ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ያለው ችግር ሞልቶ የፈሰሰ ነው ገዳዮች የሥራቸውን መቅመስ አለባቸው – የአማራ ክልል መንግሥት


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


  • “ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ያለው ችግር ሞልቶ የፈሰሰ ነው፡፡” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
  •  በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል በንጹኃን ላይ የሚፈጸም ግድያ እንዲቆም የአማራ ክልል መንግሥት አሳሰበ፡፡
(አብመድ) – የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን አስመልክቶ በተደጋጋሚ በሰጣቸው መግለጫዎች ችግሩ በድጋሜ እንዳይከሰት ማሳሰቡን የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ አስታውሰዋል፡፡ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በለውጥ ሂደት ውስጥ ችግር እንደሚያጋጥምም አብራርተዋል፡፡
ለውጡን የሚደግፍና የሚቃወም ቡድን በሁለት ጎራ ተሰልፎ እየታገለ መሆኑን በማንሳትም ቀጣይም ሊያጋጥም እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ የለውጡ ኃይል አሸንፎ ሰላም ሲፈጠር ነገሮች ጥሩ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ “ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ያለው ችግር ግን ሞልቶ የፈሰሰ ነው” ብለዋል፡፡ በአካባቢው ግጭት እንዲነሳ የሚያደርጉ ኃይሎች ፍላጎት ከታየው በላይ እንደነበርም አቶ ግዛቸው ገልጸዋል፡፡ መተከል ላይ የእርስ በርስ ግጭት እንዲቀሰቀስ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን በማንሳትም መንግሥት በመሥራቱ ችግሩን መቀነስ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ቀጣይ ግን ተግባራዊ ሥራ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማደራጀት እንደሚያስፈልግ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የክልሉም አቋም መሆኑን ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡
ለዚህም ከፌዴራል እና ከቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥታት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ችግሩ ክልሉ መታገስ ከሚችለው በላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛቸው ከዚህ በላይ የሰው ሞት እና እንግልት መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
“ገዳዮች የሥራቸውን መቅመስ አለባቸው” በማለትም የክልሉ መንግሥት ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ የራሱን ሥራ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡