በካማሺ ከተማ የሰዓት ዕላፊ ተጥሏል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ምዥጋ ወረዳ በክልሉ ልዩ ኃይሎችና በመጋቢት ወር ዕርቅ ፈጽመው ከጫካ በተመለሱ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ታጣቂዎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ፣ የ19 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ከተገደሉት መካከል የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብደኑ ጀርሞሳ፣ አንድ የአካባቢው ባለሀብትና ልጃቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 16 ሰዎች የጉህዴን ታጣቂዎች እንደሆኑ ለሪፖርተር የተናገሩት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ኡመር ሙስጠፋ፣ ዋና አስተዳዳሪውን ጨምሮ ሦስቱ ግለሰቦች ሕይወታቸው ያለፈው በተኩስ ልውውጥ መሀል በመታቸው ተባራሪ ጥይት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተኩስ ልውወጡ ከመንግሥት ኃይሎች መካከል ሕይወቱ ያለፈ ሰው ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም፡፡
ኮሚሽነር ኡመር በሳምንቱ አጋማሽ ለተደረገው የተኩስ ልውውጥ፣ ‹‹ካለፈው ሦስት ሳምንት ወዲህ ከአቅም በላይ እየሆኑ መጥተዋል›› ያሏቸውን የጉሕዴን ታጣቂዎች ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ በዕርቁ ወደ ከተማ እንዲገቡ የተደረጉት ታጣቂዎች ባለፉት ሳምንታት ዘረፋን ጨምሮ የተለያዩ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ እንደነበር የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ ዕርቅ በመፈጸሙ ምክንያት የክልሉ ኃይሎች እንዲታገሱ ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ድርጊቶቹ እየጨመሩ ሲመጡ የክልሉ ኃይሎች ‹‹ራሳቸውን እንዲከላከሉ›› እንደተናገራቸው አስታውቀዋል፡፡
ስለረቡዕ ዕለቱ ተኩስ ልውወጥ ሲገልጹ፣ ‹‹በልዩ ኃይል ካምፕ ላይ የመድፈር ሁኔታ ታይቶ ነው›› ያሉት ኮሚሽነር ኡመር፣ ታጣቂዎች የመጀመሪያውን ተኩስ በመክፈታቸው ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ውስጥ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡
የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ ፃፊዎም በተመሳሳይ ተኩሱ የተከፈተው በታጣቂዎች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዕርቁ ሒደት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለአራት ወራት ያህል ሞትም ሆነ ተኩስ እንዳልነበረ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁኔታዎች የመቀየር አዝማሚያ እንደታየባቸው ተናግረዋል፡፡
በካማሺ ዞን በተለይ በያሶ ወረዳ ጫካ ገብተው ከመንግሥት ጋር ሲዋጉ የነበሩት የጉሕዴን ታጣቂዎች ወደ ከተማ የገቡት፣ መንግሥትና ታጣቂዎች መጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ያደረጉትን ባህላዊና ሃይማኖታዊ የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ተከትሎ ነው፡፡
ዕርቁ በይፋ ከመፈጸሙ በፊት በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች አማካይነት የክልሉ መንግሥትና ታጣቂዎች ንግግር ሲያደርጉ ነበር፡፡ ታጣቂዎቹ ወደ ዕርቅ ለመምጣት ካቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ በእስር ላይ የሚገኙ አመራሮቻቸው እንዲፈቱ የሚጠይቅ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት የጉሕዴን ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታን ጨምሮ ሦስት አመራሮችና በርካታ አባላት ከእስር ተፈተዋል፡፡
በሁለቱ ኃይሎች መካከል ንግግር ሲደረግ ከዕርቁ መፈጸም በኋላ ታጣቂዎቹ ትጥቅ እንዲፈቱ ስምምነት እንደነበረ የተናገሩት ኮሚሽነር ኡመር፣ ‹‹መሣሪያ እንዲያስረክቡ ወደ እዚያ ሲኬድ ዘራፍ የሚባል ነገር መጣ፤›› በማለት ከዕርቁ በኋላ ታጣቂዎቹ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡
ረቡዕ ዕለት ከተደረገው የተኩስ ልውወጥ በኋላም በማግሥቱ ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በካማሺ ከተማ የሚገኙ ልዩ ኃይሎች በታጣቂዎቹ ከበባ እንደ ተፈጸመባቸው ጠቁመው፣ ኮሚሽናቸው ‹‹ከሞላ ጎደል›› ዕርቁ ፈርሷል ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹አሁን በአካባቢው ውዥንብር አለ፣ ጥይቱ በየትኛው ሰዓት እንደሚፈነዳ አይታወቅም፣ ከዚህ የተነሳ ነው ዕርቁ ፈርሷል የምንለው፤›› ብለዋል፡፡
የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ፣ ‹‹ዕርቁ ፈርሷል›› የሚለውን ሐሳብ እንደማይስማሙበት አስታውቀዋል፡፡ የአፈጻጸም ችግሮች ቢኖርበትም ዕርቁ ‹‹ውጤታማ›› እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ብጅጋ፣ ‹‹እኛ ዕርቁ ፈርሷል ብለን አልገመገምንም፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና የምዥጋ ወረዳው ክስተት የዕርቁን ሒደት ወደኋላ ይወስዳል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው እንደሚሉት፣ መንግሥትና ታጣቂዎቹ ስምምነታቸው በፊርማ እንዲያኖሩ ከመንግሥትና ከታጣቂዎች በተወከለ ኮሚቴ ሰነድ የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ታጣቂዎቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች በሰነዱ ላይ መካተታቸውን የተናገሩት አቶ ብጅጋ፣ ‹‹ዕርቁ እንዲፈርስ የሚጥር ቡድን አለ፣ ምዥጋ ላይ የተፈጸመው ይኼንን ነገር ወደ ኋላ ለመመለስ የሚደረግ ጥረት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በቀጣይ የሚኖረው ዕርምጃ ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ በመንግሥት በሚቀመጥ አቅጣጫ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና በካማሺ ዞን በክልሉ መንግሥትና በታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተባብሶ ዓርብ ግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት የዞኑ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፣ በካማሺ ከተማ የሰዓት ገደብ መጣሉን አስታውቋል፡፡ የዞኑ ፀጥታ ምክር ቤት ‹‹በየአቅጣጫዎች ለማኅበረሰቡ ደኅንነት ሥጋት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ስላሉ›› በሚል በጣለው የሰዓት ገደብ ከምሽቱ 2:00 ሰዓት በኋላ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ አግዷል፡፡
የፀጥታ ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ የመንግሥትም ሆነ የግል ሞተር ብስክሌቶች በከተማ ውስጥም ሆነ ውጪ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችሉ ገልጾ፣ ይህንን ተላልፈው በተገኙ አካላት ላይ የፀጥታ ኃይሉ ለሚወስደው ዕርምጃ መንግሥት ኃፊነቱን እንደማይወስድ አስጠንቅቋል፡