አዎን አንድነት አንድ መሆን አይደለም ፣ ግን አንድነት ከሌለ ውጤቱ ዉደቀት ነው #ግርማ_ካሳ

ዛሬ በከፋ ቦንጋ በሚያስደንቅና በሚያስደምም ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ ፍቅር ከፍ ከፍ ተደርጓል።

አዎን አንድነት ማለት አንድ መሆን አይደለም። እንኳን ከተለያዩ ብሄረሰቦች የመጡ ቀርቶ በስጋ ወንድማማች፣ እህትማማች በሆኑት መካከልም ልዩነት አለ። ልዩነትና አንድነት አብረው የሚሄዱ ናቸው። ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች አሉ። በእምነት የተለያዩ ናቸው። ከሰማኒያ በላይ የተለያዩ ብሄረሰቦችና የዚያኑ ያህል ቋንቋዎች፣ ባህሎች አሉ።  ግን ችግር የለዉም። የኢትዮጵያ ዉበቷ ብሄረሰⶅቿ ናቸው። በአበባና በቢራቢሮ የተለያዩ ቀለማት ዉበት እንደሆኑት፣ በኢትዮጵያ ያሉ ልዩነቶች ዉበቷ ናቸው። አዎን አንድነት ማለት አንድ መሆን አይደለም። አፍንጫና ጆሮ አንድ አይደሉም። እግርና እጅ አንድ አይደሉም።

ሆኖም ግን የተለያዩ አካላት የተዛመዱ፣ የተገመዱ ናቸው። በኢትዮጵያ ብሄረሰⶅቹ፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮችዋ አንድ የሚያደርጋቸው፣ የሚያስተሳሰራቸው ነገር ቢኖር ደግሞ ኢትዮጵያዊነታቸው ነው። የጋራ እሴታቸው፣ የጋራ ቤታቸው ኢትዮጵያ ናት። ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ አማራው፣ ጉራጌው ያለ ኢትዮጵያ ዋጋ የለውም። ኦሮሞው ለብቻው ቢቆም የትም አይደርስም። የኦሮሞው እድል ፈንታ ከአማራው፣ ከጉሙዙ፣ ከሲዳማው ፣ ከሶማሌው ..ጋር የተቆራኘ ነው። ሌላውን አግልሎ፣ ሌላው ሸሽቶ፣ ሌላው አፈናቅሎ፣  ኦሮሞ ዋጋ አይኖረውም። አማራውም እንደዚሁ፣ ከትግሬው፣ ከአፋሩ፣ ከኦሮሞው .. ጋር ተሳስሯል። ያንን ለመበጠስ መሞከር ማለት እራስን ማጥፋት ማለት ነው።

አንዱ የሚኖረው ሁሉም ሲኖሩ ነውና፣ የአንዱ ቤት ፈርሶ የሌላው ቤት አይቆምምና፣ አንዱ ወድቆ፣ ሌላው መሄድ አይችልምና፣  መያያዙ፣ መደጋገፉ፣ በአንድነት መሰለፉ ብቸኛ አማራጫችን ነው። በፍቅር ወደ ፊት ሊያሻግረን የሚችለው ኢትዮጵያዊነታችን ነው። ኢትዮጵያዊነት ጸረ-ኦሮሞነት ፣ ጸረ-ትግሬነት፣ ጸረ-አማራነት አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ኦሮሞነትንም፣ ትግሪነትን፣ ጉራጐነተን..ያካተተ የሁሉም ነጸብራቅ የሆነ ነው። በአንጻሩ ግን ጸረ-ኢትዮጵያዎነት ጸረ-ኦሮሞነትም ጸሮ-አማራነትም፣ ጸረ-ትግሬነት .. ነው።

አንዳንድ ወገኖቼ ለኢትዮጵያዊነት ፣ ለሰንደቋም የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው ሲገልጹ አያለሁ።ያን የማድረግ መብታቸው እንደሆነ ቢታወቅም፣ ቆም ብለው እንዲያስቡ እመክራቸዋለሁ። በተለይም በወለጋና በትግራይ አካባቢ ያሉ ወገኖች በኢትዮጵያዊነት ድንኳን ስር እንዲሰባሰቡና እንዲደመሩ በአክብሮት እጠይቃለሁ። ጂጂጋ፣ ወልቂጤ፣ ቡታጅራ፣ ጂንካ፣ ሆሳና፣ ዱራሜ፣ ወራቤ፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ባህር ዳር…ዛሬ ደግሞ ቦንጋ መከፋፈል ሳይሆን አንድነት፣ ጥላቻ ሳይሆን ፍቅር፣ ዘረኝነት ሳይሆን አብሮነት ይሻለናል እያሉ ነው። እየተደመሩ ነው። ወለጋና ትግራይ የታላላቅ አርበኞች፣ ጀግኖች ትዉልድ ቦታዎች ናቸው። የኢትዮጵያ አንድነትን በተመለለተ ወለጋና ትግራይ ቀዳሚ ሚና የተጫወቱ ናቸው። ትግራይ የነ ጀግናው አሉላ አበነጋ ፤ የጀግናው አጼ ዪሐነስ አገር ናት። ወለጋ የነ አርበኛ ቡራዮ፣ የነ ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ፣ ደርቡሾችን ድባቅ ያደረጉት የነ ደጃዝማች ጆቲ አገር ናት። ምን አልባትም የተወሰኑ ወገኖች በረጩት የተሳሰተና ዘረኛ አመለካከት ለጊዜው ወደ ኋላ እየተጎተቱ ይሆናል። ግን ተስፋ አለኝ እንደሚነቁ።

ከዚህ በታች ያለው አስደናቂ ፎቶ ዛሬ በከፋ ቦንጋ የተደረገ ነው። የፊታችን ቅዳሜ ደግሞ በሌላ የደቡብ ክልል ታላቅ ከተማ በባህር ዳር ፣ ምን አልባትን ከሸገርና ከባህር ዳር ሰለፍ ሶስተኛ ትልቁ ሰልፍ ሊሆን የሚችል ሰልፍ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።መረጃ ቲቪን በተሻለ ጥራት እና ፍጥነት እንድናቀርብ እገዛችሁን እንሻለን።
መረጃ ቲቪን ለማገዝ ይህን ሊንክ በመጫን አባል ይህኑ - JOIN Mereja TV