ከታጣቂዎች ጋር የሚደረገው ስምምነት በደንብ ሊታሰብበት ይገበል – ፖለቲከኞች

ኢትዩ ኤፍ ኤም – ከታጣቂዎች ጋር የሚደረገው ስምምነት በደንብ ሊታሰብበት ይገበል አሉ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች

የኦሮሚያ መንግስት ከዚህ በፊት በትጥቅ ትግል ውስጥ ከነበሩ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች አመራሮች ጋር ስምምነት ማድረጉን እና ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደተመለሱ ማሳወቁ የሚታወስ ነው፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ከ14 ዓመት በላይ በደቡብ ዞን ግንባር የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ሲመሩ የነበሩት ግለሰብ ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሳቸውም በሰፊው ተዘግቧል ፡፡

አንድንድ ሰዎችም በአሸባሪነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር እንዴት መደራደር ይቻለል? የሚል ጥያቄን ሲያነሱ ሰንብተው ነበር፡፡

አቀባበል አደረጉ የተባሉት የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን ሌሉችም ቢመጡ እንቀበላለን ማለታቸው ብዙ አጨቃጭቋል ፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ደረጀ በቀለ ጉደታ ከኢትዩ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ በዚህ ጎዳይ ላይ እንደማይሰማሙ ገልጸው መጀመሪያውኑ እውነት በትጥቅ ትግሉ ላይ አሉ ወይ ? ምን ያህል ቁጥር ያለው ሰራዊት ከኋላቸው አለ? የሚለውም አጣርቶ ማወቅ ይገባል ብለዋል ፡፡

አቶ ደረጀ አክለውም ‹‹ሁሉም ታጋይ ነኝ እያለ የመጣውን ሁሉ ሆቴል ማስቀመጡ ትክክል አይደለም ይህ ቀልድ ነው ›› ይላሉ፡፡

የትኛውም ስምምነት ለህዝብ ይጠቅማል ከተባለ እውነተኛ ታጋይ ነው ብሎ ማጣራት ያስፈልጋል ነው የሚሉት ሊቀመንበሩ፡፡

‹‹ ከቦረናም ይመለስ ከወለጋም ይመለስ ..እንዴት ሊመጣ ቻለ? ..ለምን መጣ? ..እዚያስ ምን ነበር ? የሚለውን የክልሉ መንግስት በጥንቃቄ ማጥናት ይኖረበታል ›› ብለዋል፡፡

‹‹ የሚሄዱበት መንገድ አግባብ አለመሆኑን ተረድተው ወደ ሰላማዊ ትግሉ የተመሱትን ሰዎች ማክበር ይገባል›› የሚሉት ደግሞ የሰብአዊ መብት ታጋይ እና የህግ ባለሞያው አቶ ወንድሙ ኢብሳ ናቸው፡፡

አቶ ወንድሙ ‹‹ ከአሁን በኃላ የትጥቅ ትግል በኢትዮጵያ እንደማያዋጣ ከተገነዘቡ ፤ህዝቡም አባ ገዳዎችም ጭምር አምርረው እያወገዙ ስለሆነ ይህ የይቅርታ መንገድ ጥሩ ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ ፡፡

ከዚህ ቀደም የጉጂ እና የቦረና አባ ገዳዎች በኦሮሚያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው እና በርካታ ንጹሀንን የሚግድለውን በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ታጣቂው ቡድን ‹‹ሸኔ›› የኦሮሞ ጠላት ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡