አዲስ አበባ የደህንነት ስጋት እንዳለባት በማስመሰል የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ አንቂዎች ከድርጊታቸው ይቆጠቡ – ፖሊስ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በአዲስ አበባ ከተማ በከባድ ወንጀሎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ 34 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ከተማዋ የደህንነት ስጋት እንዳለባት በማስመሰል የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ አንቂዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽም በመዲናዋ ወቅታዊ ሠላምና ደህንነት እንዲሁም በኮቪድ-19 ፕሮቶኮል አተገባበር ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ፖሊስ በቁጥጥር ስር ባዋላቸው የወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ባደረገው ጥልቅ ምርመራ 12 ተሽከርካሪዎች ቴሌቪዥንና ኮምፒውተሮችን መያዙን ተናግረዋል።

የፖሊስ ተልዕኮ ሕዝብን መጠበቅና በሠብዓዊነት ማገልግል ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ፖሊስ የወንጀል ድርጊት ፈፃሚዎች ላይ ባደረገው ምርመራ 34 ተጠርጣሪዎችን ከዘረፉት ንብረት ጋር በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል ብለዋል።

በከባድ ወንጀሎች ላይ ተሰማርተው የተገኙት ተጠርጣሪዎቹ በቡድን በጦር መሳሪያ በመታገዝ ትላልቅ ተቋማትና ድርጅቶችን ሲዘርፉና የድብደባ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተደራጀ መንገድ በዘረፋ ተግባር የተሰማሩት ተጠርጣሪዎቹ ውድ እቃዎችና ገንዘብ ያለበትን የሚያጠና፣ ጊዜና ቦታ አመቻችቶ የሚዘርፍና የዘረፈውን የሚሸጥ ሶስት ቡድን እንዳላቸው ደርሰንበታል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ከተማዋ የደህንነት ስጋት እንዳለባት በማስመሰል የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ አንቂዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ይህን ተላልፈው ከተገኙ ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለንም ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ የሚካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ ከ4 ሺህ 180 በላይ አዲስ ምልምል ፖሊሶች ኮሚሽኑን መቀላቀላቸውን በመግለፅ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚሞክሩ ካሉ አደብ ለማስያዝ በቂ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት።

በመዲናዋ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ማጭበርበር ወንጀሎች መሰማራታቸውን ደርሰንበታል ያሉት ኮሚሽነር ጌቱ ለፍርድ ቀርበው በማረሚያ ቤት የሚገኙ መኖራቸውን አረጋግጠዋል።

በቀጣይም በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት እንዳይሳተፉ ለመከላከል በሚያርፉባቸው ሆቴሎችና እንቅስቃሴ በሚያደርጉባቸው አካባቢዎች የፖሊስ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ የኅብረተሰቡ መዘናጋት ‘አሳስቦኛል’ ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን በማይተገብሩ ግለሰቦች ላይም እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን