አቶ ዳውድ ኢብሳ በድጋሚ በጸጥታ ኃይሎች ወደ ቤታቸው መወሰዳቸውን ግንባሩ አስታወቀ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

DW : ከቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ጽህፈት ቤታቸው ተመልሰው የነበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በድጋሚ በጸጥታ ኃይሎች ወደ ቤታቸው መወሰዳቸውን ግንባሩ አስታወቀ። አቶ ዳውድ በጸጥታ ኃይሎች ተገደው ወደ ቤት እንዲመለሱ የተደረጉት «ለደህንነታቸው ሲባል ነው» የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን የግንባሩ ቃል አቃባይ ቀጄላ መርዳሳ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

የግንባሩ ሊቀመንበር በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጥብቅ ቁጥጥር ስር መሆናቸው በዕለት ተዕለት ስራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንም አቶ ቀጄላ ተናግረዋል።«ባለፈው ጊዜም እንደተነገረው ከእርሳቸውም አንደበትም የሰማነው ለደህንነታቸው ተብሎ ነው ። ነገር ግን ይሄ ጉዳይ በስራቸው ላይ ቢሮአቸው ለመሄድ ተጽዕኖ አለው»ቀደም ሲል የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ባልተገኙበት በተወሰኑ የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አማካኝነት ተከናውኖ የነበረው ስብሰባ ዓላማውን ባልተረዱ ሰዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶበት በግንባሩ ላይ ብርቱ ጉዳት ማስከተሉን አቶ ቀጄላ ተናግረዋል።

«አሁን ከስብሰባው ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ውዥንብር ብዙ ጥፋት ተከስቷል። መጠነ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሲከፈት ነበር። በስብሰባው ላይ የተሳተፉትን ሁሉ በጠላትነት የመፈረጅ ስራ ውች ሀገር ባሉ በግንባሩ አባላት እና ደጋፊዎች ሲከናወን ቆይቷል። «አንዳንድ ሰዎች የሚጽፉትን እያየን ነው በጣም አጥፊ ተግባር ነው » በግንባሩ ውስጥ ተፈጠረ ችግርም አቶ ዳውድ ኢብሳ ወደ መደበኛ ስራቸው ሲመለሱ ሁሉም ነገር በንግግር ይፈታልም ብለዋል አቶ ቀጄላ ፡፡

አያይዘውም አቶ ዳውድ ኢብሳ ዛሬ ወደ መኖርያ ቤታቸው ከተወሰዱ በኋላ ከግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር አራርሶ ቢቂላ ጋር መወያየታቸውን ቃል አቃባዩ ተናግረዋል።ዶይቼ ቨሌ ዛሬ ከሰዓቱን ጉለሌ ከሚገኘው የግንባሩ ጽህፈት ቤት አከባቢ እንደተመለከተው በቢሮው መግቢያ በር ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ተቀምጠው ከመጠበቃቸው ውጭ ምንም እንቅስቃሴ አላስተዋለም፡፡ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ስዩም ጌቱ በአቶ ዳውድ ስልክ ላይ ደውሎ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ የእጅ ስልካቸው ባለመስራቱ ሳይሳካ ቀርቷል።