እኔ ብሔርና ብሔር እንዳይጋጩ ስጮህ ነበር። በብሔር ግጭት መከሰሴ ለእኔ ፌዝ ነው – ይልቃል ጌትነት

እኔ ብሔርና ብሔር እንዳይጋጩ ስጮህ ነበር። በብሔር ግጭት መከሰሴ ለእኔ ፌዝ ነው – ይልቃል ጌትነት
የኢሃን ሊቀመንበር የሆኑት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት 3:00 ላይ ከመኖሪያ ቤታቸው እያሉ በድንገት በፀጥታ ኃይሎች መያዛቸው ይታወቃል።
“በአዲስ አበባ ለተነሳው ሁከት እና ግርግር ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት ሁነሀል ” በሚል የተጠረጠሩ ሲሆን ፤ ሀምሌ 21/2012 ዓ.ም በነበረው ችሎት ፖሊስ ‘ከደረሰው የንብረት መውደም እና የሰው ህይወት መጥፋት እንዲሁም ከወንጀሉ ውስብስብነት አንፃር’ በሚል መረጃዎችን አደራጅቼ እስክጨርስ 14 ቀን የምርመራ ግዜ ይሰጠኝ ያለ ሲሆን በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቃ የተከሰሱበት ክስ አግባብ እንዳልሆነ እና 14 ቀን የምርመራ ግዜ እንደማያስፈልግ በመግለፅ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ተመልክቶ ‘የምርመራ መዝገቡን መርምሮ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ይሰጥ አይሰጥ’ የሚለውን ለመበየን ለትናንት ሀምሌ 24 ቀን 2012 ዓ.ም መቀጠራቸው ይታወሳል።
በትናንትናው ዕለት በተከበረው የዒድ አል አድሐ (አረፋ) በዓል መክንያት የመንግስት ተቋማት ዝግ በመሆናቸው በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ሊቀመንበሩ በዛሬው ዕለት ችሎት የቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱም ‘የምርመራ መዝገቡን መርምሮ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ይሰጥ አይሰጥ’ የሚለውን የግራ ቀኙን ተመልክቶ ከሀምሌ 24 ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የ10 ቀን የምርመራ ግዜ ለፖሊስ በመፍቀድ ለነሐሴ 4 መቀጠራቸውን ጠበቃ አቶ አዲሱ ጌትነት አስታውቀዋል።
ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው “የእኔ ጉዳይ ከእዚህ ችሎት አቅም በላይ ነው። ያ ባይሆን አንድ ቀን ማደር አልነበረብኝም። ዝም የምለው ቃለ መሃላ ፈፅመው ለተቀመጡት ዳኞች ክብር ስላለኝ ነው እንጂ ለሆነውና እየሆነ ላለው ነገር ሁሉ ተጠያቂው መንግስት ነው።
24 ሰዓት ስለ ፍትሕ ስርዓቱ መሻሻል በሚወራበት ሀገር ፖሊስ የፖለቲካ ውሳኔ እያስፈፀመ ነው። እኔ ብሔርና ብሔር እንዳይጋጩ ስጮህ ነበር። በብሔር ግጭት መከሰሴ ለእኔ ፌዝ ነው።” ሲሉ መናገራቸውን ጠበቃ እና የህግ አማካሪ አቶ አዲሱ ጌትነት ለአሚማ ተናግረዋል።
የኢሃን ሊቀመንበር የሆኑት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ከታሰሩ ዛሬ ሀምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም አንድ ወር ሆኗቸዋል።