ፍርድ ቤቱ የቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎችም ትክክለኛ የመኖሪያ አድራሻቸው ባለመታወቁ አድራሻቸው ተጣርቶ እንዲቀርብ አዘዘ

ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ክስ ላይ በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ የመከላከያ ምስክርነታቸው እንዲሰማ ታዘው የነበሩት የቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎችም ትክክለኛ የመኖሪያ አድራሻቸው ባለመታወቁ አድራሻቸው ተጣርቶ እንዲቀርብ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጠ።

በመጋቢት 14 ቀን 2014 በነበረ የችሎት ቀጠሮ የቀድሞ የኢፌዴሪ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በተከሰሱበት የዕርሻ መሳሪያ ግዢና የመርከብ ግዢ የሙስና ክስ ላይ በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት የቀድሞ ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞ የጀርመን አንባሳደር በአሁን ወቅት በአሜሪካ የሚገኙች ፍስሀ አስገዶም፣ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ካውንስለር ካሳና የቀድሞ የፖላንድ አንባሳደርን ጨምሮ ከዛሬ ግንቦት 3 ቀን እስከ ግንቦት 5 ቀን ድረስ ባሉበት አገር ሆነው በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ የመከላከያ ምስክርነታቸው እንዲሰማ ትዛዝ ተጥሰቶ ነበር።

ሆኖም በዛሬው የችሎት ቀጠሮ በውጭ አገር የሚገኙት ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎችም የመከላከያ ምስክሮች ትክክለኛ የመኖሪያ አድራሻቸው አለመመታወቁን ፍርድ ቤቱ ተገልጿል።

በጠበቃ ዘረሰናይ በኩል ግን የኃይለማርያም ደሳለኝ አድራሻ ጀርመን ወይም አሜሪካ ሊሆን እንደሚችል በቃል ገልጿል።

በተጨማሪም ጠበቃ ዘረሰናይ የኃይለማርያም ተወካይ በሀዋሳ እንደሚኖር በማብራራት ለምስክርነት ዝግጁ እንዲሆኑ ለተወካያቸው እንደሚያሳውቀው አስተያየት ሰጥቷል።

በፍርድ ቤቱ በኩል ግን የምስክሮቹ ትክክለኛ መገኛ (የመኖሪያ) አድራሻ አለመገለጹ ተከትሎ ምስክርነታቸውን ለመስማት እንደሚያስቸግር በመጠቆም፤ ባሉበት ቦታ የምስክሮቹን የቨርቹዋል ቴክኖሎጂያቸውን ክትትል ማን ያደርጋል የሚል ጥያቄ ተነስቷል።

ጠበቃ ዘረሰናይ በበኩሉ፤ በፍርድ ቤቱ በኩል የኢንተርኔት ቴክኖሎጂው ከተመቻቸ ምስክሮቹ በማንኛውም ጊዜ በበየነ መረብ ስብሰባ እንደሚጠቀሙት ኹሉ የመከላከያ ምስክርነታቸው ሊሰማ እንደሚችል እና መገኛ አድራሻቸውንም ማጣራት እንደሚቻል ሀሳብ ተሰጥቷል።

ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር የኢንተር ፖል ስምምነት እንዳላት በመጥቀስ፤ በዚህ ስምምነት መሰረት ለፀረ ሽብር በማስረጃ የሚፈለጉ ሰዎች ተፈልገው እንዲሰጡ ይደረጋል ያሉ ሲሆን፤ በዚህ መልኩ መገኛቸው ተፈልጎ እንዲሰጡ ቢደረግ የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል።

በዚህ ደረጃ ከፖሊስ ጋር የሚደረግ ስምምነት እንጂ ከፍርድ ቤት ጋር የተደረገ የኢንተርፖል ስምምነት አለመኖሩን የችሎቱ ዳኞች አብራርተዋል።

የመከላከያ ምስክሮቹ ምስክርነታቸው ሲጀመር፤ ወደ አፈጻጻም ሲገባ ኢንተርኔት ቢቋረጥ፣ የሚጠየቁትን ጥያቄ ሳይመልሱ ትተው ቢሄዱ እንኳ የምስክር አሰማም ሂደቱን መቆጣጠር የሚያስችል እንዳይሆን ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን በሀሳብ ደረጃ የችሎቱ ዳኞች ገልጸዋል።

ጠበቃ ዘረሰናይ የምስክሮቹን መገኛ አድራሻ እና ሰዓት አጣርተን እንቀርባለን ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ሆኖም የምስክር አሰማም በፍርድ ቤቱ በኩል ስርዓትና አካሔድ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ አግባብ ሊኬድና ጥንቃቄ መደረግ ስላለበት እያንዳንዱ ምስክር መገኛ አድራሻቸው በምን አግባብ እና በየትኛው ሰዓት ይገኛሉ የሚለውን ግልጽ ሆኖ ተጣርቶ ትዕዛዝ መሰጠት እንዳለበት በችሎቱ ዳኞች ተብራርቷል።

በዚህም መሰረት በውጭ አገር የሚገኙት የሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው መከላከያ ምስክሮች ትክክለኛ አድራሻ ተጣርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በዚሁ መዝገብ በአካል ቀርበው ለመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩ በመከላከያ ሚኒስቴር ሥር የሚገኙ አራት ምስክሮችን በተመለከተ ትዕዛዝ ወቶ በመከላከያ ሚኒስቴር በኩል ምንም አይነት ምላሽ ባለመቅረቡ ትዕዛዙ በድጋሚ ወጪ ተደርጎ በፌደራል ፖሊስ መጥሪያ እንዲደርሳቸው ታዟል።

በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ ቀርበው በመከላከያ ምስክርነታቸው እንዲሰማ ትክክለኛ መገኛ አድራሻቸው ተጣርቶ እንዲቀርብ የታዘዙ ምስክሮችን የአድራሻ ውጤት ለመጠባበቅ እንዲሁም በድጋሚ መጥሪያ ደርሷቸው በአካል እንዲቀርቡ የታዘዙ አራት ምስክሮችን የመከላከያ ምስክርነትታቸውን ቃል ለመስማት ከሰኔ 20 ቀን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በሌላ በኩል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መጥሪያ እንዲደርሳቸው በጥር 23 ቀን ትዕዛዝ የወጣባቸው የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን በተመለከተ በምን አግባብ ይቀርባሉ የሚለውም በዚሁ ተመሳሳይ ቀጠሮ ተጣርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ትዕዛዙን ተከትሎ ጠበቃ ዘረሰናይ ከዶ/ር ወርቅነህ ጋር አብረዋቸው በሚሰሩት በቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ በኩል አጣርቶ ምላሽ እንደሚያቀርብ መግለፁን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

በዚህ በዛሬው ቀጠሮ ከዓቃቢህግ በኩል የቀረበ ተወካይ አለመኖሩም ታውቋል።