በወለጋ የብሔር ግጭት እንዲከሰት እየሰሩ ያሉት አሸባሪው ሸኔና በዚያው አካባቢ ተደራጅቶ የሸፈተ ሌላ የአማርኛ ተናጋሪ ቡድን ናቸው – የኦሮሚያ ክልል

የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በጥቃቱ 15 ሰዎች መገደላቸውንና የጥቃቱ ፈፃሚዎች “የብሔር ግጭት እንዲከሰት እየሰሩ ያሉት አሸባሪው ሸኔና በዚያው አካባቢ ተደራጅቶ የሸፈተ ሌላ የአማርኛ ተናጋሪ ቡድን ናቸው” ብለዋል።
አክለውም ጥቃቱ አንድ ብሔር ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን ንፁሃንን ዒላማ ያደረገና የብሔር ማንነትን ያልለየ ነው ያሉም ሲሆን፤ የቢሮው ኃላፊ ምሽቱን ለኢቲቪ በሰጡት የስልክ መረጃ የክልሉ መንግሥት የተፈናቀሉ አባወራዎችን መልሶ የማቋቋምና አጥፊዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ ሥራን እየከወነ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ ሰላምን ለማምጣት በታጣቂዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን እንዲያጠናክሩ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውና ከአቻው ሕወሓት ጋር እንደሚሰራ ይፋ ያደረገው አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ኦሮሚያና ሌሎችም አካባቢዎች በንፁሃን ላይ ጥቃት ሲፈፅምና ሲያፈናቅል ከርሟል፡፡ መንግሥት በበኩሉ በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እየገለፀ ነው፡፡