ደቡብ ወሎንና ሰሜን ሸዋን ሳያካትት በአማራ ክልል በአምስት ዞኖች በህወሓት አማጺያን የተጸፈመው ውድመት በአስርት ዓመታት የሚተካ አይደለም !

BBC Amharic : በትግራይ ክልል ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ወደ አማራ ክልል ከተስፋፋ በኋላ በአማጺያኑ በተያዙና አሁንም ተይዘው ባሉ አምስት የክልሎቹ ዞኖች ውስጥ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ለቢቢሲ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አንሙት በለጠ እንዳሉት በአምስቱ ዞኖች ማለትም በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደር፣ በዋግ ኽምራ እና በደቡብ ወሎ በከፊል በሚገኙ 45 ወረዳዎች ውስጥ በአማጺያኑ 280 ቢሊዮን ብር የሚገመት ዘረፋና ውድመት ደርሷል።

ይህም አሃዝ በቅርቡ ጦርነቱ የተስፋፋባቸውን የደቡብ ወሎ ዞን እና አንዳንድ የሰሜን ሸዋ አካባቢዎችን አያካትትም።

በጦርነቱ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ከተለያዩ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ጋር በጥምረት በሰራው የዳሰሳ ጥናቱ ለማወቅ መቻሉን ኃላፊው ጠቅሰው፤ በተለይ በግብርናው ዘርፍ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዳሰሳ ጥናቱ በርካታ ቦታዎችን ለመሸፈን ውስንነት እንዳለው የገለጹት አቶ አንሙት የደረሰው ውድመት 280 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ነው ብለዋል።

ኃላፊው ጦርነቱ ጠንካራ ኢኮኖሚ ወዳላቸው ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች እንዲሁም የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች በመስፋፋቱ በክልሉ የደረሰው ውድመት ከተገለጸው በላይ ከፍተኛ እንደሚሆን አስረድተዋል።

አቶ አንሙት እንዳሉት የዳሰሳ ጥናቱ በተካሄደባቸው ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ የጤና ጣቢያዎች እና የመንግሥት መሠረተ ልማቶች ወድመዋል። በተለይ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ተፈጽሞበታል ብለዋል።

“ስሪንቃ፣ ሰቆጣ እና ቆቦ ባሉ ሦስት የግብርና ምርምር ተቋማት፣ ተሽከርካሪዎች፣ ትራክተሮች፣ ሰብሎች፣ በእንስሳት ሀብት እና በመስኖ መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል” ብለዋል ኃላፊ።

የውድመት መጠኑ የተሰላው በመነሻ ዋጋ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው አሁን ባለው ዋጋና ወደፊት ሊፈጥሩት በሚችሉት ሀብት ቢሰላ የውድመት መጠኑ ከተጠቀሰው በላይ እንደሚሆን አመልክተዋል።

ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ የተፈፀመበት ሌላኛው ዘርፍ ጤና እንደሆነም አቶ አንሙት ጠቅሰዋል። እርሳቸው እንዳሉት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ክሊኒኮች ወድመዋል፤ በውስጣቸው የነበሩ ቁሳቁሶች ተዘርፈዋል።

ትምህርት ቤቶች እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተብለው የተቋቋሙ ኢንተርፕራይዞች ላይም ተመሳሳይ ውድመት መድረሱን ኃላፊው አክለዋል።

“በኢንተርፕራይዞቹ ውስጥ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎችም፣ ሠራተኞችም እንዲሁም የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ማኅበረሰቡ አባላት ሥራ አጥ ሆነዋል። መንገዶች እና ድልድዮች ወድመዋል። አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች፣ ሆቴሎችና የቱሪስት መስህብ ቦታዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብለዋል ኃላፊው።

አቶ አንሙት በአማጺያኑ ተይዘው በተለቀቁ ቦታዎች የዳሰሳ ጥናቱ አጥኝ ቡድን በአካል ተገኝተው፤ በአማጺያኑ ሥር በሚገኙ አካባቢዎች ደግሞ እዚያው ካሉ ነዋሪዎችና ለቀው ከወጡ አመራሮች ጋር ቃለ መጠይቅና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም መረጃ እንዳሰባሰቡ ተናግረዋል።

ደረሰውድመት ለክልሉ ምን ማለት ነው?

የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንሙት በለጠ ለቢቢሲ እንዳስረዱት በተጠቀሱት ቦታዎች የደረሰው ውድመትን ለመተካት በክልሉ አቅም የማይቻል ነው ብለዋል።

የክልሉ 2014 ዓ.ም በጀት 80 ቢሊየን ብር መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው ክልሉ ምንም ሳይሰራ ሁሉንም መደበኛ ሥራዎቹን አቁሞ የወደመውን ልመልስ ቢል በ10 ዓመታት ውስጥ ሊመልሰው እንደማይችል ተናግረዋል።

በፌደራል ደረጃ ያለው በጀትም 500 ቢሊየን አካባቢ እንደሆነና ይህም በብድርና በውስጥ ገቢ የተሰበሰበ ነው በማለት በክልሉ የደረሰውን ውድመት ለመመለስ በፌደራል መንግሥትም የሚቻል አለመሆኑን ገልጸዋል።

የዳሰሳ ጥናቱ ለዚህ ውድመትና ዘረፋ ተጠያቂ ያደረገው የህወሓት አማጺያንን ሲሆን፣ ይህን በቢሊዮን ብሮች የሚገመተው ውድመትም ክልሉን 40 እና 50 ዓመት ወደኋላ የሚመልስ ነው ብለዋል ኃላፊው።

ወቅት ውድመት ከደረሰባቸው ንብረቶች ባሻገር ከፍተኛ ወጪን የሚፈልጉ ሕዝብ መገልገያ ተቋማት ንብረቶች “ሆነ ተብለው በባለሙያ ተፈትተው የተወሰዱ የህክምና ማሽኖች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የግብርና መሳሪያዎች አሉ” በማለት ክልሉ በዝርፊያ ከፍተኛ ንብረት ማጣቱን አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ በክልሉ አምስት ዞኖች ውስጥ በህወሓት አማጺያን ሆን ተብለው ተፈጸሙ የተባሉትን ዘረፋዎችና ውድመቶችን በተመለከተ ቡድኑ አስካሁን ያለው ነገር የለም።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር የህወሓት ኃይሎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀሙትን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አሁንም መቋጫ አላገኘም።

ባለፈው ሰኔ ወር ላይ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ካስወጣ በኋላ የህወሓት አማጺያን ወደ አጎራባች የአማራ እና አፋር አካባቢዎች ዘልቀው በመግባት ጦርነት ከፍተዋል።

በዚህም ሳቢያ በትግራይ ውስጥ ካጋጠመው ሰብአዊ ቀውስ በተጨማሪ በሁለቱ ክልሎች ውስጥም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀልና እርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተዳርገዋል።

በአማራ ክልል በጦርነቱ ሳቢያ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የገለፀ ሲሆን፤ በቅርቡ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ ቁጥሩ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይታሰባል።

በክልሉ በህወሓት አማጺያን ለወራት ተይዘው በሚገኙ አካባቢዎች ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ምንም ዓይነት የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ አለመገኘቱን ክልሉ ገልጿል።

ይህም በአካባቢዎቹ ያሉ ነዋሪዎችን ለከፋ ችግር እንደዳረገና በአንዳንድ አካባቢዎችም በምግብና በመድኃኒት እጥረት የሰዎች ሕይወት ማለፉን ኮሚሽኑ መግለጹ ይታወሳል።