በርካቶች የፊልድ ማርሻል ማዕረግ ላይ ጥያቄዎችን ቢያነሱም ጄኔራል ባጫ ደበሌ ጥያቄውን ያነሱት ጁንታና የጁንታ ደጋፊዎች ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገሪ ቱ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም የተሰጠው ‘የፊልድ ማርሻል’ ማዕረግ አገርን ከከባድ አደጋ ለታደጉ የጦር መኮንን መበርከቱ አግባብ ነው ሲሉ ጄነራል ባጫ ደበሌ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከቀናት በፊት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ለጄነራል ብርሃኑ ጁላ የፊልድ ማርሻል ማዕረግ መስጠታቸው ይታወሳል።

በዕለቱ የተሰጠው የፊልድ ማርሻልነት ማዕረግ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ከፍተኛው ወታደራዊ ሹመት ሲሆን በዕለቱ ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተጨማሪ ለ100 የሠራዊቱ አባላት የተለያዩ ወታደራዊ ማዕረጎች ተሰጥቷዋል።

በዕለቱ ለጀነራል ብርሃኑ ጁላ የፊልድ ማርሻል ማዕረግ የተሰጠው፤ በጄነራሉ አመራር ሰጪነት የህወሓት ኃይሎችን መመከት በመቻሉ እና የተመዘገበው ስኬት አገርን ከውድቀት የታደገ መሆኑን ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ የአገር መከላከያ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

ይሁን እንጂ በርካቶች የጦር መኮንኑ የመሩት በአገር ውስጥ የተደረገ የእርስ በእርስ ጦርነት መሆኑን በማውሳት የተሰጠው የፊልድ ማርሻል ማዕረግ ላይ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ነበሩ።

በሥነ ሥርኣቱ ላይ ከሌተናል ጄነራልነት ማዕረግ ወደ ጄነራልነት ከፍ ያሉት ባጫ ደበሌ ግን ለኤታማዦር ሹሙ የፊልድ ማርሻል ማዕረግ መሰጠቱ ትክክል ነው ይላሉ።

ጄነራል ባጫ፤ የፊልድ ማርሻል ማዕረጉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር መሰጠቱን በማስታወስ የሹመቱን ሕጋዊ አካሄደ ትክክለኛነትን አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል።

ጄነራል ባጫ አገራት የፊልድ ማርሻል ማዕረግ በመስጠት የተለያየ ተሞክሮዎች እንዳላቸውና ማዕረጉን ለረዥም አገልግሎት በክብር የሚሰጡት አገራት እንዳሉት ሁሉ፣ ሕግ ለማስከበር የጦር ሜዳ ውሎን መሠረት በማድረግ የፊልድ ማርሻል ማዕረግ የሚሰጡ አገራት እንዳሉም አስረድተዋል።

“ለምሳሌ ሩሲያን ብንወስድ ለመጨረሻ ጊዜ የፊልድ ማርሻል ማዕረግን የሰጠችው የሶቪዬት ኅብረት ከፈረሰ በኋላ ሠራዊቱ መልሶ እንዲደራጅ፣ የአገሪቱ የኒውክሊር ትጥቅ እንዳይበተን እና ሩሲያ ታላቅነቷን እንድታስቀጥል ላስቻለ መኮንን ይህ ማዕረግ ተሰጥቶታል” ብለዋል።

በሌላ በኩል የጦርነት ተሳትፎን ተከትሎ አሜሪካዊው ጆርጅ ዋሽንግተን ከአገሩ የፊልድ ማርሻል ማዕረግ እንደተበረከተላቸው ጀነራል ባጫ ያስረዳሉ።

“ጆርጅ ዋሽንግተን የፊልድ ማርሻል ማዕረግ ተሰጥቶታል። ይህም በአሜሪካ የእርስ በእስር ጦርነት ወቅት ዋሽንግተን በፈጸሙት ጀብዱ ነው የተሰጣቸው። በየትኛውም ጦርነት ወቅት ብቃት ላሳየ ይህ ማዕረግ ይሰጣል” ይላሉ።

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ “የአገር ውስጥ እና የውጭ ኃይሎች” አገሪቱን ለማፈራረስ በተነሱ ወቅት የተደቀነባትን ከባድ አደጋ መቀልበስ ለቻሉት ይህ ማዕረግ መሰጠቱ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለዋል።

“በኢትዮጵያ የሰለጠን ጦር መልሶ ይወጋታል ተብሎ አልተጠበቀም። ይህ አዲስ ክስተት ነው። መላ የሠራዊቱ ትጥቅ ተቀምቶ፤ ኢትዮጵያ ወታደር የሚባል የላትም ከተባለ በኋላ ተጋድሎ ተደርጎ አገሪቷ እና ሠራዊቱን ከመበተን ላዳነ . . . የፊልድ ማርሻል ማዕረግ መስጠት ያንስ ይሆናል እንጂ አይበዛም” በማለት ጄነራል ባጫ የውሳኔውን ትክክለኛነት ያስረዳሉ።

ፊልድ ማርሻል የሚለው ማዕረግ በምን ሁኔታ ይሰጣል የሚለውን ማየት አስፈላጊ ነው የሚሉት ጄነራል ባጫ “ጉዳዩ የእስር በእርስ ጦርነት አልያም ዓለም አቀፍ ጦርነት በመሆኑ አይደለም። የጦሩ መሪ ለአገሪቱና ለሠራዊቱ ባበረከተው አስተዋጽኦ ነው።”

በተጨማሪም በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት፣ ጦርነቱን በማስቀረትና ያስከተለውን ጉዳት መቀነስ ባልተቻለበት ሁኔታ ለሠራዊቱ መሪ የፊልድ ማርሻል ማዕረግ መሰጠቱን ተገቢ አይደለም በሚል የሚቀርበውን ትችት ጄነራል ባጫ አይቀበሉም።

“ሠራዊቱ ተልዕኮውን መፈጸም ባይችል ኖሮ ይሄኔ ወያኔ አዲስ አበባ ነበር። ይህን የሚሉት እውነት ኢትዮጵያውያንም አይመስሉኝም። ይህን የሚለው ጁንታ ነው ወይ ደጋፊ ነው። ምክንያቱም ስለ ኢትዮጵያ የሚያስብ ይህን አይልም። ሠራዊቱ ድል ነው ያደረገው። ለዚህ ደግሞ አፋችንን ሞልተን ደረታችን ገፍተን ነው የምንናገረው።”

ከሦስት ቀናት በፊት በነበረው ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ ካገኙት የጦር መኮንኖች መካከል አንዱ የሆኑት ጄነራል ባጫ ደበሌ የማዕረግ እድገቱ የፈጠረባቸውን ስሜት ለቢቢሲ አጋርተው ነበር።

“ሠራዊት በአደረጃጀት ሲሰፋ እንደዚህ አይነት ማዕረጎች ይሰጣሉ። ከሠራዊቱ ስፋት አንጸር ብዙ ሥራ ነበር። ይህን ሥራ በብቃት እና በጀግንነት መወጣት በየደረጃው ላሉት የሠራዊት አባላት የማዕረግ እድገት ተሰጥቷል። እኔም ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ በመሆኔ በጣም ደስ ብሎኛል” ብለዋል።

ጀነራል ባጫ፤ የማዕረግ እድገቱ “ደስታን የሚፈጥር እና የበለጠ ሥራ ለመስራት የሞራል ኃይል” የሚሆን ነው በማለት “ለአገራችን ለምንከፍለው መሥዋዕትነት ዝግጅት ላይ ከፍትኛ አስተዋጽኦ ስላለው ደስታችን ወደር የለውም” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።

ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቅራቢነት በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የተሰጡት ከፍተኛ ወታደራዊ ሹመቶች 100 ሲሆኑ፣ 4 የጄነራል ማዕረግ፣ 14 የሌተናል ጄነራል ማዕረግ፣ 24 የሜጀር ጄነራል ማዕረግ እና 58 የብርጋዲየር ጄነራል ማዕረግ ለሠራዊቱ መኮንኖች ተሰጥቷል።