ከ45 ሀገራት የተውጣጡ 70 ወታደራዊ አታሼዎች በመኮንኖች ክበብ ተሰበሰቡ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር ቀነዓ ያደታ ፣ ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ ለሆኑ ወታደራዊ አታሼዎች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጡ ።በመኮንኖች ክበብ በተካሄደው በዚሁ መድረክ ላይ ፣ ከ 45 ሀገራት የተውጣጡ 70 ወታደራዊ አታሼዎች ተሳትፈዋል ።
ሚኒስትሩ ፣ በኢትዮጵያ ፣ ግፈኛው የህወሐት ቡድን የብሔር ግጭቶች ማስነሳቱን ፣ ብዙ ህዝብ እንዲጨፈጨፍ ማድረጉን ፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መጣሱን ፣ ጦርነቱንም ራሱ ሰሜን እዝን በማጥቃት እንደጀመረው እና ኢትዮጵያም የህግ የበላይነት እያስከበረች መሆንዋን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አብራርተዋል ።
በውይይቱ ላይ ፣ የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌ/ጀ አስራት ዴኔሮ ፣ ጁንታው ህገ መንግስቱን ጥሶ የፈፀመውን ግድያ ፣ ከሀዲው የሰላም መንገድን ረግጦ ሰሜን እዝን በመውረር ግጭቱን እንዴት እንደ ጀመረው ፣ እያሰራጨ ስላለው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም የፌዴራል መንግስት ህግን ለማስከበር እያደረገ ስላለው ጥረት በዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል ።
አንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ ፣ በውጭ ጣልቃ ገብነትና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላነሱት ጥያቄ የመከላከያ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል ።ዶ/ር ቀነዓ ፣ ነጻ በወጡ አካባቢዎች መንግስት የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ፣ ኢትዮጵያ የውጭ ድጋፍ የምትፈልግበት ምንም ምክንያት እንደሌለ እንዲሁም ሠራዊታችን የጦርነት ህግና የአለም ዓቀፍ ህግን እንደሚያከብር አረጋግጠዋል ።