ከኢትዮጵያዊያን ወላጆች የተገኙት ሁለት ወንድማማቾች በስዊዝ ሊግ ስማቸው የገነነ ማንችስተር ዐይኑን የጣለባቸው


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

BBC Amharic : ከዙሪክ ኡፊኮን ሰፈር የተነሳቸው BMW X5 ጠይም ቄንጠኛ ተሽከርካሪ እንደ ወፍ ትበራለች፤ ወደ ኒውሼትል። ኒውሼትል ከስዊዘርላንድ 26 ክፍለ አገሮች አንዷ ናት፤ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች የሚበዙባት።

የመኪናዋ ካፒቴን አቶ ምሥጢረ ኃይለሥላሴ ናቸው። ባለቤታቸው ወ/ሮ ማክዳ በቀለ ጋቢና ከጎናቸው ተቀምጠዋል።

ባልና ሚስት ብዙ ሰዓታቸውን የሚያወሩት ስለ ኳስ ነው፤ እንደ አዲሳባ ኤፍ ኤም።

ስለ ልጃቸው ፐርፎርማንስ፣ ስለ ስዊዝ-ሊግ…ስለ ቡንደስሊጋ ያወጋሉ፤ ይስቃሉ፣ አሰላለፍ ይተቻሉ፤ ቴክኒክ-ታክቲክ ያብላላሉ፣ ቦል ፖዚሽን እና ቦል ፖሰስሽን እያባዙ ያካፍላሉ…እየደመሩ ይቀንሳሉ…። ነገረ ሥራቸው ሁሉ ያስቃልም፣ ያስቀናልም።

ባልና ሚስቱ ኳስ ላይ የሙጥኝ ያሉት ያለምክንያት አይደለም። ከልጆቻቸው 2/3ኛ የሚሆኑት ኳስ ተጫዋቾች በመሆናቸው ነው፤ ለዚያውም ፕሮፌሽናሎች። የስታትስቲክስ ጅራፍ አጮኽኩ እንጂ…፤ ከሦስቱ ልጆቻቸው ሁለቱ ማለቴ ነው።

አልፎ አልፎ ታዲያ የኳስ ወሬያቸው ረገብ ሲል በውስጥ ስፖኪዮ ወደኔ እያማተሩ “ተጫወት እንጂ” ይሉኛል።

“እሺ…እየተጫወትኩ ነው”

‘ዕድለኛ ነህ፤ ጥሩ ጌም ባለበት ቀን ነው ዙሪክ የመጣኸው”

“አይደል?! እኔም አጋጣሚው ደስ ብሎኛል።”

“በረራህ ጥሩ ነበር?”

“ምንም አይል…11 ሰዓት ፈጀ። ከናይሮቢ-ዳሬሰላም፣ ከዳሬሰላም-ዙሪክ”

“ው….! ደክሞኻላ!”

ረ ደህና ነኝ! ፕሌን ውስጥ መተኛቴ በጀኝ፤ ዳሬሰላም የጀመርኩትን ህልም ስዊዘርላንድ ነው የጨረስኩት”

“እውነትህን ነው?”

“አዎ! የሕልሜ ‘መቼት’ ከሞላ ጎደል ሜዲትራኒያን ላይ ነበር ማለት ይቻላል…”

ከዚህ በኳስ ፍቅር ካበደ ቤተሰብ ጋር በቀላሉ ለመግባባት እየሞከርኩ ነው።

ገና ዙሪክ ደርሼ ሆቴል ከመግባቴ ነበር ‹‹ተነስ የካምቦሎጆ ሰዓት ደርሷል›› ብለው አንከብክበው ይዘውኝ የወጡት፤ ባልና ሚስቱ፤ በኳስ ያበዱቱ።

ማረን ኃይለሥላሴ

ማረን እና ቅዱስ

አቶ ምሥጢረ ኃይለሥላሴና ወ/ሮ ማክዳ በቀለ ሲበዛ ተጫዋቾች ናቸው። ድሮስ ልጆቻቸውን ኳስ እያጫወቱ እነሱ እንግዳ ማጫወት ሊያቅታቸው ነበር’ንዴ?

ሦስት ወንድ ልጆች አሏቸው። ማረን ኃይለሥላሴ፣ ቅዱስ ኃይለሥላሴና ቃለዓብ ኃይለሥላሴ ይባላሉ። (ኃይለሥላሴ ቤተሰባዊ ስም በመሆኑ በአገሬው ደንብ የቤተሰቡ ሁሉ ቅጥያ ሆኖ ያገለግላል)

ማረን እና ቅዱስ ታላቅና ታናሽ ናቸው። ሁለቱም እሳት የላሱ ተጫዋቾች ናቸው። ለትንሹ ቅዱስ ኳስ ትታዘዝለታለች፤ ለትልቁ ማረን ኳስ ታሸረግድለታለች…እያሉ ይጽፋሉ ‘አሉ፤ የአገሬው ጋዜጦች፣ በአገሬው ቋንቋ።

ማረን በተለይ የበቃ የነቃ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ሆኗል። አሁን 21 ዓመቱ ነው። እንዲህ ክንፍ አውጥተን ወደ ኒውሼትል የምንበረው ለምን ሆነና! 

ታናሹ ቅዱስም የዋዛ አይደለም፤ ለስዊዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን ከ18 ዓመት በታች ቋሚ ተሰላፊ ነው። አብሮን መኪና ውስጥ አለ። የጎረምሳ ሹራብ ኮፍያ አድርጎ ጸጥ ብሎ ሞባይሉን ይጎረጉራል።

“ማረን ዛሬ ወሳኝ ጌም ነው ያለበት።” አቶ ምሥጢረ መሪያቸውን እንደጨበጡ በድጋሚ አስገነዘቡኝ።

ረ!?”

“አዎ! ተጋጣሚያችን “ያንግ ቦይስ” ይባላል። የዋዛ ቡድን እንዳይመስልህ።” ጉጉታቸው ከአነዳዳቸው ይፈጥናል።

“ስሙን ሰምቼው አላውቅም ግን?”

“ምናለፋህ የዚህ አገር ማንችስተር በለው? ወይም የኛን ቅ/ጊዮርጊስ ልትለው ትችላለህ”

ረ?”

“አዎ! የስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ቡድን እኮ ነው። ላለፉት ሁለት ዓመታት የስዊስ ሱፐርሊግ ሻምፒዮን ነበር፤ የጥሎ ማለፉን ዋንጫም የወሰደ ክለብ ነው” አቶ ምሥጢረ ጎላ ባለ ድምጽ ተናገሩ።

“…በዚያ ላይ ደግሞ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ያውቃል” ወ/ሮ ማክዳ ተደረበች።

“ልጃችሁ ማረን ግን ለዙሪክ ኤፍሲ እንደሚጫወት ነበር የሰማሁት…?”

“ልክ ነህ! ነገር ግን አንተ ከመምጣትህ ከአንድ አምስት ሳምንት በፊት ነው ወደ ኒውሼትል የተዛወረው…በውሰት።”

ከዙሪክ ወደ ኒውሻትል በውሰት የተዛወረው ማረን

ከአዲስ’ባ አሰላ…ከዙሪክ-ኒውሼትል

አቶ ምሥጢረ በኳስ ስሜት ውስጥ ሆነው ነው መሰለኝ እያሰለሱ መኪናዋን ክንፍ ያስበቅሏታል።

ዝግ አሉልኝ ስል… ያፈተልካሉ…፣ልክ እንደ ዎልቭሀምተኑ አዳማ ትራዎሬ….፤ ለዚያውም የጎዳናውን ቀኝ ክንፍ ይዘው፤ ለዚያውም በ140።

እኔ ደ’ሞ ፍጥነት ያስፈራኛል። ነፍሴን ይሰውረዋል። ያም ሆኖ የመኪናው ይሁን የአስፋልቱ ልስላሴ አላውቅም…ብቻ…ወትሮ በአገርቤት ‹‹ሃይሩፍ ሚኒባስ›› ስሳፈር እንደማደርገው ለጊዜው ጸሎተ-ንሰሐ አልጀመርኩም።

“አይዞህ! በተፈቀደ ፍጥነት ነው የምንሄደው። ይታይኻል ይሄ ማሽን? ከተፈቀደው ፍጥነት ይቺን ታክል ብታልፍ ነገ ቤትህ የቅጣት ወረቀት ነው የሚመጣልህ…”

ለካስ አቶ ምሥጢረ ፍርሃት እንዳኮማተረኝ በውስጥ ስፖኪዮ አሻግረው ተመልክተዋል።

የሆነ ቦታ ስንደርስ በግድ ዝግ እንድንል ሆነ። አውላላ የነበረው አውራ ጎዳና ድንገት በተሽከርካሪ ተጨናነቀ። አቶ ምሥጢረ ከፊታችን አንዳች አደጋ መፈጠሩን ተነበዩ።

ትንበያቸው ልክ ነበር። አውራጎዳናው ላይ አደገኛ የሚባል ግጭት ተከስቶ አንዱ መኪና አፍንጫው ተጣሞ፣ በበቃኝ የተዘረረ ቡጢኛ መስሏል፤ ቀኝ የወኋላ ቆሟል። ሌላኛውም እንደዚሁ…።

ግጭቱን ሾልከን እንዳለፍን ግን አቶ ምሥጢረ መኪናዋን በተለመደው ፍጥነት መጋለብ ጀመሩ፤ ልክ እንደ ፓሪስሴንዣርማኑ ኪሊያን እምባቤ

እርግጥ ነው ኳሱ ሊያመልጠን አይገባም። እኔም ጉጉቴ ሰማይ ነክቷል። የሆነ አውሮፓ አገር ሺህ ተመልካች መሀል ቁጢጥ ብዬ ኳስ ማየት አጓጉቶኛል። እስከዛሬ ኳስ በቴሌቪዥን መስኮት አጮልቄ እንጂ ባይኔ በብረቱ! በአካልወስጋ…!? ከየት ተገኝቶ።

“የምንሄድበት ስቴዲየም በጣም ሩቅ ነው እንዴ አቶ ምሥጢረ?”

“ያን ያህልም አይደለም…170 ኪ/ሜ ነው። ከአዲስ አበባ አሰላ በለው…”

ቼኮሌት…ስዊዝ ባንክ…የአንድ ሚሊዮን ብር የእጅ ሰዓት…

ከዙሪክ ተነስተን ዋና ከተማዋን በርንን በግራ አ’ታለን አጋድመናት፣ ኒውሼትል ለመግባት ወደ 2፡00 ሰዓት ግድም ይወስድብናል። አቶ ምሥጢረ ‹‹ቢኤምደብሊው›› መኪናቸውን እየረገጧት ነው፤ ልክ እንደ ማንሲቲው ኬይል ዎከር

ከኋላ የማረን ታናሽ ቅዱስ ኃይለሥላሴ እና ወጣቱ አጎታቸው አማኑኤል በቀለ አብረውኝ ተቀምጠናል።

ባልና ሚስቱ ጋቢና የራሳቸውን ወግ ሲይዙ እኔም ለነ ቅዱስ ጥያቄ አነሳሁ…

“እኔ ምልህ ቅዱስ፤ እየሄድክ ኳስ ታያለህ? ትልልቅ ቡድኖችን?”

“ሜሲን፣ ሮናልዶን ሮናልዲንሆን ኔይማርን እየሄድኩ ጌማቸውን ኢመለከታሎ። ምሳሌ ሜሲን ባርሳ ከጁቬንቱስ ሻምፒዯንስሊግ ፋይናል ላይ ነበርኩ። እዚህ ማድሪድ ከዙሪክ ሲጫወት ሮናልዶን አይቼዋለሁ።” የቅዱስ አማርኛ በስዊዘርላንድ ቼኮሌት የተለበጠ ይመስል ይጣፍጣል።

“ማነው ግን ይበልጥ የሚማርክህ ተጨዋች”

“እኔ ኔማር አንደኛ”

የስፖርት ውርርድ አዲሱ የወጣቶች ሱስ ይሆን?

ወጣቱ አጎታቸው አማኑኤል ስለስዊዝ ሊግ ጥንካሬ፤ ሊጉ መሐመድ ሳላህን የመሳሰሉ ድንቅ ተጫዋቾችን ስለማፍራቱ አጫወተኝ። ሞባይሉን አውጥቶ ቅዱሥ ከዚህ ቀደም ያስቆጠራቸውን ጎሎች በተንቀሳቃሽ ምሥል አሳየኝ። ያን ጊዜ ቅዱስ በቴክኒክ የበሰለ ‘ፌንተኛ’ ተጫዋች መሆኑን መረዳት ቻልኩ።

ከአፍታ በኋላ ቀልቤን ወደ ጋቢና መለስኩ።

“ቅዱስዬ ለበጋ እረፍት ከባርሴሎና ዛሬ መምጣቱ ነው፤ ትንሽ አመም አድርጎታል። አማርኛ ጎበዝ ነው ግን አይደል?” ወ/ሮ ማክዳ ተቀበለችኝ፤

“በጣም እንጂ…እዚህ ተወልዶ ያደገም አይመስልም!”

“አይደል?”

“አዎ! ከጠበቅኩት በላይ ጎበዝ ነው”

ትንሽ ራሱን አመም ስላደረገው ተጨንቃለች። አሁንም አሁንም የሚጠጣ፣ የሚበላ ታቀብለዋለች።እሱ ግን በጄ አይልም።

“እኔምልሽ ማክዳ! ማረን ስንተኛ ጨዋታው ነው የሚያደርገው ዛሬ?”

“ማረንዬ ዛሬ ሁለተኛ ጨዋታውን ነው የሚያደርገው…ሱፐርሊጉ ገና መጀመሩ’ኮ ነው…”

“የመጀመርያውን ጨዋታ ገብታችሁ ነበር?”

“እንዴ! እኛ የትም ቢሆን ጌም ካለው ቀርተን አናውቅም። የትም…! አይደለም ስዊዘርላንድ…የትም…!”የሮቤርቶ ካርሎስን ቅጣት ምት በሚያስንቅ ፍጥነትና አጽእኖት ተናገረች። እናት ማክዳ!

ለኪሎ ሜትሮች ያህል በዝምታ ተጓዝን።

እነሱ አንድ ጊዜ ፕሪምየር ሊጉን፣ አንድ ጊዜ ላሊጋውን፣ አንድ ጊዜ ቡንደስሊጋውን ሲተነትኑት የኔ ዝምታ መልሶ እኔኑ አስጨነቀኝ። በነርሱ ወሬ ደማቅ ተሳትፎ እንዳላደርግ ደግሞ እግር ኳሳዊ ዕውቀቴ ሳሳብኝ።

“የመጀመርያህ ነው ስዊዘርላንድ ስትመጣ?” ዝምታውን ለመስበር ይመስላል፤ ጠየቁኝ።

“አዎ የመጀመርያዬ ነው!”

ሆኖም ለኔ አንድ ጥያቄ ወርውረው እነሱ ወደ ኳስ ወሬያቸው ይመለሳሉ።

የዙሪክ ቡድን ይፋዊ ፎቶ

የመኪና ወግ ከነ ወ/ሮ ማክዳ ጋር

“እንደማየው ለምለም አገር ይመስላል…በዚያ ላይ ተራራማ ነው።”

“አታውቅም እንዴ! ኢትዮጵያ የአፍሪካ ስዊዝ እንደምትባል?” አቶ ምሥጢረ ጠየቁኝ።

“የሰማሁ መሰለኝ”

“የአልፕስ ተራራ ሰንሰለት እንደምታየው ነው። የዚህ አገር ረዥሙ ተራራ ከራስ ዳሽን ይስተካከላል።”

“እያየሁት እኮ ነው! ዙሪያ ገባው ተራራ ነው…የተራራ አጥር…”

“ሌላ ልንገርህ….ተራራማነቱ የፈጠረው የቋንቋ ብዝኃነት አለ፤ በሁለቱም አገር። ኢትዮጵያ በአንድ ቋንቋ ውስጥ ብዙ ቀዬ (ዳያሌክት) ያላት አገር ናት። ለምን ይመስልሃል?

“እኔ እንጃ”

“ከዚህ ከተራራማነት ጋ ተያይዞ ነው፤ ከተራራ ማዶና ከተራራ ወዲህ አንድ ቋንቋ አይነገርም። ድሮ ኮሚኒኬሽን እንዳሁኑ አልነበረም፤ የጎንደር፣ የሸዋ፣ የወሎ አማርኛ ዳያሌክት የተፈጠረው…አንዱ በዚህ ምክንያት ነው።”

“እዚህም ብዙ ነው ቋንቋው አቶ ምሥጢረ?”

“ስዊዘርላንድ እንኳ 4 ቋንቋ ነው ያላት በዋናነት። ግን ብዙ ዳያሌክት ነው ያላት፤ ልክ እንደ ኢትዯጵያ…”

“ይሄን የፈጠረው ተራራማነቱ ነው የሚሉኝ”

“ትክክል”

እንደገና ዝም ዝም።

“ለምን እንዲህ አናደርግም?” ድንገተኛ ሐሳብ አቀረብኩ።

“ምን?”

“ስለስዊዘርላንድ በወሬ የሰማኋቸውን ነገሮች ልንገራችሁና እናንተ ደግሞ እውነት ስለመሆናቸው አረጋግጡልኝ…”

“አሁን ጥሩ ሐሳብ አመጣህ፤ እንዳውም መንገዱ ያጥርልናል…” ወ/ሮ ማክዳ ሐሳቤን በሙሉ ድምጽና በምንም ድምጸ ተአቅቦ ደገፈችው።

“ስንት ዓመት ሆነዎት ግን እዚህ ከመጡ፤ አቶ ምሥጢረ?”

“ዓመቱን እንኳ ተወው! በጣም ድሮ ነው…” (ሳቁ!) አሳሳቃቸው ዙሪክ ከመቆርቆሯ በፊት የመጡ ያስመስልባቸዋል።

“አቶ ምሥጢረ አንቱታውን ብተወው ቅር ይልዎታል?”

“እንዳውም ገላገልከኝ…”(በድጋሚ ሳቁ)።

የስፖርተኛ ተክለሰውነት ነው ያላቸው። አሰልጣኞች በልምምድ ጊዜ የሚለብሱት ቀለል ያለ ቱታ በጅንስ ነው ያደረጉት። ወግ ሆኖብኝ ነው እንጂ ምንም ለአንቱታ የሚሆን ገጽታ አላገኘሁም። ደግሞስ በተቃጠለ የኳስ ስሜት ወደ ካምቦሎጆ የሚሄድ ሰው አንቱ ይባላል እንዴ?

“በጣም ቆይተዋል/ቆይተኻል ማለት ነው እዚህ?” (አንቱታው አ’ለቅ አለኝ…)

“ኡ! በጣም…!”

እሺ በቃ ጥያቄዬን ልጀምር…(ማስታወሻዬን አወጣሁ)

“ስዊዘርላንድ ውስጥ ቡና ሲፈላ እንደ ዳቦ ቆሎ የሚቀርበው ቼኮሌት ነው የሚባለው እውነት ነው?”

ባልና ሚስት ከት ብለው ሳቁብኝ!

የስዊዝ ቼኮሌት፣ የስዊዝ ሰዓት፣ የስዊዝ ባንክ እየተባለ ወሬ ስለሚነዛ ያንኑ ማጋነኔ ነበር…።

(አንዳንዱ ነገር እንዳሰብኩት ግነት ብቻ አልሆነም፣ ታዲያ። ለምሳሌ በቀጣዩ ቀን 140ሺህ የስዊዝ ፍራንክ ተመን የተቀመጠበት የእጅ ሰዓት በዓለም ላይ ውድ ከሚባሉ ጉሊቶች አንዱ በሆነው ባንሆስትራሰ (Bahnhofstrasse) ጎዳና በአንድ ቄንጠኛ ሱቅ ውስጥ ማየቴን አንባቢ በግርጌ ማስታወሻ ቢይዝልኝ አልጠላም። ሰው እንዴት ‹‹ስንት ሰዓት ነው?›› ሲባል የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የእጅ ሰዓቱን ገልጦ ‹‹ለ2 ሰዓት ሩብ ጉዳይ›› ይላል?)

“አቶ ሚሥጢረ፣ የስዊዝ ባንክ ግን የቱ ጋ ነው ያለው?” የአህጉሬ አምባገነኖች ብር የሚያከማቹበትን መጋዘን በሩቁም ቢሆን ማየት ጓጉቻለሁ። ከጃንሆይ የልጅ ልጆች የተረፈም ካለ…

ነገ እናሳይኻለን…ግን ስዊዝ ባንክ የሚባል አንድ ባንክ የለም’ኮ። እዚህ አገር የደንበኞቻቸውን ምሥጢር የሚጠብቁ ብዙ ባንኮች ናቸው ያሉት። በተለምዶ ስዊዝ ባንክ እንላለን እንጂ…አንድ ባንክ አይደለም።

“እሺ ሌላ ጥያቄ፡- ስዊዘርላንድ ውስጥ የእንሰሳት የወሲብ ፍላጎት ለማክበር ሲባል አንድን ጾታ ብቻ ለይቶ ማሳደግ አይቻልም። ለምሳሌ ሴት ውሻ ካለ ወንድ ዉሻ…ወንድ ድመት ካለ ሴት ድመት አብሮ ማሳደግ ሕግ ያስገድዳል…እውነት ነው?”

ከት ብለው ሳቁብኝ! “አይ ይሄ ሐሰት ነው። የጎረቤታችን የነ እንትና ውሻ ብቻዋን ነው የምታድገው…ሲንግል መሰለችኝ…

ሌላ ጥያቄ፡-“የኑኩሌር ጦርነት ቢከሰት በሚል ሁሉም ስዊዘርላንዳዊ ዜጋ ሊደበቅበት የሚችል ዋሻ በየሰፈሩ አለ የሚባለውስ?”

“ልክ ነው፤ ዋሻዎች (Bunkers) በየሰፈሩ አሉ።”

ሌላ ጥያቄ፡- “አልበርት አንስታይን የአንጻራዊ ሕግ [ሪላቲቪቲ ቲዯሪን] የቀመረው እዚህ ነበር?”

“ይሄም ልክ ነው፤ እዚህ ዙሪክ ዩኒቨርስቲ ያስተምር ነበር። በነገርህ ላይ ኖቤል ካሸነፉት ሰዎች ብዙዎቹ ከዙሪክ ነው የወጡት። ካልተሳሳትኩ 12 የሚሆኑት…ከዙሪክ ዩኒቨርስቲ ናቸው።

መንገዱን እንዲህ እንዲህ እየተጨዋወትን ተሲያት ላይ ኒውሼትል ደረስን።

እዚያም ስታዲየም ሰልፍ አለ

ኒውሼትል ከተማ ስንደርስ በጩኸታዊ ዝማሬያቸው ከቡና ደጋፊ ጋር የሚመሳሰሉ፤ በቁመታቸው “የስታዲየም ዳፍ” የሚያካክሉ የያንግ ቦይስ ደጋፊዎች መንገዱን ሞልተውታል። የሚያወጡት ድምጽ ጎርናና በጣም የሚያስፈራ ነው። ቆመን አሳለፍናቸው። ኋላ ቢደበድቡንስ…

ማክዳና ምሥጢረ የዓመት መግቢያ ነበራቸው፤ እኔ ግን ስላልነበረኝ ለትኬት መሰለፍ ተገደድኩ። ትኬት በወንበር ቁጥር ጋር መዛመድ ስላለበት ከቤተሰቡ ጋር ለመቀመጥ አስቸጋሪ ሆነ። በኋላ ላይ አቶ ምሥጢረ መላ መታ።

“የቢቢሲ ጋዜጠኛ የሚል መታወቂያ ይዘኻል?”

“አዎ!”

ትኬት ቆራጮቹን በአገሬው ቋንቋ አነጋገራቸው። ተባበሩን። ከቤተሰቡ ጋ እንድመለከት በ82 የስዊዝ ፍራንክ ትኬት ተገዛልኝ።

እናትና አባት በኒውሼትል ስታዲየም

ልጃቸው ቅዱስ፣ አጎታቸው አማኑኤል፣ እና እኔ በስታዲየሙ ተሰይመናል። በአዲስ አበብኛ ጥላ ፎቅ ነን። ለዚያም ቀኝ ጥላ ፎቅ።

አዲስ አበባ ቢሆን ግን አቶ ምሥጢረ በፍጹም ቀኝ ጥላ ፎቅ አይቀመጡም ነበር። ድሮ ቀንደኛ የሳንጃው ደጋፊ ነበሯ። …እንዲያም እነ ማረን ወደ ሜዳ እስኪገቡ ለምን በአጭሩ በርሳቸው የድሮ ታሪክ አናሟሙቅም?

“መንግሥቱ ወርቁ ሜሲዬ ነበር” አቶ ምሥጢረ ኃይለሥላሴ

“አንዳንዴ ጸሎቴ ተሰምቷል እላለሁ። ለምን መሰለህ…ገና ድሮ ሁለት ነገር እመኝ ነበር፤ ወንድ ልጆች እንዲኖሩኝና ኳስ ተጫዋች እንዲሆኑ። ሁለቱም ተሳክተውልኛል።

በልጅነቴ ኳስ ወዳጅ ነኝ፤ እንደ ልጆቼ ግን የተመቻቸ ነገር አልነበረም። እንደምታውቀው ድሮ የኳስና የክት ጫማ ብሎ ነገር እንኳ የለም። ወደ ትምህርት ቤት በሄድንበት ጫማ እንጫወታለን። ጫማው ይንሻፈፋል፤ እንገረፋለን። በዚያ ላይ ኳስ መውደዳችን በትምህርት ላይ ተጽእኖ ነበረው። በኛ ጊዜ ትምህርት የሕይወት አልፋና ኦሜጋ ነበር።

በኔ ጊዜ ስለ ኢንተርናሽናል ጨዋታ መረጃ ማግኘት በራሱ ከባድ ነበር። በሳምንት አንድ ጊዜ የሚወጣ ‹‹ስፖርት ፋና›› የሚባል ጋዜጣ ትዝ ይለኛል። ስለነፔሌና ጋራንቻ ሞቅ ተደርጎ ይወራ ነበር። ..

ከማስታውሰው ልንገርህ፤ ‹‹ፔሌ የመታው ኳስ ማዕዘን መልሶበት አንግሉ ይለካልኝ አለ›› ተብሎ ይጻፋል። እውነት ነበር የሚመስለን።

የዲኤንኤ ነገር ይሆን ታዲያ ዛሬ በሁለት ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የተባረከው?” ጥያቄ አነሳሁ።

አላውቅም፤ ሊሆን ይችላል፤ በነገርህ ላይ እዚህ ኳስ ልጆቹን ከአልባሌ ነገርም ይጠብቃቸዋል። ከትምህርት መልስ ልምምድ ነው ቤት ነው። ለአጓጉል ነገር ጊዜም የለም።

“ሌላ ምን ትዝ ይልኻል ከድሮ?”

“ምን ትዝ የማይለኝ አለና! እንዲያውም ስላለፈው ዓመት ከምትጠይቀኝ የዛሬ 40 ዓመት የነበረውን ብትጠይቀኝ ከነ ደቂቃው እነግርኻለሁ…።

በዚያን ጊዜ ጊዮርጊስ ባርሴሎናዬ ነበር። መንግሥቱ ወርቁ ሜሲዬ ነበር። አንዳንዴ ኢትዮጵያ መሆኑ በድሎታል ብዬ አስባለሁ። አሁን እነ ማረን የሚያገኙትን ልምምድ ቢያገኝ መንግሥቱ የት በደረሰ? መንግሥቱ እኮ የእግዚአብሔር ስጦታ ነበር። በቁመቱ ረዥም አልነበረም፤ የዝላይ ብቃቱ፤ የትኛው የአፍሪካ ተከላካይ ያቆመው ነበር? ንገረኝ…የትኛው…”

እነ ሸዋንግዛው አጎናፍር፣ ፍሰሐ ወልደአማኑኤል፤ እነ አዋድ… ለአገራቸው በቀን 5 ብር አበል እየተከፈላቸው የተጫወቱ ባለውለታ ናቸው። ነፍሳቸውን ይማርና ክቡር ይድነቃቸው ያን ጊዜ ፕሮፌሽናሊዝምን ይጸየፉ ነበር። የአማተሪዝም አቀንቃኝ ነበሩ። ለአገርህ ነው የምትዋደቀው። ኳስ ዛሬ የቢሊዮን ዶላር ኢንደስትሪ ሆኗል…እንደምታየው። ያኔ ግን…”

“አንተ ግን ለየትኛው ቡድን ተሰልፈኻል ድሮ?”

“…የጊዮርጊስ ደጋፊ ብቻ አልነበርኩም፤ የጊዮርጊስ ተጫዋችም ነበሩ። በዚህ ምክንያት በልጅነቴ ስቴዲየም ዘንጬ ነበር የምገባው።

“…በዚያ ዘመን ለልጆች ስታዲየም መግባት “ግመል በመርፌ ቀዳዳ…” እንደማለት ነው። ጋሼ ይዘውኝ ይግቡ ተብሎ መለመን የተለመደ ነበር። እኔ ግን ያኔ ቴሴራ የሚባል ነጻ መግቢያ ነበረኝ። ቴሴራውን ወደ ካምቦሎጆ መግባት ላልቻሉ እያቀበልን ሁሉ ገንዘብ ሸቃቅለንበታል፤ ይሄ ታዲያ በ60ዎቹ መጨረሻ ነው።

አቶ ምሥጢረ ያኔ አንተ ያጣኸውን ነገር አሁን በልጆችህ እየተበቀልከው ይመስልኻል?

“መበቀል ሳይሆን መ’ካስ ልትለው ትችላለህ” (ሳቀ)

ከአቶ ምሥጢረ ጋር እየተጨዋወትን የያንግ ቦይስ ቡድን ለማማሟቅ ወደ ሜዳ ገባ። ስታዲየሙ መሙላት ጀምሯል።

የያንግ ቦይሶቹ “አቻኖ” እና «አዳነ» በፈረንሳይኛ ሕዝቡን ያስጨፍሩታል። ዝማሬው የሆነ የሚነዝር ነገር አለው። እነ ማረን ወደ ሜዳ እስኪገቡ ወደ እናቱ ማክዳ በቀለ ዞርኩ።

“ልጆቼ ኳስ ሲያቀበል ለማየት ስታዲየም እገባ ነበር” ወ/ሮ ማክዳ

“አንድ ነገር ልንገርህ?

“…ማረንና ቅዱስ ኳስ አቀባይ ነበሩ፤ ኳስ ማቀበል ራሱ የሚገኝ ዕድል መሰለህ? ዋናው ቡድን ሲጫወት እነሱ ኳስ ያቀብሉ ነበር፤ ትዝ ይለኛል የመጀመርያ ቀን ማረን በ18 ዓመቱ ለብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ኳስ ያቀብላቸው ከነበሩት ተጨዋቾች ጋር ሲጫወት ሳይ በደስታ አለቀስኩ።

አስበው፤ እሱ ቲኒሽዬ ልጅ ነበር። ኳስ ሲያቀብላቸው የነበሩት ጋ ተሰልፎ ሲጫወት ማየት እንዴት አያስለቅስም?

አሁን እኮ ተጫውቶ ከሜዳ ሲወጣ የሱን ቲሸርት ለመውሰድ፣ ፊርማውን ለማግኘት ልጆች ሲረባረቡ ስታይ….አስበው… ብቻ እግዚአብሔር የሚሳነው የለም።

አስተዳደጋቸውን አጫውችኝ እስቲ…

ማረን ኳስ አካዳሚ የጀመረው በ8 ዓመቱ ነው። ቅዱሥ ደግሞ በ6 ዓመቱ። ቅዱስ ኳስ ሲጀምር ከሚያንከባልላት ኳስ ራሱ በትንሹ ነበር የሚበልጣት።

ማረን በ7 ዓመቱ ሰፈር ውስጥ ሲጫወት ተሰጥኦ አዳኞች መጥተው አዩትና ወዲያው ቅድመ-ኳስ አካዳሚ አስገቡት። ቅድመ-አካዳሚ ከ9 በታች የሆኑ ልጆች የሚገቡበት የመሰናዶ ኳስ ትምህርት ቤት ነው።

ቅዱስ ግን ያኔ 5 ዓመቱ ነው፤ ኳስ ደግሞ የሚጀመረው በ7 ዓመት ነው፤ ሆኖም ማረንን ለማየት ይሄድ ስለነበር ወንድሙን ማየት ሲሰለቸው ትርፍ ኳስ ይዞ ዳር ላይ እያንጠባጠበ ትኩረት ሳበ።

አንድ አሰልጣኝ የዚህን ልጅ ወላጆች አገናኙኝ አለ። አቤት! አልን። ይሄ ልጅ እዚህ እየመጣ እንዲለማመድ እንፈልጋለን፤ አያያዙ ተስፋ የሚሰ ነው አሉ። በዚያው የኳስ መዋሕጻናት [football Kindergarten] ገባ።

በ5 ዓመቱ የጀመረ አሁን ከ18 በታች ለዙሪክ ቡድን ይጫወታል። ያም ብቻ ሳይሆን ለስዊዘርላንድ የታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ይሰለፋል።

ቅዱስ ደግሞ 2014 ሻምፒዯንስ ሊግ በርሊን ጁቬንቱስ ከባርሳ ሲጫወቱ ተጋብዞ ሄዶ ነበር። እሱ ብቻ ሳይሆን የሱ ቡድን ያኔ 13 ዓመቱ ነው፤ ሄዶ ነበር።

ከእንግሊዝ የቼልሲ የሴቶች ቡድን ጋር ሁሉ ግጥሚያ አድርገዋል። ሕጻናት ነበሩ። የነ ቅዱስ ቡድን 23 ለ 1 በሆነ አስቂኝ ውጤት ሲያሸንፍ ቅዱስ 8 ጎል አግብቶ ጋዜጣ ላይ ሁሉ ወጥቶ ነበር። ከዚያ የነቅዱስ ቡድን 2ኛ ወጥቶ ተሸለመ። ትንሹ ቅዱስ ሽልማቱን ከትልቁ ፍራንስ ቤከን ባወር እጅ ተቀበለ።

በአጭሩ ሕይወቴን ልንገርህ? ከሆኑ ዓመታት በፊት ስዊዘርላንድ ለትምህርት ሄድኩ፤ ትዳር መሠረትኩ፤ እነ ማረን ተወለዱ፣ ሕይወቴ እነሱ ሆኑ፤ አብሬያቸው አደግኩ ብልህ ይቀለኛል።

የኳስ መዋዕለ ሕጻናት

ወ/ሮ ማክዳ የስፖርተኛ ልጆች እናትም አይደለች? ንቁና ቀልጣፋ ናት። ትንሹን ቃለዓብን አራስ እያለች፤ እሱን በፈረንጅ አንቀልባ (ጨቅላ ጋሪ) እየገፋች፣ ቅዱሥን ደግሞ በጎን ድክ ድክ እያለ (ያኔ እሱ ራሱ ኳስ ነበር የሚያክለው)፣ ወደ መለማመጃ ሜዳ ትሄዳለች። ያን ጊዜ ማረን ተስፋ የሚጣልበት አዳጊ ነበር። በየቀኑ ልምምድ ሜዳ መሄድ አለበት።

ያን ጊዜ ትንሽ ልጅ የነበረው ቅዱሥ ታዲያ ታላቅ ወንድሙ ማረን ልምምድ ሲያደርግ ቁጭ ብሎ መመልከት ይሰለቸዋል። ብርር ብሎ ይሄድና ከተደረደሩ ብዙ ኳሶች ውስጥ አንዱን አንስቶ ያንቀረቅባል። (Eis, Zwoi, Dru…) 1…2….3… እያለ፤ በስዊዝ ጀርመንኛ…

የማረን አሰልጣኞች ከኳሷ ጋር ቅዥቅዥ የሚለውን ትንሹን ቅዱሥ ይመለከቱታል። በየቀኑ። ይህን ልጅ እስኪ እንየው ብለው ያለጊዜው አስጀመሩት።

ስዊዘርላንድ ትምህርት ነጻ ነው፤ ልጅን የእግር ኳስ ትምህርት ቤት ማስተማር ግን በጣም ውድ ነው። እነዚህ ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርታቸው ይለያል። ልክ ሙያ ለመማር ተግባረ እድ እንደመግባት ነው። የቀለም ትምህርትና የኳስ ትምህርትን አጣምረው ይሰጣሉ። የነማረን ወላጆች ለዚህ ትምህርት ቤት የሚከፍሉት ፍራንክ ቆንጠጥ ቢያደርጋቸውም አላፈገፈጉም።

በነዚህ ትምህርት ቤቶች ተጫዋቾች ለጌም ውጭ አገር ቢሄዱ ልጆቹ ትምህርት አመለጣቸው አይባልም። መጀመርያውኑ የትምህርት መርሃግብሩ ከኳስ የውድድር መርሃግብር ጋር የተስማማ ነው። ማረን ከዚህ ትምህርት ቤት በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ዲፕሎማ ይዟል።

ማረን አሁን ለብሔራዊ ቡድን ይጫወታል። ሳምንት ለንደን ቆይቶ ይመጣል። ትምህርት አመለጠው፣ ፈተና አለፈው፤ ወይኔ ጉዱ ፈላ አይሉም፤ ወላጆቹ። ምክንያቱም ‹‹ቢዝነስ ፉትቦል›› ትምህርት ቤት ስለሚማር።

18 ዓመት ሲሞላው ክለቡ በተማረው ትምህርት የሥራ ልምምድ (ኢንተርኒሺፕ) ባንክ ውስጥ ነበር የጀመረው። በኋላ የኤፍሲ ዙሪክ ክለብ ባለቤትና ፕሬዝደንት ማረንን እጅግ ስለሚወዱት እኔ ኩባንያ ውስጥ ይሥራ፤ እንደፈቀደው ወጥቶ እንዲገባ ብለው ፈቀዱለት። አንቺሎ ካሌፓ ይባላሉ።በጣም ነው የሚወዱት ብለውኛል ወላጆቹ።

እንዲህ እንዲህ እያለ ማረን አሁን የደረሰበት ደረጃ የደረሰው…

ማንቼ ለምን ደጅ ይጠናል ታዲያ?

ብዙዎቹ ግዙፍ ክለቦች “ፉትቦል ስካውት” የሚባሉ ተሰጥኦ አዳኝ መኮንኖች አሏቸው፤ በተለይ ባለፈው ዓመት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች እነ ምሥጢረ ጋር ደጅ የጠኑበት ዓመት ነበር። ‹‹ልጃችሁን ለክለባችን›› ተብለዋል። ከአንዴም ሁለት ሦስቴ።

ሆኖም የታፈሩ የኳስ ሽማግሌዎችን እምቢኝ ብለው መልሰዋል። ባልና ሚስቱ ይህንን ሲነግሩኝ ለማመን ተቸገርኩ።

“እንዴት ለማንቼ እምቢ ይባላል?” በወላጆቹ ድርጊት ተናደድኩ። በአጠያየቄ ትንሽ ስሜታዊ ሳልሆን አልቀረሁም መሰለኝ…የጉዳዩን ውስብስብነት ተረጋግተው ያስረዱኝ ጀመር፤ ባልና ሚስቱ።

አንድ ቡድን አንድን ታዳጊ ተጨዋች ፈለገው ማለት ወዲያውኑ ተሰልፎ መጫወት ይጀምራል ማለት እንዳልሆነ፤ ማሳደጊያ ውስጥ ገብቶ በዚያው ቀልጦ መቅረትም እንዳለ…ልጅን አሳልፎ ከመስጠት በፊት ብዙ ጥንቃቄዎች እንደሚያስፈልግ አብራሩልኝ።

የምናውቃቸው አንድ ሁለት ልጆች አሉ፤ ማንችስተር የሄዱ የማረን ጓደኞችም አሉ። ብዙም አልተሳካላቸውም፤ ተመልሰው ይመጣሉ።በዚህ ዕድሜያቸው ሄደው ከሚባክኑ ትንሽ እዚሁ ቢያድጉ መረጥን። አሰልጣኞቻቸውንም ስናማክር እንደዚያ ነው ያሉን…።

ከዘረዘሩልኝ ምክንያቶችም ባሻገር እናታቸው ልጆቹ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ፤ በዕድሜም ትንሽ ከፍ ሳይሉ እንዲርቋት እንደማትፈልግ ተረድቻለሁ።

ከቡንደስሊጋ የመጡና የጠየቁም ነበሩ፤ በየጊዜው ማረንን እኛ ወስደን እናሳድገው ይሉናል…።

“አያጓጓችሁም ታዲያ? “እኔ ብሆን ባንዳፍ” ነበር የምላቸው”

“በእርግጥ ቡንደስሊጋ አጓጊ ነው። መልማዮቹ ቀስ ብለው እኛን ወላጆቻቸውን ነው የሚያግባቡት፤ ጉጉታችንን ስለሚያውቁ። ብዙዉን ጊዜ ደላሎች ገንዘባቸውን ነው የሚያዩት…” አቶ ምሥጢረ አስረዳኝ። እሱ ሲጨርስ ደግሞ ማክዳ ማብራሪያ አከለች።

“ማረንና ቅዱስን ማናጀር እንሁናቸሁ የሚላቸውም ብዙ ነው፤ ያው እነሱም ሲሳካለቸው እንጀራቸውን ለመጋገር ነው። ትልልቅ ክለቦች ለኛ ስጡን ብለው ሲያነጋግሩን እና በራሳችን ብቻ አንወስንም። ከነማረን ማኔጀሮች ጋር በስፋት እንመካከራለን። ለአሁኑ ጊዜው አይደለም በሚል አቆይተናቸዋል። ወደፊት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆነውን ማየት ነው…”

ማረን እና ቅዱስ ስለ ኢትዮጵያ ያስባሉ?

የጋመ ኢትዮጵያዊ ስሜት ካላቸው ወላጆች የተገኙት ማረንና ቅዱስ ትኩረታቸው ገናና ክለብ ውስጥ ገብቶ ውጤታማ መሆን ነው። ስለኢትዮጵያ በጠየቅኳቸው ጊዜ የኢትዮጵያን ኳስ እንደማያውቁ ተረድቻለሁ። የኢትዮጵያን ማሊያ ለብሰው እንዲጫወቱ ግን የአባትየው ጥልቅ ፍላጎት ነው። የፓስፖርት ጉዳይ ራስ ምታት መሆኑ እንደማይቀር ግን ከወዲሁ ይገምታል።

“ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቢጫወት ህልሜ ነው፤ ሆኖም የድርብ ዜግነት ጉዳይ መፍትሄ ማግኘት አለበት። ቀናነትም ያስፈልጋል። ዘንድሮ የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነውን የአልጄሪያን ብሔራዊ ቡድን ውሰድ፤ 90 ከመቶ የሚሆኑት ተጨዋቾች ውጭ አገር ተወልደው ያደጉ ናቸው።” ይላል አቶ ሚስጢረ።

ማረን እና ቅዱስ አሁን ጥሩ ተከፋይ ተጫዋቾች ናቸው። ኢትዮጵያ ባይወለዱም ስለ ኢትዮጵያ ያስባሉ። ገና በልጅነታቸው በጎ አድራጎት ውስጥ ገብተዋል።ማረን 2 ልጅ፤ ቅዱስ አንድ ልጅ ወጪ ችለው ያስተምራሉ። በአዲስ አበባ።

እግአብሔር በዚህ ዕድሜያችሁ የማይታመን ነገር አደረገላችሁ፤ እንደናንተ የመማር ዕድል ላላገኙ ኢትዮጵያዊ ጓደኞቻችሁ ምን ታስባላችሁ? ስላቸው ነው ይህንን በጎ ተግባር የጀመሩት “ ትላለች እናት ማክዳ።

ከለላ የሚባል የልጆች ቡድን ደግሞ አለ፤ አዲስ አበባ። በዚህ የሰፈር ቡድን ውስጥ አንዳንዶቹ ልጆች ካለ ጫማ በባዶ እግር ሁሉ ኳስ ይጫወቱ ነበር። እነ ማረን ወደ 40 አዳዲስ ታኬታ የተለያየ ቁጥር አሰባጥረው ላኩላቸው። ልጆቹ በጣም ደስ አላቸው። እሱን ለማመስገን ለማረን ልደቱ ኬክ ቆርሰው ‹‹ሀፒ በርዝደይ ማረን›› እያሉ ቪዲዮ ላኩለት።

“ኢትዯጵያዊያን ኳስ ውስጣችን ነው። ያም ሆኖ ትልቅ ደረጃ የደረሰ ተጫዋች አልወጣልንም። የኔ ልጆች የሆነ ቦታ ቢደርሱ ለስንት ልጆች አርአያ ይሆናሉ እያልኩ አስባለሁ። በዚህ ረገድ እግዚአብሔር ቀዳሚ ያደርጋቸዋል ብዬም አስባለሁ።” ይላል አቶ ምሥጢረ።

“ትእግስትን የተማርኩት ከቤተክርስቲያንም በላይ ከኳስ ሜዳ ይመስለኛል” ወ/ሮ ማክዳ

ባልና ሚስት የልጆቻቸውን ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የጀመርን ሊጎችንም በአንክሮ ይከታተላሉ።

ባየርሙኒክና ዶርትሙንድ እና ሌሎች የቡንደስሊጋ ውድድሮችን ከዙሪክ እየነዱ አንዳንዴም በአውሮፕላን በረው እየታደሙ ይመለከታሉ።

“እዚህ ያው ጊዜ የለም። ሆኖም ግን ቅዳሜና ሑድ ልጆቻችን ኳስ ግጥሚያ ከሌላቸው ይጨንቀናል።” ትላለች እናት ማክዳ።

እሑድ እሑድ ከቤተክርስቲያን መልስ ሁልጊዜም ወደ ኳስ ነው።

“አንዳንድ ጊዜ ትእግስትን የተማርኩት ከቤተክርስቲያንም በላይ ከኳስ ሜዳ ይመስለኛል። መሸነፍን የማልቀበል ሴት ነበርኩ። እንዴት ተሸነፍኸው ትመጣለህ ስለው ማረንን፣ “ማሚ እነሱ እኮ በልጠውን ተጫውተዋል” ሲሉኝ ” አሃ ለካስ ሽንፈትን መቀበልም አለብኝ ማለት ጀመርኩ። ኳስ ምን ያላስተማረኝ ነገር አለ? ሁሌ ማሸነፍ እንደሌለ..ታጋሽነትን…”

“ጀርመን ያልሄድነበትን ቦታ ጠይቀኝ፤ ክረምት የአዳራሽ ጨዋታ አላቸው። ኮሎን ድረስ 14 ሰዓት ደርሶ መልስ እየነዳን ሁሉ እናያቸው ነበር። ሆቴል ነው የምናርፈው ወጪው ብዙ ነው፤ ብዙ ሰዓት ነው የምንነዳው፤ ግን ደስታው ይበልጣል፤ ልጆቻችንን ማየት ትልቅ ፍሰሀ ይሰጣል።” ይላል አባት ምሥጢረ።

ማክዳ በበኩሏ “እኔ ማንችስተርን ከማይ ቅዱስ ጌም ሲያደርግ ማየት የበለጠ ደስታን ይፈጥርልኛል፤ አንደኛ ቅዱስ ተአምር ሳይሰራ አይወጣም።” ትላለች።

ስዊዝሊግ መጫወት ብርቅ ነው እንዴ?

የስዊዝ ሊግ በአውሮፓ ደረጃ መካከለኛ ከሚባሉት ነው። የስዊዝ ብሔራዊ ቡድን በኮካ ኮላ ደረጃ ሰንጠረዥ (ራንኪንግ) እስከ ሆነ ጊዜ ድረስ ከምርጥ አምስት ውስጥ ነበር፤ ለብዙ አመታት። ከነብራዚል ሁሉ ይበልጥ ነበር። በዚህ ዓመት ነው 11ኛ የወረደው ይላል አቶ ምሥጢረ።

ለመሆኑ ከዚህ ሊግ ወጥተው ገናና የሆኑ አሉ?

“በጣም ብዙ…”ማክዳ መለሰች፤ “ለምሳሌ መሐመድ ሳላህ ከዚሁ ከባዝል ነው የመጣው።”

“…ሻኪሪ ብትል፣ ሻካ የአርሴናሉ ከዚህ ነው የሄደው። ኢሚዲ ፣ ራኪቲቺ የባርሴሎናው…ሮልድሪገንስ ሚላን…

በተለይ በተለይ ቡንደስሊጋ ውስጥ በጣም ብዙ ተጨዋቾች አሉ።

ማረን እያታለለ ነው…

ኒውሼትል ስታዲየም ጥላ ፎቅ ተቀምጠናል። እኔና የማረን ቤተሰብ።

ሰዓቱ ደርሶ አሰላልፍ በድምጽ ማጉያ ሲገለጽ ማረን ዋና ተሰላፊ እንዳልሆነ ታወቀ። በወላጆቹ ፊት ላይ ቅሬታ ያየሁ መሰለኝ። ወይም አላየሁ ይሆናል…ብቻ አልተሰለፈም። የኔም ድካም አፈር በላ።

‹‹ እንደነገርንህ በተውሶ ስለሆነ የመጣው ገና እየሞከሩት ነው ያሉት…ተቀይሮ መግባቱ አይቅርም…›› አሉኝ፤ እያጽናኑኝ ይሆን? ወይም እየተጽናኑ?

እንዳሉትም ከእረፍት መልስ ከተቀያሪ ወንበር ድንገት ብርር ብሎ ተነስቶ ማሟሟቅ ጀመረ። ማክዳ ልቧ ተንጠለጠለ…‹‹ማሪዬ!›› ተጣራች።

በዚህ ጉጉት መሐል ተከታታይ ጥያቄ መሰንዘር ጀምርኩ። ዐይኗን ከማረን ሳትነቅል ታወራኛለች….

“እኔምልሽ ማክዳ! ልጅሽ ጎል ሲያስቆጥር ምንድነው የሚሰማሽ?

ምን ዓይነት ጥያቄ ነው የምትጠይቀኝ?” በሚል ለአፍታ ዞራ ተመለከተችኝ።

“ማለቴ እንደ እናት ከባድ ይመስለኛል…” ራሴን ቶሎ አረምኩ።

“በጣም ነዋ የምደሰተው…የሱ ክለብ ኤፍሲ ዙሪክ ትልቅ ቡድን ስለሆነ ማሸነፍ የለመደ ነው። እሱ ገና ኳስ ሲይዝ ደጋፊው በጩኸት ነው የሚያግዘው…ጎ…በዝ ነው ብታይ…።

በድምጽ ማጉያው ‹‹ኃይለሥላሴ….!›› የሚል ድምጽ ሲስተጋባ ደጋፊዎች በታላቅ ጩኸትና ዝማሬ ተቀበሉት። ማረን ተንደርድሮ ወደ ሜዳ ገባ።

‹‹ማርዬ! አይዞን!››

“ለምሳሌ ልጅሽ ማረን ኳስ ሲይዝ ጭንቅ አይልሽም?” ጠልፈው እንዳይጥሉት… ምናምን?”

“አሁን’ኮ እንደሱ አይነት ስሜትን አልፌዋለሁ። ድሮ ነበር…ልጅ እያለ። አሁንማ አጣጥፏቸው እንደሚሄድ ስለማውቅ(ሳቀችና አሳቀችኝ)

ከድሮም ኳስ ትወጂ ነበር ግን?

ረ እኔ ማንቼ አርሴ ከሚሉት አልነበርኩም! ማረንዬ ኳስ መግፋት ሲጀምር ነው በልጄ ውስጥ ‘ፉትቦል’ እያፈቀርኩ የመጣሁት…”

አሁን ማክዳ የለየላት የኳስ ተንታኝ መሆን ይቃጣታል፤ ተደራቢ አጥቂ አምጥቶ በ ‘ካውነተር አታክ’ ነበር ‘ፈርስት ሃፍ መጨረስ የነበረበት’ ምናምን ትላለች።

በጨዋታ መሀል ሌላ ጥያቄ ሰነዘርኩ። ልቧ እንደሁ ልጇ ጋ ሄዷል። ጮክ ካላልኩ አትሰማኝም።

“ልጅሽ ግን ምነው ኮሰስ አለ፤ እያቸው ጓደኞቹን ምን እንደሚያካክሉ…ማረን ደቃቃ ነው…አታበይውም እንዴ?” በነገር ጎነተልኳት።

በግማሽ ልብ ወደኔ ዞራ ተኮሳትራ ካየችኝ በኋላ…“…የኔ ልጆች የጭንቅላት ተጫዋቾች ናቸው እሺ!” አለችኝ።

ነገሩ ከነከናት መሰለኝ ኳስ ወደ ውጭ መውጣቱን ተመልክታ ፋታ ስታገኝ ማብራሪያ አከለችልኝ…።

“የኔ ልጆች ማረንም ቅዱስም ጥበበኞች ናቸው፤ ፈጣን ጭንቅላት አላቸው፤ ካላመንክ አሰልጣኞቻቸው ጠይቅ። እንደዚያ ነው የሚሏቸው። ኳስ ጉልበት ብቻ አይደለም…።”

ማክዳ ከክለብ የዶርትሙንድ፣ ከተጫዋች የሜሲ ደጋፊ የሆነችውም በነርሱ ውስጥ ልጇ ማረን ስለሚታያት ይሆናል። ማረን ቢጫወት ደስ የሚላትም ወይ ላሊጋ ወይ ቡንደስሊጋ ውስጥ ነው።

አቶ ምሥጢረም የባለቤቱን መንገብገብ አይቶ ነው መሰለኝ እሷን ደግፎ ተናገረ፤

“በእርግጥ የሰውነት ግዝፈት አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም ግን የግድ አይደለም። የኔ ልጆች ለምሳሌ ጥበባቸውና በፍጥነታቸው ከመጀመርያው ረድፍ የሚመደቡ ናቸው፤ እዚህ አገር “እሽፒል ኢንተለጀንስ” ይሉታል። ጨዋታን ቀድሞ ማንበብ። ያን የታደሉ ናቸው። ማረንን በዚህ ረገድ ሁሉም አሰልጣኝ የሚመሰክርለት ልጅ ነው።

የማረን ቡድን አንድ ለባዶ ተሸነፈ

ማረን ኃይለሥላሴ መልከ ቀና፣ ለግላጋ ወጣት ነው። ግሩም የግብ ሙከራ አድርጎ፣ አልያም ጎል አስቆጥሮ፣ አልያም ኳሷ ለጥቂት የግብ ማዕዘን ስትገጭበት የሚያሳየው ፈገግታ መለስተኛ የስታዲየም ፖውዛ ነው፤ በእርግጥ ይህ ዓረፍተ ነገር ተጋኗል። የማረን ፈገግታ ግን አልተጋነነም።

በኔ እይታ ሜዳ ላይ በቆየበት አጭር ደቂቃዎች እጅግ ማራኪ እንቅስቃሴን አሳይቷል። ደጋፊውም በከፍተኛ ጩኸት ድጋፉን ገልጾለታል። ተደራቢ አጥቂ ነበር። ጨዋታው ሊጠናቀቀ ጥቂት ደቂቃዎች በቀሩት ጊዜም አንድ ያለቀለት ግሩም ኳስ አቀብሏል። ምን ዋጋ አለው…።

ልክ 90ኛ ደቂቃው ላይ ፊሽካ ሲነፋ ማረን ሮጦ መልበሻ ክፍል አልገባም። ዓይኖቹ ወደ ክቡር ትሪቡን ያማትራሉ። ወደ ወላጅ እናቱ ማክዳ ይንከራተታሉ። አቶ ምሥጢረና ወ/ሮ ማክዳ ተንደርድረው ከወንበራቸው ይነሱና የትሪቡኑን ደረጃ ጥንድ ጥንዱን እየዘለሉ ተመልካችና ተጫዋችን የሚያግደው አጥር ላይ ይደርሳሉ።

“ማረንዬ! ዛሬ ደግሞ ልዩ ነበርክ” ትለዋለች እናቱ።

“አንበሳ የኔ ልጅ” ይሉታል አባቱ አቶ ምሥጢረ።

እሱ ምንም አይልም። ፈገግታውን ይመግባቸዋል። ዐይናፋር ሳይሆን አይቀርም። ዐይናፋርነቱ በንኖ የሚጠፋው ከባለጋራ በረኛ ሲገናኝ ብቻ ነው ትላለች እናቱ።

እኔም ተከትያቸው ወረድኩ። ከአገር ቤት የመጣሁ ጋዜጠኛ መሆኔን ጠቅሼ አጭር ቃለ ምልልስ እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት። ብዙም አልተስማማም። እያቅማማ አማርኛም እየቸገረው ‹‹ጥሩ ጌም ነበር፤ አቻ መውጣት ነበረብን። ያንግ ቦይስ ግን ከባድ ቡድን ነው›› አለኝ።

“ለምንድነው 90 ደቂቃ ያልተሰለፍከው? አልኩት።

“እሱን የሚመልስ አሰልጣኝ ነውአኔ የለም አለኝ ከትሁት ፈገግታ ጋር።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጫወት ሕልም አለህ? አንድ ቀን…።

“እኔንጃ…እኔ መናገር አላውቅም”። (ምናልባት ‘በእኔ ፍላጎት የሚወሰን ነገር አይደለም ማለቱ መሰለኝ)

ሁላችንንም ቻው ብሎን ወደ መልበሻ ክፍል እየሮጠ ገባ። ፈገግታውን ታቅፈን ቀረን።

ድኅረ ታሪክ

ወደ ናይሮቢ የቢቢሲ ቢሮ ተመልሼ ይህን ዘገባ ለድረ-ገጽ ኅትመት ከመስደዴ በፊት ወደ ዙሪክ የመጨረሻ የጽምጽ መልእክት ሰደድኩ፤ ‹‹ምን አዲስ ነገር አለ?›› የሚል።

“አንተ ከተመለስክ በኋላ ማረን አስደናቂ አቋም እያሳየ ነው፤ ባለፈው ከFC Thun ቡድን ጋር በነበረው ጨዋታ 3-2 ሲያሸንፉ የማሸነፊያዋን ጎል ማን ያስቆጠረ ይመስልኻል?”

“ማረን ኃይለሥላሴ?”

በትክክል!”

“ሌላም ዜና አለ፤ ታናሹ ቅዱስ ኃይለሥላሴም ለZurich FC ለመጫወት በይፋ ፊርማውን አስቀምጧል። የአገሬው ጋዜጦችም ይህንኑ ዘግበዋል። ታዲያ ይሄ ደስ አይልም?”

“በጣም እንጂ! በጣም!”

ማረን የማሸነፊያ ጎሏን ያስቆጠረ “ለታ እናቱ ወ/ሮ ማክዳ እንዴት ሆና ይሆን?