በሕወሓት የተያዙ አካባቢዎችን ለማስለቀቅ መልሶ ማጥቃት ጀምረናል – የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና የሰሜን ወሎ ዞን ባለስልጣናት

May be an image of one or more people and roadሕወሓት በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የአማራ ክልል ኃይሎች መልሶ ማጥቃት እያደረጉ መሆኑን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና የሰሜን ወሎ ዞን ባለስልጣናት ገለጹ፡፡ ሕወሓት በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የመንግስት ጦር የመልሶ ማጥቃት ጦርነት መጀመሩን የሕወሓት ቃል አቃባይ ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የህወሓትን ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን ጠቅሶ ትናንት እንደዘገበው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የአማራ ክልል ኃይሎች በቅንጅት በሁሉም ግንባሮች በታጣቂዎቻቸው ላይ ጥቃት ከፍተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ አልሰጠም። አቶ ጌታቸው ለዜና ወኪሉ “በአማራ ክልል ወገል ጤና፣ ውርጌሳና ሐሮ በተባሉ አካባቢዎች ከምድርና ከአየር በሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች በሕወሓት ኃይሎች ላይ ጥቃት ተከፍቷል” ብለዋል ፡፡

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው የሕወሃት ቃል አቃባይ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የሚሰጡት መግለጫ «የተምታታ» እና «ማፌዝ» ነው በማለት ተናግረዋል ፡፡  በአማራ ክልል የዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ገብሬ ለዶይቼ ቬለ በስልክ እንደተናገሩት መንግስት በሕወሓት የተያዙ አካባቢዎችን ለማስለቀቅ ውጊያ ጀምሯል። “ጠላት” ባሉት የህወሓት ኃይል ላይም ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው ብለዋል፡፡

ቡድኑ የያዛቸውን አካባቢዎች በጦርነትም፣ ተስፋ በመቁረጥም ጥሎ እየሸሸ እንደሆነና የተስፋ ቆራጭነት ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን የአስተዳደርና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለማሪያም አምባዬ በበኩላቸው የሕወሓት ኃይል በሁሉም ግንባሮች በመልሶ ማጥቃት ውጊያ እየተመታ እንደሆነ ነው የተናገሩት። ነገር ግን የተጠቃለለ መረጃ ለመስጠት ጊዜው ገና መሆኑን አስረድተዋል። የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ከቀናት በፊት በቲውተር ገፃቸው “በአሸባሪው ትሕነግ (ሕወሓት) ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኘውን ሕዝባችን ነፃ ለማውጣት በሁሉም ግንባሮች የማያዳግም መልሶ ማጥቃት በየትኛውም ጊዜና ሰዓት ሊደረግ ስለሚችል ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀውን ለማድረግ በያለንበት 24 ሰዓት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል” ብለው ነበር፡፡ ከአማራ ክልል ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ DW