በትግራይ ክልል ለወራት ከተቋረጠ መሰረታዊ አገልግሎች ጋር ተያይዞ ነዋሪዎች በከፋ ችግር ላይ መሆናቸውን ተናገሩ ። በከተሞች የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር ባልተለመደ ሁኔታ ጨምሯል፣ በልመና የሚተዳደሩ አዛውንቶችና ሴቶች ተበራክተዋል፣ ከእርዳታ አቅርቦት መስተጓጎል ጋር በተገናኘ ምክንያት በመጠልያዎች የነበሩ ተፈናቃዮች እየተበተኑ መሆኑም ተገልጿል።
በትግራይ ላለፉት ስድስት ወራት የባንክ፣ ቴሌኮም፣ የምድርና አውሮፕላን መጓጓዣ የተቋረጠ መሆኑን እና ህዝቡ በፋይናንስ ተቋማት ያስቀመጠውን ገንዘብ ሊያገኝ እንዳልቻለ ይገልጻል። መድሃኒትን ጨምሮ ሌሎች የፍጆታ ሸቀጦችም ከሀገር ውስጥ ይሁን ከውጭ እንዳልገባለቸው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።