በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ከመጋረጃ ጀርባ የመሰከረው ግለሰብ ታወቀ

በእነ የተከበሩ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ከመጋረጃ ጀርባ የመሰከረው ግለሰብ መቶ አለቃ አሰፋ አድማሱ መሆኑ ተረጋገጠ።

ግለሰቡ በምዕራብ ጎጃም ዞን የቋሪት ወረዳ ተወላጅ ሲሆን እስከ 2016 ዓ.ም ታህሳስ አጋማሽ ድረስ በገረመው ወንዳወቅ ብርጌድ የፋኖ አባል ነበር።

ግለሰቡ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊና የቀድሞው የባህርዳር ከንቲባ ድረስ ሳህሉ የቅርብ ዘመድ ሲሆን ከዚሁ ባለስልጣንም ሽልማት ተቀብሏል። ከዚህ በተጨማሪም በእስር ላይ ከሚገኙት የምክር ቤት አባሉ ከአቶ ክርስቲያን ታደለ ጋር የቅርብ ዘመድም መሆኑ ተገልጿል። አቶ ክርስቲያን ታደለ ምርጫ ሲወዳደሩ ምርጫውን አሸንፈው የምክርቤት አባል እንዲሆኑ ቅስቀሳ ሲያደርግ ነበር።

ይሁን እንጅ ግለሰቡ ጥቅም ፈላጊ በመሆን በመንግስትም በታጋዮቹም ዘንድ ለመመስገን ጥረት ያደርግ እንደነበር የቅርብ ማስረጃዎች አሉ። በዚህም በቋሪት፣ በፍኖተ ሰላምና በባህርዳር ቤትና ሌላ ንብረት ያለው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ፋኖን በመክዳት ከመንግስትና ከብልጽግና ፓርቲ ጋር እየሰራ ይገኛል።

በነገራችን ላይ ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የተለየ ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል።

ግለሰቡ ለፍትሕ ሚኒስቴር ቃል በገባኸውና እኛ ባልንህ መሰረት አልመሰከርክም፤ ይህንን ያደረከው ደግሞ ከተከሳሾች ጋር ተደራድረህ ነው የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰበት እንደሆነ የዐቃቤ ሕግና የደህንነት ምንጮች አረጋግጠዋል።

ከመጋረጃ ጀርባ የመሰከረው ይህ ግለሰብ ሊታሰርና ክስ ሊመሰረትበት እንደሚችልም ተገልጿል።