በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ እየተካሄዱ ያሉት ግጭቶችና ጥቃቶች ያሳስቡኛል – አሜሪካ

አሜሪካ በቅርቡ በአማራ ክልል ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ጨምሮ በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዳሳሰባት ገለጸች።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ባወጣው መግለጫ እንዳለው አሜሪካ በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ እየተካሄዱ ያሉት ግጭቶች በጽኑ እንደሚያሳስባትም ተናግራለች።

በቅርቡ በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኝ መንደር ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ጨምሮ በግጭቱ ተሳታፊ በሆኑ ሁሉም ወገኖች ስለሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችና ጭፍጫፋዎችን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች መውጣት መቀጠላቸው በጽኑ የሚረብሽ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

መግለጫው አክሎም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ እንዲህ አይነት ግፎችን አሜሪካ በሁሉም መልኩ አጥብቃ የምታወግዝ መሆኗን፣ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩና ለዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ተገዢ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው ግጭት ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ እንደማይሆንና ዘላቂ መፍትሄ ሊፈለግ እንደሚገባ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ሕብረት መሪዎች የቀረበውን ሐሳብ አሜሪካ እንደምትስማማበትም ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አክሎም የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ዘላቂ የተኩስ አቁም ለማድረግ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል።

እየተደራረቡ የመጡት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች በአስቸኳይ ገለልተኛና ተአማኒ የሆነ ዓለም አቀፍ ምርመራ የማድረግን አስፈላጊነት የሚያመለክቱ ናቸው ያለው መግለጫው፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች ለምርመራው አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ጠይቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን በትግራይ ውስጥ የተከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ በጋራ ሲያካሂዱት የነበረው ምርምራ ውጤት ይፋ መሆንን እንደሚከታተልም ጠቅሶ፤ የአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብቶች አካል ለሚያደርገው ምርመራ ሙሉ ትብብር እንዲደረግለት ጠይቋል።

በኢትዮጵያ እጅጉን አስፈላጊ ለሆነው ፖለቲካዊ እርቅና ሰላም ሲባል በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ እጃቸው ያለበትን ሰዎች ተጠያቂ ለማድረግ ግልጽና ነጻ የሆነ መንገድ ሊመቻች እንደሚገባም አሳስቧል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የሚደረገው ምርመራ የመስክ ሥራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በሚቀጥለው ሳምንትም ሁለቱም አካላት ሲያከናውኑት የነበረውን ሥራ በተመለከተ መግለጫ የሚሰጡ ሲሆን የምርመራቸው ውጤትም በጥቂት ወራት ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።