አሁን የጥገኝነት የበላይነት ነው ያለው አሁን ያለንበት ፈተና ተሻግረነዋል የሚባል አይደለም ገና ግጥሚያ ላይ ነን ምከታ ላይ ነን- ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከመቓልሕ ትግራይ መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ህወሓትን ሊበትኑ ይችሉ የነበሩ ዓበይት ፈተናዎች ምንና በየትኛው መድረክ ነበሩ? እንዴት መሻገር ተቻለ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ከሰጡት ምላሽየተቀነጨበ፡-

አማራጭ ሲታጣ ወደ ትጥቅ ትግል መገባቱን በመጠቆም፤ ራሱ የትጥቅ ትግሉ ከባድ ፈተና እንደነበረ ከገለፁ በኋላ የመጀመሪያው ፈተና ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1974/75 የነበረው ፈተና ነው ይላሉ፡፡

ከ1975 በኋላ የነበረው ደግሞ ሌላ ፈተና ነው ይላሉ፡፡
የመጀመሪያው ፈተና የህልውና፤ የድርጅት መቀጠልና አለመቀጠል ጉዳይ ነበር፡፡ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ መሪዎቹን ማጣት የጀመረ ጨቅላ ድርጅት ነበር፡፡ ዓላማውን ሊያስቀጥል ይችል ይሆን? የሚልጥያቄ ነበር፡፡ የጠራናፊት እንቅስቃሴ ሽፍታ የሚያስተዳድረው ነበር፡፡ በመቀጠልም ከኢዲዩ ጋር የነበረ ውጊያና የጀብሃ እንቅስቃሴም ነበር፡፡ በተለይ በምስራቅ በማዕከልም የተወሰነ የኢህአፓ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ በተነፃፃሪ የተሻለ ትጥቅ የነበራቸው እነሱ ነበሩ ይላሉ፡፡

ደርግ ደግሞ እዚያው እንዳለ ከፍተኛ ፈተና ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በድርጅት ውስጥ ሕንፍሽፍሽ የተባለ በታኝ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ በዋነኝነት በ1969 ዓ.ም. የተጀመረ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ የተከተለው ፈተና ከ1975-1979 ዓ.ም. የነበረው የመገታት ችግር ነበር፡፡ መገታት ወይም አዙሪት እየተባለ የሚታወቀው ዕድገት የማይታይበት ተዋግተን ተዋግተን በመጨረሻ የት ነው የምንደርሰው? እውነት ደርግን ልንደመስሰው እንችል ይሆን? የሚል ጥርጣሬ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡

ይህንን ተሻግረን ድል እናደርግ ይሆን? የሚል ጥያቄ የተነሳበት ሌላው ወቅት የ1977 ዓ.ም. ድርቅ ነበር፡፡ የትግራይ ህዝብ በጣም የተጎዳበት ወቅት ነበር፡፡ በትጥቅ ትግሉ መድረኮች የነበሩት ፈተናዎች እነዚህ ነበሩ ብለዋል፡፡
የ2010 ፈተና ግን የተለየ ፈተና ነው፡፡ አዲስ የመስመር ወይም የአሰላለፍ ማስተካከያ የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ጥገኛው ሃይል በራሱ የብልሽት መንገድ ነው የመጣው፡፡ በ1994 የተሃድሶ ወቅት እንዳስቀመጥነው ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፤ እርሱ ላይ ማተኮር አለብን ብለን ነበር፡፡

አርሶ አደሩንም ሌላውንም ይዘን ኪራይ ሰብሳቢዎችን እንግጠም የሚል አቋም ነበረን፡፡ በዚያም መሰረት ብዙ ተራምደናል፡፡ ነገር ግን በሚገባ ስላልተወገነ ኪራይ ሰብሳቢው ወደ ስልጣን መጣ፡፡ ስለዚህ ጠላት ነው ብለን ያስቀመጥነው፤ ልናፈርሰው ይገባናል ያልነው፤ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ካልተቀየረ ያ ጠላት ሊፈርስ አይችልም፡፡

ስለዚህ በሂደት እያለ ተኮላሸ እንጂ አሁን አዲስ ሁነት አልተፈጠረም፡፡ የትግሉ አግባብ፤ ጠላት የምንለውም፤ የምንገነባው ስርዓትም እስከ 40 ዓመት ምን መሆን እንዳለበት ተቀምጧል ብለዋል፡፡
ውስጣዊ ትግል ስለተቀዛቀዘ፤ መገንባት ያለበት ስርዓት ስላልተገነባ ጥገኛው ተመልሶ የመምጣት ዕድል ነው ያገኘው፡፡ አሁን አዲስ መስመር አይደለም የሚያስፈልገን፡፡ መስመሩ እሱ ራሱ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገን ትግል ነው፡፡ አሁን ያጋጠመንን አደጋ እንዴት አድርገን በፅናት እንመክተው የሚለው ካልሆነ በቀር መስመሩ ለረጅም ጊዜ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

ልማታዊ መንግስት የምንለው አብቅቶለታል ማለት አይደለም፡፡ አሁን ልማታዊው መንግስትና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ነው በመፍረስ ላይ ያለው፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከሌላው የተለየ ነው፡፡ የተለየ የትግል አግባብ ያስፈልጋል፡፡

እንደ ትግራይ ያስቀመጥነው አለ፡፡ ማዕከላችንን ትግራይ አድርገን እንስራ ነው የምንለው፡፡ በትግራይ ያለውን ችግር እየፈቱ በሃገር ደረጃ ደግሞ እንደ ህወሓት ከሌሎች ፌዴራሊስት ሃይሎች ጋር በመተባበር ግዴታህን መፈፀም ነው፡፡ የነበረን መስመር ሊቀጥል የሚችል ነው፡፡ የመስመር ለውጥ አያስፈልገንም፡፡

እነሱ የመስመር ለውጥ አድርገዋል፡፡ እኛ ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢ ነው እንላለን፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የምንለው ልማታዊ ዲሞክራሲ አይሰራም ነው የሚሉት፡፡ ነገር ግን ብዙ ልማት እንዳስገኘ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ መስመሩ እሱ ነው እንላለን፡፡ የትግል አግባብና ሰትራቴጂዎችን በማስተካከል መታገል ነው የሚጠይቀው፡፡

አሁን የጥገኝነት የበላይነት ነው ያለው፡፡ አሁን ያለንበት ፈተና ተሻግረነዋል የሚባል አይደለም፡፡ ገና ግጥሚያ ላይ ነን፡፡ ምከታ ላይ ነን፡፡ አሁን በገለፅነው አግባብ ገጥመን ልንሻገረው ይገባናል፡፡ በትግል ውስጥ እንገኛለን እንጂ ተፈትቷል ማለት አንችልም፡፡ በድምሩ የትጥቅ ትግሉ ፈተናዎች ታልፈዋል፡፡
በሰላም ወቅት ያጋጠመችንን አንዲት ፈታኝ መድረክም ተሻግረናታል፡፡

ሁለተኛዋን ለመሻገር ግን ገና በትግል ላይ ነን፡፡ ፍላጎታችን የተሻለ ውጤት ማምጣትና ማስተካከል ነው፡፡ ልናሸንፍ እንችላለን የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
ለካቲት 5 ፡ 2012 ዓ/ም መቐለ