበቁም ጥሪ አድርጓል።