መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ነው – የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት

DW : የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ “መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ እየተፈጠረ እንደሆነ” አስጠነቀቀ። እስከ ዛሬ ማክሰኞ ሕዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 27,000 ሰዎች ውጊያ ሸሽተው ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን አስታውቋል።

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ባባር ባሎች እንዳሉት በቀን ወደ አራት ሺሕ ገደማ ሰዎች ውጊያ ሸሽተው ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ነው።

ባሎች “ውጊያ የሚሸሹ ስደተኞች ከረዥም የእግር ጉዞ በኋላ ተዳክመው ጥቂት ንብረቶቻቸውን እንደያዙ እየደረሱ ነው” ሲሉ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

“በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሚካሔደውን ውጊያ በመሸሽ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሱዳን እየተሰደዱ በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ እየተፈጠረ መሆኑን ያስጠነቅቃል” ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ባባር ባሎች ተናግረዋል።

“ፍጥነቱ ከፍተኛ ነው” ያሉት ባሎች ሱዳን ከዚህ ቀደም “በዚህ የአገሪቱ ክፍል ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያልታየ መጥለቅለቅ” እንደገጠማት አስረድተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ቃል-አቀባይ የንስ ላርከ “በትግራይ ውስጥ ከፍተኛ መፈናቀል ሊኖር ይችላል። ያ ደግሞ አሳሳቢ ነው። በተቻለ መጠን ለመዘጋጀት እንሞክራለን” ብለዋል።