የህወሓት መግለጫ ለኢትዮጵያ የወደፊት ፖለቲካዊ ርምጃ ምን እንደምታ ይኖረዉ ይሆን?


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

DW ዉይይት፤ የህወሓት መግለጫና ቀጣዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ

የህወሓትን መግለጫ እንዴት አገኙት? ለኢትዮጵያ የወደፊት ፖለቲካዊ ጉዞ ምን እንደምታ ይኖረዉ ይሆን? የህወሓትና የብአዴን ዉዝግብና ንትርክስ ምክንያቱ ምን ይሆን? ይህ ፍጥጫ በሃገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሚኖረዉ አንድምታ ምን ሊሆን ይችላል? የምርጫ ጊዜ ተቃርቦአል፤ ፓርቲዎች በዘርና ሃይማኖት የመከፋፈል አዝማምያ ዉስጥ ተኾኖ እንዴት መስራት ይችላሉ?

ላለፉት 29 ዓመታት ኢትዮጵያን ከመራዉ ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እህት ድርጅቶች አንዱና ዋነኛ የነበረዉ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሰሞኑን ለሁለት ቀን በጠራዉ አስቸኳይ የጉባኤ፤ የኢሕአዴግ ውህደትን እንደማይቀበለው ታህሳስ 27 ቀን የመጨረሻ ውሳኔዉን አስተላልፏል።

ጠቅላላ ጉባዔዉ ባወጣዉ የአቋም መግለጫ ዉህደቱን ዉድቅ ከማድረግም አልፎ ኢሕአዴግ ‘በክህደት’ ፈርሷል፤  ብልፅግና ከተባለው ፓርቲ ጋር ሃገር ለማፍረስና ወደ አህዳዊ ስርዓት ለመሄድ አንዋሃድም ፤ በጋራ መስራትም አንችልም በማለት ገልጿል፡፡ ህወሓት ብልፅግና ፓርቲን «አዲስ፣ ሕገ-ወጥና ጥገኛ» ፓርቲ ነዉ በማለትም ወቅሷል።

ህወሓት ራሱ የመሰረተዉን እና እንዲዋሃድ ሲከራከርለት የነበረዉን የኢሕአዴግ ዉህደት ዉድቅ ያደረገዉ በአዲሱ ፓርቲ ዉስጥ የቀድሞዉን አይነት ተሰሚነት እና ተቀባይነት ስለሌለዉ ነዉ የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም።  ያም ሆነ ግን ይህ ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ከፍተኛ ተጽኖ ያለዉ ፓርቲ ሕወሓት የገዥዉን ዉሕደት አለመቀበሉ ፤ ከገዥነት ወደ ተቃዋሚ ፓርቲነት መቀየሩ እዉን የሆነ ይመስላል። የወደፊቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካም እስካሁን ይጓዝበት ከነበረዉ በተለየ መልኩ የሚሄድ መሆኑንም አመላካች ነዉ።

በሌላ በኩል ህወሓትም ኢህአዴግን የመሰለ ሌላ ግንባር ለመፍጠር የተለያዩ ወገኖችን ሰብስቦ አንድ የትብብር መድረክ መፍጠሩ እስካሁን የነበረዉን ተጽኖ እንደያዘ ለመቀጠል ያለመ ነዉ ያሉ ጥቂቶች አይደሉም ። የህወሓት መግለጫ እና የወደፊት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ የእለቱ መወያያ ርዕሳችን ነዉ።

በዉይይቱ ላይ ሃሳባቸዉን እንዲያካፍሉን የጋበዝናቸዉ፤

ዶክተር ፍስሃ ሃብተጽዮን የፖሊሲ ጥናት ተቋም ኃላፊና የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራር አባል፤  ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን)ሊቀመንበር፤ አቶ ጅብሪል አደብ የቀድሞ የኦነግ አመራር እና ወታደር እንዲሁም በፈቃዱ ኃይሉ የተለያዩ የዓለም ዓቀፍ ሽልማቶን ያገኘዉ የዞን ዘጠኝ መስራች አባል፤ ጦማሪ ነዉ። የህወሓትን መግለጫ እንዴት አገኛችሁት? መግለጫዉ ለኢትዮጵያ የወደፊት ፖለቲካዊ ርምጃ ምን እንደምታ ይኖረዉ ይሆን? ሃሳባችሁን አካፍሉን!