ትግል አይቆምም (ብለታ ታከለ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ትግል አይቆምም (ብለታ ታከለ)

ጀርመናዊያን ከናዚ ዘመነ መንግሥት በኋላ ራሳቸውን ለማደስ ብዙ ለፍተዋል፡፡ በነሒትለር የግፍ አገዛዝ ዘመን በአይሁዳዊያን፣ በጅብሲዎችና በሌሎች ሕዝቦች ላይ የደረሰውን መከራ በሚመለከት ብዙ ተጽፏል፤ ሰፊ ክርክርና ውይይትም ተደርጓል፡፡ የሚበዙት ጀርመናዊያን ያ ደርጊት መሆን ያልነበረበት ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ከቶም ሊደገም የማይገባው እኩይ ድርጊት ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡

ታላቁ ጀርመናዊ (አይሁዳዊ) ፈላስፋ ካርል ያስፐርስ “The Question of German Guilt” በሚለው ሥራው በዚያ በአይሁዶችና በጅብሲዎች ላይ በተፈፀመው የዘር ፍጅት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ ጀርመናዊያን ሁሉ በሞራል ደረጃ ጥፋተኞች ናቸው ይላል፡፡ በርካታ ጀርመናዊያን በእንዲህ ዓይነቱ አስተያየት ይስማማሉ፡፡ ስለሆነም በታሪክ መጻሕፍት ሳይቀር ስለዚያ ድርጊት እኩይነትና ነውረኝነት በግልጽ ተጽፎ ተማሪዎች እንዲማሩት ይደረጋል፡፡ እንደ ናዚ ፓርቲ ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ ወደፊት እንዲህ ዓይነት አዝማሚያ ያላቸው ፓርቲዎች ሥልጣን እንዳይዙ የሚያደርግ “militant democracy” የተሰኘ የፖለቲካ አሠራር ዘርግተዋል፡፡ የትኛውም አብላጫ ድምጽ አገኘሁ በሚል ስም አሁን ያለውን የሊብራል ዴሞክራቲክ መንግሥታዊ ሥርዓት አስወግዶ ጠቅላይ (totalitarian) አገዛዝ እመሠርታለሁ የሚል ኀይል ሥልጣን የሚይዝበት ዕድል እንዳይኖር ለፓርላማው፣ ለሥራ አስፈጻሚው አካል እና ለፍርድ ቤት ጠንካራ ሥልጣን የሚሰጥ አሠራር ነው፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣን ለመያዝ የሊብራል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን መቀበል ግዴታ ነው፡፡

የናዚ አገዛዝ ፍፁም ኢሰብአዊ ተግባራት በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ የፈጠረውን መጥፎ ገጽታ ለመቀየር ጀርመናዊያን አያሌ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ላለቁት አይሁዳዊያን መታሰቢያ የሚሆን ትልቅ ሙዚየም በርሊን ከተማ ላይ አቁመዋል፡፡ ቤተ መጻሕፍትና ሌሎች ልዩ ልዩ መታዎሻዎችም እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡ የሒትለር መጽሐፍ ጀርመን ውስጥ እንዳይታተምና እንዳይሰጥ ተከልክሏል፤ የናዚ አርማና ሰላምታም በጥብቅ የተከለከሉ ናቸው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከሁለት ተከፍላ የኖረችው ጀርመን ከሶሻሊስት ካምፑ መፈረካከስ ማግስት ወደ አንድነት መጥታ በአውሮፓ ግንባር ቀደም ኢኮኖሚ ከመገንባቷም በላይ በዴሞክራሲም ቀንዲል የሆነች አገር ሆናለች፡፡ ጀርመን ወደ ውስጧ በማየቷና ራሷን ኂስ በማድረጓ በጣም ብዙ ርቀት መራመድ ችላለች፡፡ ራስን የማየትን በረከት በጀርመን ተዓምራዊ ሊባል የሚችል የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግስጋሴ ማየት ይቻላል፡፡

የኢጣሊያ ሁኔታም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ ከፋሽስት አገዛዝ በኋላ ያለችው ኢጣሊያ ከፋሽዝም እስተምህሮና አስተሳሰብ እንድትፀዳ በርካታ ፋሽስቶች ለፈፀሙት ወንጀል ኀላፊነት እንዲወስዱና እንዲጠየቁ ተደርጓል፤ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል፡፡ ዋናዎቹ የድኅረ ፋሽዝም ኢጣሊያ መገለጫዎች ግን ዴሞክራሲ፣ ነጻነት፣ ሐቀኝነት፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት እና ዝመና የሚሉ ነበሩ፡፡ እነዚህ በተለምዶ “የፀረ ፋሽዝም ተጋድሎው ዕሴቶች” (values of the resistance) የሚባሉት ዕሴቶች ጎልተው እንዲወጡ እና ኅብረተሰቡ በዚህ መንፈስ እንዲታነፅ ብዙ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከመፈራረስ ወጥታ ተዓምራዊ ሊባል የሚችል የኢኮኖሚ ግስጋሴ ያሳየችው ድኅረ ፋሽስት ኢጣሊያ ከዚያ በኋላ፣ በተለይም በ1960ዎቹና 70ዎቹ በፖለቲካ መስክ ከፍ ያለ ውጣ ውረድና ምስቅልቅል ብታሳልፍም ተመልሳ ወደ አንድ ቡድን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ አልዘቀጠችም፡፡ ከነውስንነቱም ቢሆን የኢጣሊያ ዴሞክራሲ አሁንም አብነት ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ወደ ውስጥ መመልከትና ራስን ኂስ ማድረግ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ የኢጣሊያ ሁኔታም አስረጂ ነው፡፡

የሩዋንዳ የታሪክ ጉዞም ትልቅ ምሳሌነት ያለው ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከሚያዚያ 7 ቀን 1994 – ነሐሴ 1994 በሩዋንዳ የተካሄደው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ያለቁበት ዘግናኝ የዘር ፍጅት እንዲህ እንደዘበት የተፈፀመ አልነበረም፡፡ ዛሬ በአገራችን እንደሚታየው ዘውጋዊ ማንነት ዋናው የፖለቲካ ማደራጃና የሥልጣን መወጣጫ ሆኖ ከልክ በላይ ስለተቀሰቀሰ በጊዜ ሒደት በሩዋንዳዊያን መሀከል የእርስ በርስ መጠራጠር፣ ጥላቻና ግጭትን እየወለደ ቀጥሎ ወደ ዘርፍ ፍጅት የደረሰ ክስተት ነው፡፡

ሩዋንዳ ከዚያ ዘግናኝ እልቂት በኋላ ትልቅ ትምህርት ቀስማለች፡፡ በዚያ ዘግናኝ ድርጊት የተሳተፉ አካለት ተጠያቂ እንዲሆኑ ሠፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የእውነት እና የእርቅ ሥራም ተሠርቷል፤ ሒደቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ከፍጅቱ በኋላ በዚያች አገር በጎሳ ወይም በዘውጋዊ ማንነት መደራጀት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ ሩዋንዳዊያን ወደውስጣቸው ተመልክተው ራሳቸውን ኂስ አድርገዋል፡፡ እንዲያ ዓይነት ዘግናኝ እልቂት መቼም እንዳይደገም ከራሳቸውም አልፈው ለሌላው ዓለም እያስተማሩና ፍቅርን እየሰበኩ ይገኛሉ፡፡ ዛሬ አፍሪካዊቱ ሩዋንዳ በፖለቲካው መስክ ብዙ የሚቀራት ቢሆንም ፊቷን ወደ ልማት አዙራ እጅግ አመርቂ ግስጋሴ እያደረገች ትገኛለች።

ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ

ናንሲ ፊሊፕስ በደቡብ አፍሪካው የስትሊንቦሽ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ ናት፡፡ የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፏን በደቡብ አፍሪካንና የኢትዮጵያ “የፖለቲካ ሽግግር” ላይ የምትሠራው ናንሲ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመረዳት ፈታኝ እንደሆነባት ትገልጻለች፡፡

“የፖለቲካ ለውጥ ማለት ከአንድ ቡድን፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ግለሰብ (አምባገነን) አገዛዝ ወደ ሌላ ቡድን፣ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ግለሰብ አገዛዝ የሚደረግን የሥልጣን መቀያየር የሚያመለክት ሲሆን ሽግግር በአንጻሩ ከአንድ ኢዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ፣ ከአለመረጋጋት ወደ ሰላምና መረጋጋት፣ ከድህነት ወደ ልማት የሚደረግን የዝመናና የዕድገት ጉዞ የሚያሳይ ሒደት ነው፡፡ የአፓርታይድ ሥርዓት ተንኮታኩቶ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ በፕሬዚዳንትነት ከተመረጡ በኋላ ያለው የደቡብ አፍሪካ ሁኔታ ሽግግር ምን ማለት እንደሆነ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ከዚያን ጊዜ በኋላ በነጮችና በጥቁሮች መሀከል ያለው መረን የለቀቀ ልዩነትና ዘረኝነት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፤ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫዎች ይደረጋሉ፤ ዜጎች በመሰላቸው መንገድ በነጻነት የሚደራጁበት፣ ሐሳባቸውን የሚገልጹበት እና የሚሰበሰቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የሥራ መሪዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት ጠንካራ ሥርዓት ተገንብቷል፤ ወዘተ… በኢትዮጵያ በአንጻሩ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አይታይም፡፡ በድኅረ ኢሠፓም ይሁን ድኅረ ኢሕአዴግ ያለው ሁኔታ ሽግግር ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ በድኅረ ኢሠፓ የነበረው ለውጥ ሽግግርን እንዳላመጣ በግልጽ ታይቷል፡፡ ያሁኑ ለውጥም ቢሆን ወደ ሽግግር ለማደጉ የሚያሳዩ ምልክቶች የሉም” ትላለች ናንሲ፡፡

የኢሕአዴግ አገዛዝ ከሥርዓት ውስጥና ከውጭ በተደረገው ትግል መለወጡ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ የፈጠረ ለውጥ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በተለምዶ “የለውጥ ኀይል”፣ “ቲም ለማ” ወዘተ… እየተባለ የሚጠራው ቡድን ወደሥልጣን ሲመጣ የነበረው የደስታ እና የተስፋ ስሜት እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ለውጡን ተከትሎ በዚህች አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባበት ዕድል መጣ በሚል መንፈስ ብዙዎች ደስታቸውንና ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ መንፈስም ብዙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጓዛቸውን ጠቅልለው አገር ቤት ገብተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን እንደያዙ ባደረጉት ንግግር ያልተማረከ ኢትዮጵያዊ ነበር ማለት ከባድ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘመነ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያዊያን ላይ የተሠሩ ኢሰብአዊ ተግባራትን ኮንነው እንዲህ ዓይነት ደርጊት በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን እንደማይፈፀም ቃል ገብተው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተራራቀ አቋም ያላቸው የፖለቲካ ኀይሎች/ግለሰቦች ሊወከሉበት እንደሚገባ፣ እርሳቸውና መንግሥታቸውም ለዚህ እንደሚሠራ የእስራኤልን ፓርላማ (ክነሴት) እንደ አብነት እየጠቀሱ ተናገሩ፤ በዚህም ብዙዎች ተደሰቱ፡፡ ኢትዮጵያን ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ሊወስዱ የሚችሉ አንዳንድ ጅምር ተግባራትም ተሠሩ፡፡ ለምሳሌ ያህል በጠንካራ የሞራል ልዕልናቸውን የሚታወቁ ሰዎች በሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና በምርጫ ቦርድ አካባቢ በኀላፊነት ተመደቡ፡፡ ሌሎችም በጎ እርምጃዎች ተወሰዱ፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ በጎ ጅምሮችና ጥረቶች ከጅምሩ በሌሎች ትይይዩ አፍራሽ ተግባራትም የታጀቡ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል በከፍተኛ ደረጃ ሲወገዝ የነበረውና ትልቅ እሮሮ ፈጥሮ የነበረው ሙስና ተጠናክሮ መቀጠሉ፣ ሕዝብ ያማረሩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተጠያቂ መሆን ሲገባቸው አሁንም ከአንዱ የኀላፊነት ቦታ እየተነሱ ወደሌላው የሚገለባበጡበት አሠራር አለመቆሙ፣ ብሔር ተኮር የሆነ የመሬት እና የመንግሥት ሥራ ወረራ መቀጠሉ፣ ሳናጣራ አናስርም በተባለ ማግስት ብዙ ሰዎች በገፍ የሚታሰሩበት አሠራር አለመሻሻሉ፣ በገዥውና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መሀከል ያለው ግንኙነት አሁንም ጤናማ አለመሆኑ፣ ከሥርዓታትና ተቋማት ግንባታ ይልቅ አሁንም በእሳት ማጥፋትና በዘመቻ ተግባር መጠመዱ ወዘተ… የሚያስገነዝቡት ኢትዮጵያ የሽግግሩን መንገድ ገና እንዳልጀመረችው ነው፡፡

ጉዞው ቀላል አይሆንም

አሜሪካዊው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ጃክ ሺናይደር “From Voting to Violence: Democratization and Nationalist Conflict” በሚለው መጽሐፉ በስፋት እንደገለጸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ባለ ብዙ ብሔረሰብና ሃይማኖት አገሮች ውስጥ፣ በተለይም ብሔረሰባዊና ሃይማኖታዊ ማንነት እንደማደራጃ ጥቅም ላይ በሚውልበት የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ ለውጥ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር የማድረጉ ነገር ፈታኝ ነው፡፡ እንደ ፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ገለጻ ግጭት የሚበረክተው እና ብዙ ሰዎች የሚሞቱት በአምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ሳይሆን ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር በሚያደርጉ አገሮች ውስጥ ነው፡፡ ሺናይደር እንደሚለው ለግጭቱ መጨመር ምክንያቱ ማንነት ተኮር ቅስቀሳዎችና አደረጃጀቶች በነጻነትና በግላጭ ሲደረጉ ሌላው ብሔረሰብ ወይም የሃይማኖት ተከታይ በበኩሉ እነዚያ (ሌሎች) እየተደራጁ ነው የሚል እምነት በመያዝ ራሱን ወደማደራጀት ይሄዳል፡፡ ሁሉም የየራሱ ሚዲያ፣ የየራሱ ሲቪክና የፖለቲካ ድርጅት ያቋቁማል፡፡ በሚዲያዎች አማካይነት ግልጽ በሆነ መልኩ ተቃራኒ እና የሚጠፋፉ የታሪክና የፖለቲካ ትርክቶች ለአድማጭና ተመልካች ይሰራጫሉ፡፡ በጊዜ ሒደት አንዱ ስለሌላው መስማት ያቆምና ሁሉም “የየራሱን እውነት” ብቻ ወደ ማድመጥ ይሄዳል፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ የተገነባ ማንነት ለግጭት በጣም ቅርብ ነው፡፡

“የኢትዮጵያ ሁኔታ ከደቡብ አፍሪካ ይልቅ ለዩጎዝላቪያ ይቀርባል” የምትለው ናንሲ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ብሔረሰብ ለሌላው ያለው አመለካከት በእጅጉ የተዛባ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ድኅረ አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ወደ እርቅና ሰላም ስትሄድ ድኅረ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ግን ይበልጥ ወደ መራራቅ እያመራች መሆኑን ትገልጻለች ናንሲ፡፡
ዶ/ር ዳምጠው ተፈራ በበኩላቸው “ጉዞው ቀላል ባይሆንም ኢትዮጵያ ወደ ትክክለኛው ትራክ ተመልሳ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የምትችልበት ዕድል ዝግ አይደለም” ይላሉ፡፡ ግን እንዴት?

“እዚህ ላይ፣ በኅብረተሰባዊ ለውጥ ላይ መዋቅር (Structure) እና ግለሰብ/ወኪል (Agency) ያላቸውን ሚና በሚገባ ማጤን ይገባል፡፡ ብሔረሰብ ተኮር የሆነ አስተሳሰብና ፖለቲካ ወይም በጥቅሉ ማንነትን (የብሔረሰብና የሃይማኖት) መሠረት ያደረገ ፖለቲካ በዚህች አገር ማዕከላዊ ቦታ ይዞ ቆይቷል፡፡ በዚህና በሌሎች ታሪካዊ ምክንያቶች በልኂቃኑ መሀከል ያለው ግንኙነት ጤናማ አይደለም፡፡ ጥርጣሬ አለ፤ ክፍፍል አለ፡፡ ኢኮኖሚያዊ አቅማችን በጣም ደካማ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ መዋቅራዊ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መዋቅራዊ ችግሮች አንዱ ከሌላው ጋር እየተመጋገቡ ወደፊት እንዳንንቀሳቀስ አስረው ይዘውናል፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ነገራችን ያበቃለት ነው ማለት አይደለም፡፡ ግለሰቦችም ትልቅ የለውጥ ኀይል የሚሆኑበት ዕድል አለ፡፡ በዓለም ላይ ታሪክ የሠሩ፣ አገርና ሕዝብን ወደፊት ያራመዱ መሪዎች አሉ፡፡ ኔልሰን ማንዴላን ከደቡብ አፍሪካ፣ ጀሪ ሮውሊንግስን ከጋና፣ ኦባሳንጆን ከናይጀሪያ ወዘተ… መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለሆነም በእኛም ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ጓዶቻቸው ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ በማሻገር ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ሚና መጫወት ይችላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ግለሰቦች በገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥም እንዳሉ ይሰማኛል” ይላሉ ዶ/ር ዳምጠው፡

ከግለሰቦች ይልቅ በኅብረተሰቡ (መዋቅሩ) ላይ ማተኮር እንደሚገባ እና እሱን ማስተካከል እንደሚቻል የምትናገረው ናንሲ በበኩሏ ለዚህ ግን አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በበቂ ሁኔታ መረዳት እንደሚያስፈልግ ትናገራለች፡፡ በኢትዮጵያዊያን መሀከል ያለው የእርስ በርስ መጠራጠርና ክፍፍል እንዲቀንስ በጣም ብዙ የሰላም አርበኞች እንደሚያስፈልጉ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እንቅልፍ አጥተው ተስፋ ሳይቆርጡ ሊሠሩ እንደሚገባ፣ በኬንያና በደቡብ አፍሪካ እንደታየው ሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሚዲያው በጋራ በሰላም፣ በፍቅርና በአብሮነት ጉዳዮች ላይ አብክረው መሥራት እንደሚገባቸው ትናገራለች፡፡

“በፕሬዚዳንት ኪባኪና በራይላ ኦዲንጋ መሀከል፤ በኋላም በፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና በጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ መሀከል የተከሰተውን አለመግባባት ተከትሎ በኬንያ የተቀሰቀሰው ግጭት የቆመውና ዘላቂ መፍትሔ የተበጀለት በሲቪክ ማኅበራት፣ በሃይማኖት ተቋማት እና በሚዲያው የጋራ ያላሰለሰ ጥረት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ በኩል በኢትዮጵያም ሰፊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል” ስትል ትመክራለች ናንሲ፡፡

(ብለታ ታከለ)  ሲራራ – Sirara