ግጭቱን ማስቆም ያለበት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አይደለም – አሜሪካ

DW : በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት አመራር መካከል ትግራይ ውስጥ ያለው ግጭት የሚያበቃውም በኹለቱ ኃይላት መኾኑን አሜሪካ ገለጠች። የሰላማዊ ሰዎች ደኅንነት መጠበቊ ወሳኝ እንደኾነ፤ በዋናነትም የዜጎቿን ደኅንነት ለማስጠበቅ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሳለች። ትናንት ማምሻውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪቃ ጉዳዮች ረዳት ሚንስትር ቲቦር ናዥ እና በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሚካኤል ራይኖር ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ኹኔታ በስልክ ኮንፈረንስ ለጋዜጠኞች በሰጡት ልዩ ማብራሪያ ወቅት ነበር ይኽንኑ የተናገሩት።

Äthiopien Stellv. US-Außenminister für afrikanische Angelegenheiten Tibor P. Nagy በማብራሪያው ወቅትም፦ «የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ግጭቱ ፍጻሜ እንዲያገኝ፤ ሰላም እንዲሰፍን፤ ሰላማዊ ሰዎች መጠበቃቸውን ለማሳሰብ የተቻለውን ጥረት ያደርጋል» ያሉት ቲቦር ናዥ፦ «ግጭቱን ማስቆም ያለበት ግን የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አይደለም» ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል። «ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ፤ ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ላይ የመጀመሪያውን ጥቃት ከሰነዘረበት ጊዜ አንስቶም በግልም፣ በይፋም እጅግ እንዳሳሰበን አጽንዖት ሰጥተንበታል» ሲሉም አክለዋል። ሰላማዊ ሰዎች ሆነ ተብሎ ዒላማ ውስጥ እንዲገቡና ጥቃት እንዲፈጸምባቸው ስለመደረጉ የወጡ ዘገባዎች አኹንም በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው ገልጠዋል። በማይ ካድራ ለተፈጸመው ጭፍጨፋ ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀርቡም በድጋሚ ጠይቀዋል። የማይ ካድራውን ጭፍጨፋም አውግዘዋል።

ድርጊቱ የተፈጸመው ከተማዪቱን ለቀው በሚያፈገፍጉ የሕወሓት ወታደሮች እና ሚሊሺያዎች እንደኾነ ያመላክታል» ያሉት ቲቦር ናዥ፦«የሰብአዊ መብት ጥሰቶች» በመላ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ አሳስበዋል። ጥፋተኛ ኾነው የተገኙትም በሕግ አግባብ እንዲጠየቊ ጥሪ አስለላልፈዋል።

  በተለይ አንዳንድ የውጭ ሃገራት ተንታኞች እና ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ እንደሚገልጡት በትግራይ የተጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ ቃጣናው ላይ ተጽእኖ ይኖረው እንደኾነም የተጠየቊት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪቃ ጉዳዮች ረዳት ሚንስትር ቲቦር ናዥ ስለኢትዮጵያ ጥንታዊ መንግሥትነት እና ነፃ ሀገር መኾን በማብራራት የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሚናን ጠቅሰዋል። «ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ የቃጣናው አነቃቂ ኾናለች» ብለዋል። «ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የኹለት ሺህ ዓመት የመንግሥት ታሪክ ያላት ናት። ከሰሃራ በታችም ፈጽሞ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ ሀገር ናት» ሲሉም ተናግረዋል።

ሕወሓት ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ሚሳይሎችን አስወንጭፎ ግጭቱን ቃጣናዊ ለማድረግ ቢሞክርም ኤርትራ ከግጭት ራሷን መቆጠቧን ቲቦር ናዥ አወድሰዋል። «ከሕወሓት አመራር ዓላማዎች መካከል አንዱ ግጭቱን ቃጣናዊ ለማድረግ መሞከር ነበር» ያሉት ረዳት ሚንሥትሩ፦«በትግራይ አጠቃላይ ሕዝብ ዘንድ የጀብደንነት ነበልባልን ለመለኮስ» የተሞከረ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ቲቦር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባደረጉት ውይይት መንግሥት ዋነኛ ግቡ በመቶ ሺህ የሚቆጠር አባል ካለው ሕወሓት ውስጥ አመራሩ ላይ መኾኑን አጽንዖት መስጠቱን አስምረውበታል።

አምባሳደር ሚካኤል ራይኖር በበኩላቸው ቲቦር ናዥ በተናገሩት እንደሚስማሙ ገልጠዋል። የሕወሓት ፍላጎትን በተመለከተ፦ «ፍላጎታቸውን በትክክል ማወቅ ባይቻልም ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድን አስወግዶ ላለፉት 27 ዓመታት የበላይ ወደ ኾኑበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ለመመለስ ያለመ ይመስላል» ያሉት ቲቦር ናዥ፦ የህወሃት ስልት ተቃራኒ ነገር እንዳስከተለ ጠቅሰዋል። የሕወሓት ድርጊት፦ «ቢያንስ አሁን ጠቅላይ ሚንሥትሩን በመደገፍ ኢትዮጵያውያንን እንደ ሀገር ያሰባሰበ ይመስላል» ብለዋል። ኹኔታው፦ «የኢትዮጵያ ብሔራዊነትን በእውነቱ አስደንግጧል» ሲሉም አክለዋል። አምባሳደር ሚካኤል ራይኖር በኹኑ ወቅት «የክልል እና የፌዴራል መንግሥታት እንዲሁም መጠነ ሰፊ ሕዝብ በመንገስት ዙሪያ መሰባሰቡንም» ተናግረዋል።