የጃዋር ኢትዮጵያዊነትን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጠው ምርጫ ቦርድ ኢሚግሬሽንን ጠየቀ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


BBC Amharic : በቅርቡ ኦፌኮን የተቀላቀሉት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ መስራች አቶ ጃዋር መሃመድን ፓርቲያቸው ኢትዮጵያዊ ናቸው የሚል የአባልነት ማረጋገጫ መስጠቱን ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ዜግነታቸውን መልሰው የሚያገኙበትን ሂደት ማብራሪያ እንዲሰጠው ምርጫ ቦርድ ኢሚግሬሽንን ጠይቋል።

የምርጫ ቦርድ የካቲት 2፣ 2012 በፃፈው ደብዳቤ አቶ ጃዋር የኢትዮጵያ ዜግነታቸውን መልሰው በማግኘት ሂደት ላይ እያሉ ፖርቲያቸው ኢትዮጵያዊ ናቸው የሚል የአባልነት ማረጋገጫ መስጠቱን ጠቅሷል።

በአገሪቱ ህግ መሰረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ግለሰቦች በፖለቲካ መሳተፍ ስለማይችሉ ከዚህ ቀደም ምርጫ ቦርድ አቶ ጃዋር ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን መልሰው አግኝተው ከሆነ ይሕንን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ወይም ሰነድ ከደህንነት፣ ኢሚግሬሽን እና ስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን እንዲያቀርቡ ለፓርቲው ሁለት ጊዜ በደብዳቤ ጠይቋል።

ኦፌኮ በምላሹም ለምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ አቶ ጃዋር መኖሪያቸውን ኢትዮጵያ ማድረጋቸውን ጠቅሶ፣ የሌላ አገር ዜግነታቸውንም በመተው፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸው እንዲመለስላቸው ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በማመልከታቸው ኢትዮጵያዊ ናቸው የሚል ደብዳቤ ፅፏል።

በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ ከኦፌኮ ደረሰኝ ያለው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው በትውልድ ኢትዮጵያዊ ለሆነ ሰው ኢትዮጵያዊ ዜግነትን መልሶ ማግኘትን በተመለከተ ከየትኛውም የመንግሥት አካል ሰነድ ወይም ማስረጃ ሰርቲፊኬትን ማግኘት የሚደነግግ ህግ የለም ብሏል።

በዚህም መሰረት አቶ ጃዋር የኢትዮጵያዊነታቸውን ማስረጃ ሰነድ ፓርቲው እንዲያቀርብ መጠየቁ አግባብነት የለውም የሚል መከራከሪያ ሃሳብ ከማቅረብ በተጨማሪ አቶ ጃዋር ኢትዮጵያዊ ናቸው የሚል ምላሽ ለምርጫ ቦርድ ሰጥቷል።

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ፓርቲው ሰነድ ማቅረብ አይገባንም የሚለውን ከሃገሪቱ አዋጅ አንፃር በመፈተሽ ውሳኔ ማሳለፍ ቢችልም፤ ምናልባት ይህ ሁኔታ የዜግነትን ጉዳይ ለመመርመርና ለመወሰን ስልጣን ካለው የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አሰራር ሂደት ጋር ሊጣረስ ይችላል፤ እንዲሁም ወደፊትም የሚመጡ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ይቻል ዘንድ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ መጠየቁን ደብዳቤው አትቷል።

ይህንን መሰረት በማድረግ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ የሌላ አገር ዜግነት ያለው ሰው መኖሪያውን በኢትዮጵያ ካደረገ፣ የሌላ አገር ዜግነቱን ከተወ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ እንዲመለስለት ለባለስልጣኑ ካመለከተ ዜግነትን ያለ ኤጀንሲው ውሳኔ ወዲያው ያገኛል ወይስ አያገኝም የሚለው ላይ ምላሽ እንዲሰጠው ምርጫ ቦርድ በደብዳቤው ጠይቋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማብራሪያውን እስከ የካቲት 9፣2012 ዓ.ም ድረስ እንዲልክም መጠየቁን የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ያስረዳል።

ለረጅም ዓመታት የአሜሪካ ዜጋ እንደሆኑ የሚታወቁት አቶ ጃዋር መሐመድ በኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል ሆነው በቅርቡ ቀጥተኛ የፖለቲካ እንቀስቃሴ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።