ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ መሆኗ የማይቀር ነው – የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ

ሲራራ ጋዜጣ
“አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የዩጎዝላቪያን የመጨረሻ ጊዜያት የሚያስታውስ ነው”
አቶ ቀጀላ መርዳሳ – (የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ)
ስድስተኛው አገር ዐቀፍ ምርጫ መራዘሙን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ መጠየቁ ሕጋዊ መሠረት የሌላውና ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ ነው ሲሉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ተናገሩ፡፡
ሲራራ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ምርጫውን ለማራዘም መንግሥት የሄደበትን መንገድ ፓርቲያቸው እንደማይቀበለው ገልጸው ኦነግ ሒደቱ በአስቸኳይ ሊታረም እንደሚገባ አሳስቧል ብለዋል፡፡
“የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የፍርድ ቤት አልያም የግለሰቦች ሥልጣንና ኀላፊነት እንጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠ አይደለም” ያሉት አቶ ቀጀላ፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪው አካል በትክክል ሥራውን ከሠራ የሚተረጎም ሕግ አለመኖሩን ገልጾ ጉዳዩን ይመልሰዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከሕገ መንግሥቱ ጋር የማይገናኝ ነገር ለመተርጎም ከተሞከረ አደጋ ይዞ ስለሚመጣ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡
በምርጫው መራዘም ላይ ኦነግ ጥያቄ ያለውም ያሉት አቶ ቀጀላ፣ ምርጫው እስኪደረግ አገሪቱ እንዴት ትመራ በሚለው አጀንዳ ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ ፓርቲዎች መነጋገር አለባቸው የሚል አቋም እንዳለው ገልጸዋል፡፡
“መንግሥት አሁን በያዘው መንገድ ከቀጠለ ከመስከረም 30 በኋላ እንደ መንግሥት ያለውን ተቀባይነት ያጣል” የሚሉት አቶ ቀጀላ ያን ተከትሎ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፤ በዚህም ወደለየለት ሥርዓት አልበኝነትና የአገር ብተና ሊገባ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ፓርቲያቸው እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ከመስከረም 30 በኋላ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ምክር ቤት መቋቋም እንዳለበት አቶ ቀጀላ ይናገራሉ፡፡
የትግራይ ክልል መንግሥት ለብቻው ምርጫ ለማድረግ ማሰቡን እንዴት ታዩታላችሁ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ቀጀላ፣ ቀድሞም ቢሆን ፓርቲያቸው ምርጫው እንዲራዘም ፍላጎት እንደነበረው አስታውሰው በዚህ ሰዓት በክልል ደረጃ የሚደረግ ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ክልል ከምርጫ ቦርድ ዕወቅና ውጪ የሚያደርገው ምርጫ ሕጋዊ ተቀባይነት እንደማይኖረውም አቶ ቀጀላ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
“ቀድሞውንም ቢሆን የትግራይ ክልል ምርጫ ለማድረግ መነሳቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር ግጭት ውስጥ የሚከተው ነው፡፡ በቀጣይ ደግም ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ እንዲያውም ከወዲሁ መካረርና የእርስ በርስ መጠላለፍ ተጀምሯል” ያሉት አቶ ቀጀላ በኹለቱ የመንግሥት ክንፎች መካከል በሚፈጠር ግጭት ጉዳት ከመድረሱ በፊት በጠረጴዛ ዙሪያ መምከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ቀድሞም ቢሆን በገዥው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት አገሪቱን ወደ ከፍተኛ አለመረጋጋትና መጠላለፍ ከትቷት መክረመን የሚገልጹት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው፤ ከሰሞኑ በአመራሮች ደረጃ የሚታየው አላስፈላጊ የቃላት ጦርነት ልዩነቱን እያሰፋው ይሄዳል የሚል ስጋት እንዳላቸው እና ነገሮች ወዳላስፈላጊ ግጭት ከመሄዳቸው በፊት በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ አቶ ቀጀላ፡፡
“የብልጽግናም ሆነ የሕወሓት ሰዎች አሁን የያዙት መንገድ አገሪቱን ወደ አደገኛ የእርስ በርስ ግጭትና እና ብተና ሊወስዳት የሚችል የቀድሞዋ የዩጎዝላቪያ መንገድ ነው” የሚሉት አቶ ቀጀላ፡- “ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ይጎዝላቪያ ከመፈራረሷ በፊት የነበረውን የመጨረሻዎችን ጊዜያት የሚያስታውስ ነው፡፡ በተለይ በሥልጣን ላይ ያሉት አካላት እብሪትና የሥልጣን ጥም አውሯቸው በዚህ መንገድ ከቀጠሉ ኢትዮጵያ እንደ ይጎዝላቪያ መሆኗ የማይቀር ነው” ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ሲራራ ጋዜጣ