በትግራይ የአንበጣ መንጋው ላይ የኬሚካል ርጭት እንዲደረግ የፍቃደኝነት ችግር ስላለ እስካሁን አልተካሄደም


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


  • የትግራይ ክልል በበኩሉ ከግብርና ሚኒስቴር የኬሚካል እርጭት የሚካሄድባቸውን ስፍራዎች ለይተው እንዲያሳውቁ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ለቢቢሲ አረጋግጧል።
  • የገበሬው ምርት ከፖለቲካ የተለየ ነገር ነው።

BBC Amharic : የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ የአንበጣ መንጋው ላይ የኬሚካል ርጭት ለማድረግ አስፈላጊ መረጃዎችን ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ በትግራይ ክልል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል እርጭት ማካሄድ አለመቻሉን የግብርና ሚንስቴር አስታወቀ።

በግብርና ሚንስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበራ ለማ ለቢቢሲ እንደገጹት፤ የአንበጣ መንጋውን ለመዋጋት ሚኒስቴሩ አውሮፕላኖችን ጨምሮ የአንበጣ መከላከያ መሳሪያዎችን ቢያዘጋጅም “የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮም ይሁን እስከ ወረዳ ያሉት መዋቅሮች የአንበጣውን መገኛ አሳውቆ እርጭት እንዲደረግ የፍቃደኝነት ችግር ስላለ እስካሁን ርጭት አልተካሄደም” ሲሉ ትናንት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አበራ አሁንም ቢሆን ከክልሉ ወረዳዎች ጋር በስልክ እየተገናኙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የአንበጣ መንጋው የተከሰተበትን ቦታ ለይተው የሚያሳወቁ ከሆነ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

የገበሬው ምርት ከፖለቲካ የተለየ ነገር ነው ያሉት የሕዝብ ግነኙነት ዳይሬክተሩ “ፋይዳውን አይተው፤ ለሕብረተሰቡ አስበው” መረጃውን የሚሰጡ ከሆነ የፌደራል መንግሥት የኬሚካል ርጭቱን ለማካሄድ ዝግጅቱም ሆነ ፍላጎቱ አለው ብለዋል።

የትግራይ ክልል በበኩሉ ከግብርና ሚኒስቴር የኬሚካል እርጭት የሚካሄድባቸውን ስፍራዎች ለይተው እንዲያሳውቁ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ለቢቢሲ አረጋግጧል።

በትግራይ ክልል የእርሻና ገጠር ልማት ቢሮ የተምች መከላከልና ቁጥጥር፣ የዕፅዋት ኳራንታይን ዳይሬክተር አቶ መብራህቶም ገብረኪዳን “የግብርና ሚንስቴር በአውሮፕላን አማካኝነት የኬሚካል እርጭት ለማካሄድ እንደሚረዱን ገልጸውልናል” ይላሉ።

አቶ መብራህቶም “አውሮፕላን እንዲልኩና የሚረጭበት አካባቢ እንድናሳውቃቸው በነገሩን መሠረት ስምምነት ላይ ደርሰናል፤ ቢሆንም ግን እምነት የለንም” ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ “ከዚህ ቀደም በአውሮፕላን የኬሚካል እርጭት እናካሂዳለን ተብሎ ከግብርና ሚንስቴር እንድንዘጋጅ ተነግሮን ብንጠብቅም ዋጃ አጠገብ ድንበር ላይ ረጭተው ተምልሰዋል” በማለት ቀደም ሲል የነበረውን ሁኔታ ጠቅሰዋል።

አቶ መብራህቶም እንደሚሉት ከሆነ “አውሮፕላን የትም ቦታ ኬሚካል አይረጭም። ለምሳሌ በመንደር ውስጥ፣ ውሃ ላይ እንዲሁም ተራራማና ሸለቆ ውስጥ መርጨት የለበትም ወይም ለመርጨት አይመቸውም።”

አቶ መብራህቶም ጨምረውም “የግብር ሚኒስቴር ቢያግዘን ጥሩ ነው ካልሆነም በራሳችን እንሰራዋለን” ይላሉ።

የግብርና ሚንስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበራ ለማ በበኩላቸው “መጠንቀቅ ያለባቸው ለአርሶ አደሩ ሰብል ነው። ለአርሶ አደሩ ካሰቡ ኮኦርዲኔቶቹን [የአንበጣ መንጋው ሚገኝበት ትክክለኛ ስፍራን በካርታ ላይ የሚገኙ አመላካቾች] ሰጥተው ለርጭት ቢያዘጋጁ ጥሩ ነው” ብለዋል።

“ለትግራይ፣ ለአማራ፣ ለአፋር ብለን አንለይም። የየትኛውንም አርሶ አደር ምርት ከበረሃ አንበጣ የመለየት ግዴታ ስላለብን ለሁሉም ክልል የሚሆን በጀት መድበናል። ይህን መጠቀም አለመጠቀም ጉዳይ ደግሞ የክልሎች ነው” ብለዋል።

“የአርሶ አደሩ ማሳና የአርሶ አደሩ ምርት ከፖለቲካ የተለየ ነገር ነውና ከፖለቲካው ስሜት ወጥተው መረጃዎችን ይስጡን” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ወረዳዎች በተከሰተው የአንበጣ መንጋ ሰፊ ቦታን የሚሸፍን ማሳ ላይ ያለ ሰብል ጉዳት እደረሰበት መሆኑን አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።

የአገሪቱ መንግሥትም የአንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንበጣውን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዲኤታው ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት መናገራቸው ይታወሳል።