የአቶ ልደቱ የጤና ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሆነ ኢዴፓ አስታውቋል

የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር ልደቱ አያሌው ጤንነታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሆነ ፓርቲው በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ በቢሾፍቱ ከተማ መርማሪያቸው ፖሊስ ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው መስማታቸውን ልደቱ ተናግረዋል ተብሏል፡፡ ልደቱ የአስም በሽተኛ ሲሆኑ፣ አምና ደሞ የልብ ቀዶ ሕክምና አድርገዋል፡፡ ይሄ ሁኔታ ይበልጥ ለኮሮና ቫይረስ ያጋልጣቸዋል- ብሏል ፓርቲው፡፡ እናም መንግሥት ወደ አዲስ አበባ እንዲያዛውራቸው፤ ይህ ካልሆነ ግን በታሳሪው ሕይወት ላይ ለሚደርስ አደጋ መንግሥት ተጠያቂ እንደሚሆን ፓርቲው አስጠንቅቋል፡፡

የአቶ ልደቱ የጤና ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወድቋል! – ኢዴፓ
ዛሬ ሃምሌ 24 ቀን 2012 የኢዴፓ አመራሮች አቶ ልደቱ ወደታሰሩበት ቢሾፍቱ በመሄድ ጉብኝት አድርገዋል። በጉብኝቱ ከተገኙት መካከል፦
አቶ አዳነ ታደሰ ፕሬዚዳንት
አቶ ሳህሌ ባይህ ዋና ፀሃፊ
አቶ ኤርሚያስ ባልከው የድርጅት ጉዳይ
አቶ ግዛቸው አንማው ጥናትና ምርምር ዘርፍ
አቶ አንዳርጋቸው አንዱአለም ብሄራዊ ም/ቤት አባል
አቶ አዲስ አለም ደሳለኝ አባል
አቶ ኮሚኒስት ደምሴ አባል
እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።
አቶ ልደቱ በጣቢያው የሚሰሩ አምስት የፖሊስ አባላት በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን ከተጠቁትም አንዱ የራሳቸው መርማሪ ፖሊስ እንደሚገኙበት መስማታቸውን ገልጸው ያሉበትን የጤና ስጋት ለአመራሮቹ ገልጸዋል።
አቶ ልደቱ ከባድ የአስም ህመም ተጠቂ ሲሆኑ ከአንድ ዓመት በፊት ደግሞ የልብ ቀዶ ጥገና አድርገዋል። ይህ ሁኔታ ለኮሮና ቫይረስ ክፉኛ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።
የፓርቲው አመራሮችም መንግስት ይህን በአቶ ልደቱ ላይ የተጋረጠውን የህይወት አደጋ ከግንዛቤ በማስገባት ጤንነታቸው ሊጠበቅ ወደሚችልበትና ቋሚ አድራሻቸው ወደሚገኝበት ወደ አ.አ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያዛውራቸውና በዚያው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሲሉ ለመንግስት ጥሪ አቅርበዋል!
ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ይህ ሁሉ ተጨባጭ ስጋት ባለበት መንግስት በዝምታ ካለፈው ድርጊቱ ሆን ብሎ ተብሎ እንደተደረገ እንደሚወሰድ ገልጸው አቶ ልደቱ ላይ ለሚከሰተው የጤናም ሆነ የህይወት አደጋ መንግስት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ አሳስበዋል!