አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገትን መተንበይ እንዳልቻለ አመለከተ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በአውሮፓውያኑ 2022 አስከ 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚኖራትን አጠቃላይ አገራዊ ምርት እድገትን (ጂዲፒ) መተንበይ እንዳልቻለ ገለጸ።

ድርጅቱ ለዚህ እንደምክንያት ያስቀመጠው በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ “ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ እርግጠኛ ያለመሆን” በመኖሩ እንደሆነ ገልጿል።

ይህ የድርጅቱ አስተያየት የተገለጸው በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ አስራ አንድ ወራትን ያስቆጠረው ግጭትን ተከትሎ ነው።

አይኤምኤፍ የዓለም ምጣኔ ሀብት ገጽታ ባሳየበት ሪፖርቱ ላይ በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት የኢትዮጵያ አጠቃላይ አገራዊ ምርት 2 በመቶ እድገት ያሳያል፣ ይህም ባለፈው ዓመት ከነበረው በአራት በመቶ ዝቅ ያለ ነው ብሏል።

በንጽጽርም በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆነችው ጎረቤት ኤርትራ በመጪዎቹ 2022 – 2026 ባሉት ዓመታት የ4.8 በመቶ እድገት እንደሚኖራት ተተንብይዋል።

በሌላ በኩል በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ትልቅ የሚባለው ምጣኔ ሀብት ያላት ኬንያ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ የስድስት በመቶ እድገት ያሳያል ተብሏል።

በተጨማሪም ጂቡቲ 5 በመቶ፣ ሶማሊያ 3.9 በመቶ፣ ደቡብ ሱዳን 6.5 በመቶ እንዲሁም ሱዳን 3.5 በመቶ እድገት ሊኖራቸው እንደሚችል ተተንብይዋል።

ባለፉት አስር ዓመታት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አስከ ሁለት አሃዝ የሚደርስ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ከሚጠቀሱ የአፍሪካ አገራት መካከል ውስጥ ቆይቷል።

በወቅቱ ምጣኔ ሀብቷ ድርቅና የብሔር ግጭቶችን የመሳሰሉ ጫናዎች ያጋጠሙት ሲሆን፣ አገሪቱ ለግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ የምታውለው እየናረ የሚሄድ የውጭ እዳ ችግር ሊያስከትል ይችላል በማለት ባለሙያዎች ሲያሳስቡ ነበር።

አይኤምኤፍ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ትንበያ ያላስቀመጠላቸው ሌሎቹ አገራት ግጭቶች ያሉባቸው አፍጋኒስታን፣ ሊቢያ እና ሶሪያ ናቸው።

የድርጅቱ ሪፖርት የዓለም ምጣኔ ሀብት እድገትን በተመለከተ በሰጠው ትንበያ ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት 2021 5.9 በመቶ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ግን 4.9 በመሆን ቅናሽ እንደሚያሳይ አመልክቷል።

አይኤምኤፍ ለእድገቱ መቀነስ የአቅርቦት መናጋት እና እየተባባሰ ያለው የወረርሽኝ ሁኔታ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ምጣኔ ሀብት ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ገልጿል።