ከደምቢዶሎ እገታ ያመለጠችው ተማሪና የታጋቾች ቤተሰቦች ከሚዲያዎች እንድንርቅ ማስፈራሪያ እየደረሰብን ነው አሉ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

የአማራ ተማሪዎችን መታገት ያጋለጠችው ተማሪ እና ስለ ልጆቻቸው ለሚዲያ የተናገሩ የታጋች ቤተሰቦች ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን ገለፁ።

( አሥራት ) ኦሮሚያ ክልል ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ መታገትን ያጋለጠችው ተማሪ አስምራ ሹምዬ ማስፈራሪያ እየደረሰባት መሆኑን ለአሥራት ገልፃለች።የታገቱ 17 ተማሪዎችን በተመለከተ መረጃ ለሚዲያ ያደረሰችው ተማሪ አስምራ ሹምየ ለአሥራት እንደገለፀችው ከተለያየ ቦታ የማታውቃቸው ስልኮች እየተደወሉ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሳት ይገኛል። አንቺ ማን ሆነሽ ነው መረጃ የምትሰጭው? የሚል ማስፈራሪያ ደርሶብኛል፣ ለህይወቴም እሰጋለሁ” ስትል ለአሥራት የገለፀችው አስምራ፣ “ማስፈራሪያው ቤተሰቦቼንም ጭንቀት ውስጥ ጥሏቸዋል” ብላለች። ከተማሪ አስምራ በተጨማሪ አንዳንድ የታጋች ቤተሰቦችም ተመሳሳይ ጫና እየደረሰባቸው እንደሆነ ለአሥራት መረጃው ደርሶታል።

አሥራት ያነጋገራቸው የታጋች ቤተሰቦች በበኩላቸው “እስካሁን ልጆቻችንን ማግኘት አልቻልንም ፣ መንግስት ተለቀዋል ብሎ የተናገረው እውነት ከሆነ ልጆቻችንን ያገናኘን” ብለዋል።በስልክ ያነጋገርናቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ወላጆች እንደገለፁት ከመንግስት ከሰጠው መግለጫ ውጭ ከልጆቻቸው ምንም የሰሙት ነገር እንደሌለ፣ የመረጃውን እውነተኛነት ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።የእውነት ቢለቀቁ ኖሮ ልጆቻቸው ይደውሉላቸው እንደነበር የተናገሩት እነዚህ ወላጆች እና ቤተሰቦች የመንግስትን መረጃ ማመን እንዳልቻሉ ገልፀዋል።

ታጋች ተማሪዎቹ ማሰቃቂ ሁኔታ ላይ ናቸው የምትለው ተማሪ አስምራ ሹምየ “ከታገቱ ከሶስት ሳምንት በኋላ በአጋቾች ስልክ እንዳገኘቻቸውና ከዛ በኋላ ግን ግንኙነት እንደተቋረጠ ተናግራለች።አስምራ ለአሥራት መንግስት የሀሰት መረጃ እያሰራጨ ነው ብላ እንደምታምን የገለፀች ሲሆን የአማራ ተማሪዎች ጉዳይ መንግስትን ብዙም እንደማያስጨንቀው እናውቃለን ብላለች።

የተማሪዎች መለቀቅ በተመለከተ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማብራሪያ የሰጡት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተለቀቁ ያሏቸው ተማሪዎች አሁንም ባሉበትን ሁኔታ እንደሚገኙ ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራም አልተሳካም።አሥራት ቀደም ብሎ ስለታጋች ተማሪዎች በተደጋጋሚ ዘገባ የሰራ ሲሆን የታጋች ቤተሰቦችን ከቀናት በፊት አነጋግሮ ዘገባ መስራቱ ይታወሳል።