ጂጂጋና ሻሸመኔ እንደ ድሬዳዋ ለጊዜው ቻርተር ከተማ መሆናቸው አስፈላጊ ነው #ግርማ ካሳ

በዚህ ሳምንት በጂጂጋና በርካታ የሶማሌ ክልል ከተሞች ሶማሌ ባልሆኑ ኢትዮጵያዉያን ላይ አሰቃቂ ተግባራት ተፈጽመዋል።ከመቶ በላይ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ጂጂጋ ከተማ ብቻ ከሃያ ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቅለዋል። ከሰባት በላይ አብያት ከርስቲያናት ተቃጥለዋል። በተወሰኑ አብያት ክርስቲያናት ቄሾችና መነኮሳትም አብረው የተቃጠሉበት ሁኔታ ነው ያለው። የክልሉ ፕሪዜዳንት አብዲ ኢሌ ታስሯል የሚባል ወሬ ቢናፈስም፣ አቶ አብዲ በርግጥ የት እንዳለ የሚገልጽ ትክክለኛ መረጃ የለም። በደቡብ ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል በላይ ስዩም የሚመራ ከመከላከያ ሃይል፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል የተወጣጣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ክልሉን ለማረጋጋት እየሞከረ እንደሆነ ሰምተናል።

የሶማሌ ክልል ባለቤት በክልሉ ሕገ መንግስት መሰረት የሶማሌ ማህበረሰብ ነው። ሌልች ማህበረሰባት በሶማሌዎች ፍቃድ የሚኖሩ እንግዶች ናቸው። ባለአገር ሳይሆን መጤዎች እንደሆኑ ነው በሕግ የተቀመጠው። የሶማሌ አክራሪዎች በሌሎች ማህበረሰባት ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ያበረታታቸው ይኽው በህገ መንግስታቸው የመሬቱ ባለቤት ነን የሚለው አመላከከት፣ የዘር ፖለቲካውና የዘር ሕግጋቶች መሆናቸው አሌ የማይባልለት ሃቅ ነው።

በጂጂጋ በሆነው አሳዛኝ ክስተት ሀዘናችንን ሳንጨርስ ፣ በሰላማዊቷ፣ ብዙ ከተሞችን በምታገናኘዋ፣ ታላቋ የንግድ ከተማ ሻሸመኔ አንገት የሚያስደፋ አረመኒያዊ ጉድ አየን።
በሻሸምኔ፣ ከሻሸመኔ ዙሪያ፣ ከኮፈሌ ከአዳባ ከመሳሰሉ አካባቢዎች የመጡ በርካታ ወጣቶች፣ በሻሸመኔ ካሉ ቄሮዎች ጋር በመሆን ለጃዋር አቀባበል ለማድረግ በተሰበሰቡበት ወቅት ነው ቦምብ ሊፈነዳ ነው ተብሎ፣ ባልተረጋገጠ ወሬ፣ ሰላማዊ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ላይ ለሻሸመኔ ታሪክ ትልቅ ጠባሳ የሚሆን አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙት።

በሰው ልጅ ላይ ያን አይነት ድርጊት ሲፈጸም፣ ያጨበጭብ፣ “ሆ” ይል የነበረውና ይመለከት የነበረው ሰው ብዛት ቀላል አልነበረም። አንድ ሰው ያንን አረመኔያዊ ድርጊት ለማስቆም አለመሞኮሩ እንደ ማህበረሰብ ምን ያህል የአስተሳሰብና የሞራል ወድቀት ውስጥ እንደገባን የሚያመለከት ነው።

ከዚህ በኋላ በሻሸመኔና በጂጂጋ የሚኖሩ ወገኖች እንዴት ብለው ተረጋግተው ሊኖሩ እንደሚችሉ አይገባኝም። የኦሮሞ ክልል መንግስት ሊጠብቃቸው አልቻለም። የሶማሌ ክልል መንግስት ሊጠበቃቸው አልቻለም። ለህይወታቸው፣ ለኑሯቸው ምንም አይነት ዋስትና የላቸው። እርግጥ ነው የኦሮሞ ክልል መንግስት በቃላት በመግለጫ ኦሮሚያ የሁሉም ናት ሲሉን ወራት አልፏቸዋል። ግን ሜዳ ላይ እየሆነ ያለው የተለየ ሁኔታ ነው። በኦሮሞ ክልል መንግስት ወይንም በሻሸመኔ ከንቲባ ተማምኖና ተረጋግቶ መኖር የሚችል፣ ከሌላው ማህበረሰብ የሆነ ዜጋ ሊኖር አይችልም።

በጂጂጋም የአብዲ ኢሌ ቀኝ እጅ የነበረ ፣ አብዲ ኤሊን ተክቶ የክልሉ ፕሬዘዳንት ሆኗል። አሀመድ ሺዴ አብዲ ኢሊን ተክቶ የሶደፓ መሪ ሆኗል ። በጂጂጋ የሚኖሩ የሌሎች ማህበረሰባት አባላት አብዲ ኢሌን የተኩ ባለስልጣናትን አምነው ተረጋግተው ይኖራሉ ማለት አስቸጋሪ ነው። በጭራሽ ሕልዉናቸውን ሊያረጋግጡላቸው አይችሉም። በጭራሽ። ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ነው።

ከሃያ ሺህ በላይ የጅጅጋ ነዋሪዎች ወደ ጂጂጋ ተመልሰው በሰላም ኑሯቸውን እንዲኖሩ ካስፈለገ ፣ በሻሸመኔ ያሉ የሌሎች ማህበረሰብ አባላት እንዲረጋጉ፣ ሻሸመኔም የንግድ ቀጠና ፣ ጂጂጋም ወደ በርበራ የሚወስደው መስመር ላይ ያለች ቁልፍ ታሪካዊ ከተማ እንደመሆኗ አስተማማኝ መረጋጋት እስኪፈጠር ድረስ፣ ሻሸመኔና ጂጂጋ የፌዴራል ሻርተር ከተማ እንዲሆኑ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

በከተሞቹ፣ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የአገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት ተቋቁሞ፣ አዳዲስ ከንቲባዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመው፣ ከንቲባዎቹ ከሽማግሌዎች ጋር እየተመካከሩ እንዲሰሩ በማድረግ የተፈጠረው ቁስል፣ ጠባሳዉን ማጥፋት ባይችልም፣ ቶሎ እንዲድን ማድረግ ይቻላል። በጂጂጋ አማርኛና ሶማሌኛ ፣ በሻሸመኔ ደግሞ ኦሮምኛና አማርኛ የከተሞቹ የስራ ቋንቋ ሊደረጉ ይችላሉ።

አገር እንድትበጠበጥ የሚፈልጉ ሕወሃቶች ዶ/ር አብይ ይሄን በማድረጋቸው ተቃዉሞ ሊያሰሙ ይችላሉ። “ሕገ መንግስቱን አብይ አፈረሰ” ብለው። ሆኖም የነርሱ መሪ መለስ ዜናዊ መረጋጋት ስላልነበረ ፣ ድሬዳዋ ቻርተር ከተማ እንድትሆን ማድረጉን ላስታወሳቸው እፈልጋለሁ። ደግሞም በጂጂጋም ሆነ በሻሸመኔ አደጋ ላይ ያሉት የትግራይ ተወላጆችም መሆናቸው መዘንጋት የለባቸውም።

የሶማሌና የኦሮሞ ብሄረተኛ አክራሪዎችም ጉዳዩን ከስብእና ከሰላም፣ ከመረጋጋት፣ ከከተሞቹ ብልጽግ አንጻር ሳይሆን፣ ጠበው ከዘር አንጻር በማየት ተቃዉሞ ሊያሰሙ ይችላሉ። ሆኖም ግን ዶ/ር አብይ ለነዚህ የኋላ ቀር የበታችነት ስሜት ለሚሰማቸው ደካሞች ቦታ ይሰጣሉ ብዩ አላስብም። ዶ/ር አብይ ለእያንዳንዱ ዜጋ ደህንነት ሃላፊነት እንዳለው መርሳት የለበትም። ዜጎች እየፈሩ፣ እየተሸማቀቁ እንዲኖሩ መፍር የለበትም። የአገር ችግር በቀላሉ መፋታት ባይቻልም፤ ቢያንስ በትንሹ መጀመር ይቻላል። ጂጂጋና ሻሸመኔ ላይ።

ሰላማዊ፣ እንደገና ፍቅር የሰፈነባት ጂጂጋ ስትኖር፣ በጂጂጋ ነዋሪ የሆነውም ሶማሌው ነው የሚጠቀመው። ሰላም ፍቅር መረጋጋት አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ሻሸመኔ ከማንም በላይ የምትጠቅመው ራሱን የኦሮሞን ማህበረሰብ ነው።