የትግራይ ድርጅቶች አፍራሽ ሳይሆን ገንቢ ሚና ቢጫወቱ ጥሩ ነው (ግርማ ካሳ)


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

በአጭሩ የታንድ መግለጫ፣ ታንድ ገንቢ ሳይሆን አፍራሽ፣ አቀራራቢ ሳይሆን የሚያራርቅ፣ መፍትሄ ላይ ያተኮረ ሳይሆን ያከረረ፣  ሕወሃት ከያዘው የግትርነት አቋም በጭራሽ ያልተለየ አመለካከት እንዳለው በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት እንደ ታንድ፣ አረና ያሉ ቢያንስ ለሕዝብ ያስባሉ ያልኳቸው ድርጅቶች የችግሩ አካል ሳይሆን የመፍትሄ አካል ይሆናሉ ብዬ ተስፋ አደርግ ነበር። ግን ከነዚህ ደርጅቶች የማየው ነገር ደስ አያሰኝን አይደለም።

ወደ ትግራይ የሚወስዱ መንገዶች እየተዘጉ ነው። ትግሬ ላይ ጥላቸው ቀላል አይደለም። መሆን ያልነበረበት እዉነታ ነው። ግን እነ ታንድ መረዳት ያለባቸው የሃያ ሰባት አመታት የሕወሃት ዘረኛ አገዛዝ የፈጠረው ችግር መሆኑን ነው።ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ ብለው ሰዉን የከፋፈሉት ፣ እንደ ትግሬ ፣ እንደ አማራ፣ እንደ ኦሮሞ ብቻ እንዲያስብ ያደረጉት ራሳቸው ከትግራይ የወጡ ትግራይ ፖለቲከኞች ናቸው። የአማራው ማህበረሰብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ብቻ እያለ ነበር ሲደራጅ የነበረው። እንደውም ሕወሃቶች ናቸው “ኢትዮጵያ ብላችሁ መጠራት የለባችሁም” ብለው ኢህዴን (የኢትይጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅንቄ) የሚለውን ስም ወደ ብአዴን እንዲቀየር ያደረጉት። የአማራ ብሄረተኝነትን የወለዱት፣ ወተት እየጋቱ ያሳደጉት፣ ያበረታቱት፣ ነዳጅ የጨመሩበት፣ እንዲጠናከር ያደረጉት ራሳቸው ሕወሃቶች ናቸው።

ታዲያ ብሄረተኝነት፣ የዘር ፖለቲካ ስር በሰደደበት በተስፋፋበት ሁኔታ ጤናማ ነገር መጠበቃቸው፣ እሳት ተለኩሶ ለምን አቃጠለ ማለታቸው አርቆ ማሰብ አለመቻላቸውን ነው የሚያሳየው። አንድ ነገር ከራስ አንጻር ብቻ ማየት ጠባብነት ብቻ ሳይሆን ደካማነት ነው። ታንዶች ከዚያኛው ወገን ያለውን ሁኔታ ለመረዳት የቻሉ አልመሰለኝም።

አዎን ትግሬዎች ላይ ጥላቻ አለ። አዎን ትልቅ ችግር አለ። አዎን እሳት አለ። እሳቱን ራሳቸው ለኩሰዉት ለምን አቃጠለን ብሎ ማለቃቀስ ሳይሆን ካለፈው ስህተት ተምረው፣ እሳቱን በቶሎ እንዴት በጋራ ማጥፋት እንደሚቻል ማሰብና መሰራቱ ነው የሚበጀው። ይሄንን ጥላቻ እንዴት እናስወግደው የሚለው ላይ ነው ማሰብና መጨነቅ የሚያስፈልገው። ግን እነ ታንድና አረና ያንን እያደረጉ አይደለም። እንደው ከሕወሃት ጋር ተደርበው የችግሩ አካል እየሆኑ ነው።

ሶስት ነገር በግልጽ ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል።፡

– ወልቃይትና ራያ የትግሬ ነው በሚል አሁን ያለው ሁኔታ ይቀጥል ከተባላ፣ ወልቃይትና ራያ የአማራ ነው የሚል ትልቅ ሃይል ስላለ ውጤቱ መጋጨት ነው። ጦርነት ነው።፡ ይሄ ደግሞ ለማንም አይበጅም።

– የአማራ ክልል መንግስት እንደውም በጣም ሞደሬት ነው። ነገሮችን ለማርገብ፣ ለማስተካከል ትልቅ ፍላጎት አለው።፡ ግን ወልቃይትንና ራያን በትግራይ ውስጥ የሚቀጥሉ ከሆነ የክልሉ መንግስት ትልቅ ችግር ውስጥ ነው የሚወድቀው። ብአዴን/አዴፓ ያበቃለታል። የወልቃይትና የራያ ጥያቄ በአማራ ክልል ሆነ ከዚያም አልፎ ታች ቀበሌ ድረስ የወረደ ጥያቄ ነው። የክልል መንግስቱም ሆነ አዴፓ ምርጫ አይኖረውም።

– የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚባለው አሁን ባለው ሕገ መንግስት መሰረት የወልቃይትንና የራያን ጥያቄ መፍታት አይችልም። አንደኛ ሕገ መnግስቱም የፌዴራል አወቃቀሩም በሕወሃት እና ኦነግ በሕዝቡ ላይ የተጫኑ ናቸው። የአሸናፊዎች ሕግ መንግስት ነው።  ሁለተኛ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የተባሉት ደግሞ በሞቶ በሞቶ ምርጫ አሸነፉ ተብለው የተቀመጡ ሕዝብን የማይወክሉ፣ ብቃት የሌላቸው  ናቸው።

መፍትሄው በተደጋጋሚ ብዙ ጊዜ እንደጻፍኩት፣ በጊዚያዎነት፣  የዘር መካረሩ ትንሽ ረገብ እስኪል፣ የራያ/አላማጣና፣ ወልቃይት ጠገዴ የፌዴራል ልዩ ዞን ሆነው (እንደ ድሬዳዋ ከተማ) ፣ አማርኛና ትግሪኛ የስራ ቋንቋ ተደርጎ፣  ትግሬ፣ አማራ ሳይባባሉ የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸቱ ነው የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ።

አንዳንዶች ህዝብ ዉሳኔ ይደረግ ይላሉ። በሶማሌና በኦሮሞ መካክል በአራት መቶ ቀበሌዎች ዙሪያ ሕዝብ ዉሳኔ ተደርጎ ነበር። ግን ያ መፍትሄ አላመጣም። በመቶ ሺሆች ኦሮሞዎችና ሶማሌዎች እንዳይፈናቀሉ በመቶዎች እንዳይገደሉ አላደረገም። አሁንም የፌዴራል ጦር የሶማሌ ክልልን ሙሉ ለሙሉ ስለተቆጠጠረ ነው እንጂ ችግሩ አልበረደም። የወልቃይት ሕዝብ 55%  ትግሬ ሆኖ በትግራይ እንቀጥል ቢል  45% አማራ ነኝ የሚለው ደስተኛ አይሆንም። ለምን አገሩን የተነጠቀ ነው የሚመስለው። ትግራይ የትግሬዎች ስለሆነች። እንደዚሁም 55%  አማራ ነኝ ብሎ  ወደ አማራ ክልል ቢጠቃለል፣ 45% ትግሬው ደስተኛ አይሆንም። ያ ብቻ አይደለም፣ አሁን ባለውም ሁኔታ ዘርን ባማከለ ሕዝበ ዉሳኔ ማድረግ አመችና ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው የሚሆነው።

ታንድና አረና በዚህ ረገድ አሁም ከስሜታዊነትና ነገሮችን በዘር መነጽር ከማየት አልፈው ከዘለቂታዊ ጥቅም አኳያ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ በድጋሚ እጠይቃለሁ። በአሁኑ ጊዜ ትልቁ ስራ መሰራት ያለበት የዘር ጥላቻን እንዲቀንስ ብሎም እንዲወገድ ማድረግ ነው። ለዚህም ደግሞ የወልቃይትና የራይ በትግራይ ስር መቀጠል ትልቅ እንቅፋት ነው። እዚያ አካባቢ የፖለቲካ ፈውስ እንዲኖር፣ ያለዉን ሁኔታ ለማቀዝቀዝ እነ ወቅላይት በፌዴራል ስር መሆናቸው ብቸኛ ሰላምንና መረጋጋትን የሚያመጣ አማራጭ  ነው ባይ ነኝ። ይታሰብበት እላለሁ።