“ስምምነቱ ከመጠላለፍ የሚያወጣን ነው” አዴፓና አብን

BBC Amharic : ከሰሞኑ የአማራን ህዝብ ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የጋራ መድረክም በመፍጠር በሚያስሟሟቸው አጀንዳዎች ላይ አብረው ለመስራት የተስማሙት ፓርቲዎች አዴፓ፣ አብን፣ አዴኃን፣ መአህድ፣ መላው አማራ ህዝብ ፓርቲና ነፀብራቅ አማራ ናቸው።

ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተለያዩ ፕሮግራሞች፣ ርዕዮተ ዓለም ከመኖራቸው አንፃር እንዲሁም የአማራን ህዝብ ጥቅም አልወከሉም በሚል ከመወነጃጀላቸው ጋር ተያይዞ በምን አይነት ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት ስምምነት ላይ ደረሱ የሚለው ጥያቄን የሚያስነሳ ነው።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ለተመሳሳይ ህዝብ እንደመስራታቸው መጠን ምንም እንኳን ፕሮግራማቸውም ሆነ ሌሎች የሚለያዩዋቸው ጉዳዮች ቢኖርም አብሮ ለመስራቱም መሰረቱ እንወክለዋለን የሚሉት ህዝብ ልማትና ብልፅግና እንደሆነ የአብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ይናገራሉ።

ይህንንም መሰረት በማድረግ በዋነኝነት የአማራን ህዝብ ጥቅም እንዲሁም ደህነነት ማስጠበቅ አጀንዳዎች ላይ ስምምነት መደረሱን ዶ/ር ደሳለኝ ያስረዳሉ።

ይህም መሰረታዊ ለውጥ ለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው በተለይም ሲወነጃጀሉ ለነበሩ ፓርቲዎች አዙሪቱን የሰበረ ጉዳይ መሆኑንም ይናገራሉ።

“ከመጠላለፍ ወጥተን ወደ መተባበሩ እንድናተኩር፤ የምናደርጋቸውም ውድድሮች በሰለጠነና በሰከነ መንገድ እንዲሆን ስምምነት ላይ ደርሰናል” ብለዋል።

የአዴፓ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተተካ በቀለም ሃሳብ ከዚህ የተለየ አይደለም።

“መድረኩ የሚለየው ከመጠላለፍ ወጥቶ በሰከነ ፖለቲካዊ ትግል ውስጥ ለማለፍ እና በአማራ ህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የሚያደርጉት ሥራ በትብብር ላይ የተመሰረተ ሆኖ ህዝቡ በላቀ ደረጃ የሚጠቀምበት እና በአማራ የጋራ አጀንዳዎች ላይ በጋራ መስራት ነው። በዚህም ሁሉንም በአማራ ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች የተሰባሰቡበት እና ልብ ለልብ የተግባባንበት ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።

ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የጋራ አቅጣጫ ለመቀየስ የተስማሙ ሲሆን ይህም የህዝቡን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በጠራ መልኩ ማስቀመጥ፣ የአጭር፣ የመካከለኛና ረዥም ጊዜ ግብ በመንደፍ አብረው ለመስራትም ስምምነት ላይ እንደደረሱ ይናገራሉ።

በፖለቲካው ዘርፍ ስምምነት ላይ ከደረሱባቸው መካከል የተወሰኑትን ዶ/ር ደሳለኝ እንደጠቀሱት ፓርቲዎቹ በማንኛውም እንቅሴያቸው ላይ ስም ከማጠልሸት፣ ከመወነጃጀልና ከመጠላለፍ መታቀብ፤ ወጣቱን በጋራ አቅጣጫ ማስያዝ፤ ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን አብሮ መስራት ናቸው።

“ለዘመናት የነበረውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጠላለፍና የመገዳደል ባህልንም የሚያስቀር ነው። አሁን ባለው ሁኔታ አማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ይህ ነው የሚባል ልዩነት የለንም” በማለትም አቶ ተተካ ይናገራሉ።

የአማራን ህዝብና ፍላጎት በዘላቂነት ለማረጋገጥ፤ ከጥቃት ለመከላከል እና ከችግር ለመጠበቅ በአማራ ህዝብ ስም የተደራጁ ኃይሎች ማዶ ለማዶ ሆነው ከሚጠላለፉ ተቀራርበው መስራት በሚችሉበት ላይ አብረው ህዝቡን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ መጣር አለባቸው የሚል ጽኑ እምነት አዴፓ አለው ብለዋል ኃላፊው።

በክልሉ ብቻ ሳይሆን ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ ሚሊዮን አማሮችም ድምፃቸው የሚሰማበትን መንገድ መቀየስ፣ ህዝቡ በቋንቋው የመጠቀም፣ ባህሉን የማዳበር እንዲሁም የፖለቲካ ውክልና የሚያገኙበት መንገድ ላይ ለመስራትም ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የህይወት ደህንነቱ፣ የንብረት ዋስትና የማግኘት እሱንም የማስጠበቅም ሥራ ለመስራት ማቀዳቸውንም ፓርቲዎቹ ያስረዳሉ።

ከፖለቲካው በተጨማሪ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊና የወጣቱንም የፖለቲካ ተሳትፎ በመጨመር ረገድም አብረው ለመስራት ከተስማሙባቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ስምምነት በአንዳንድ አካላት ዘንድ እንደ ውህደት ወይም ግንባር የመፍጠር አድርገው የተመለከቱት ቢኖሩም ዶ/ር ደሳለኝም ሆነ አቶ ተተካ ይህ እንዳልሆነ አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

“በሚያስማሙን እና በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ አብረን እንሥራ፤ በማያግባቡን ደግሞ እንተባበር ነው። በጋራ የመስራት ፍላጎት ሰነድ እንጂ አስገዳጅ ህግም ሰነድም አይደለም ” ሲሉ አቶ ተተካ ያስረዳሉ።

ወደፊት በግንባር ደረጃ ወይንም በመዋሃድ ዕቅድ ይኖር ይሆን ወይ በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ዓላማ እና አጀንዳ እየጠበበ ከሄደ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ድርጅቶች መካከል እስከ ውህደት ልናመራበት የምንችልበት አጋጣሚ ዝግ ላይሆን ይችላል” ሲሉ አቶ ተተካ መልሰዋል።

በትብብር መድረኩ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ ምሁራን የሃይማኖት አባቶች እና ታዋቂ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በየጊዜው በመገናኘት ሥራዎች እየተገመገሙ አቅጣጫ በማስያዝ በቀጣይነት እንደሚሰራም ያስረዳሉ።

“ለዓመታት የጨቋኝና ተጨቋኝ ታሪክ በመፍጠር የአማራን ህዝብ የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማው ለረዥም ጊዜ ተሰርቷል፤ ይሄ በጥናትና በዕውቀት ተመስርቶ መቀልበስ አለበት የሚል ፅኑ እምነት አዴፓ አለው፤ ይህንን ከሞላ ጎደል ሌሎች ፓርቲዎችም ይስማሙበታል” ይላሉ አቶ ተተካ።

ለረዥም ጊዜያት አብን፤ አዴፓን ወይም የቀድሞውን ብአዴን ለአማራ ህዝብ ጥቅም እየሰራ አልነበረም፤ የአማራ ህዝብ ውክልና የለውም ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማ ነበር፤ ይህንን ሃሳባቸውን ያስቀየራቸው ጉዳይም አዴፓ ካደረገው የአመራር ለውጥ ጋር እንደሚገናኝም ሊቀመንበሩ ያስረዳሉ።

የቀደመ የአዴፓ ታሪክ “የአማራን ህዝብ አጀንዳ አሳልፎ የሚሰጥ ነበር” የሚሉት ዶ/ር ደሳለኝ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ድርጅቱ ውስጥ “ለአማራ ጥቅም አልታመኑም” የተባሉ አመራሮችን ያጠራበት፤ የተሻለ የአማራ ወገንተኝነት የሚያሳይና ለአማራ ህዝብ የሚቆረቆሩ አመራሮችን ወደፊት ያመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ።

“ሙሉ በሙሉ ባይሆንም አብሮ በመስራት ደረጃ የሚያስችለውን ማስተካከል አምጥቷል” ይላሉ።

በተለይም ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተያይዞ አማራ ህዝብ አልተወከለበትም የሚሉ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ከአብን ይሰማ ነበር።

አዴፓ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ካረቀቁት ድርጅቶች አንዱ ከመሆኑ አንፃር ተቃርኖ የለውም ወይ? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ዶ/ር ደሳለኝ ምላሻቸው አሁን ያለው የአዴፓ አቋም ነው።

አብን ሕገ መንግሥቱ የአማራ ህዝብ ስላልተወከለበት ሊሻሻል ይገባል ብሎ ከማመኑ አንፃር አዴፓም ይህንን መቀበሉ አብሮ ለመስራት እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።

ከአዴፓ ጋር ከነበራቸው ቅራኔ በተጨማሪ ህወሓትን ጋር ያላቸውን የከፋ ቅሬታም በተደጋጋሚ ከመናገራቸው አንፃር፤ አብረው ሊሰሩት ያቀዱት አዴፓ ደግሞ ከህወሓት ጋር በአንድ ግንባር ስር ነው፤ ይህ እንዴት ይታያል? ቢቢሲ ለዶ/ር ደሳለኝ ያቀረበላቸው ጥያቄ ነው።

ምንም እንኳን ህወሓትና አዴፓ ከአስርት ዓመታት በላይ በእህትማማችነት በኢህአዴግ ውስጥ ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም በቅርብ ጊዜያት ግን በግልፅ ተቃርኗቸው እየታየ ነው ይላሉ።

በቅርብ ጊዜያት ፓርቲዎቹ ባወጧቸው መግለጫዎችም ያላቸውን የሻከረ ግንኙነት ያሳየ ሲሆን፤ ይህንንም በማየት በአሁኑ ሰዓት ያላቸው ግንኙነት የይምሰል አይነት ነው በማለት ዶ/ር ደሳለኝ ያስረዳሉ።

ይህንንም በመታዘብ በቀጣይ ሊፈጠር በሚችለው አዲሱ የውህድ ፓርቲ ህወሓት ሊገባ የማይችልበት እድል ሰፊ መሆኑን ያስረዳሉ።

የዚህ አንድምታውም “አዴፓ ወደ አማራ ህዝብ ጥያቄ እየቀረበ መሔዱን የሚያሳይ ነው፤ እሱንም የሚያረጋግጥልን ነው። ከአዴፓም ጋር እያደረግናቸው ያሉ ግንኙነቶች ወደፊት የሚያስኬደን መሆኑን የሚያሳይ ነው። ከህወሓት ጋር በአንድ ግንባር ውስጥ ስላለ አማራዊ የሆነውን አዴፓን ገፍተን አብረን አንሰራም የምንልበት ምክንያት ሊኖር አይችልም” ይላሉ።

ምንም እንኳን ህወሓት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ቢኖራቸውም ህወሓትም ቢሆን ሥርዓት ወዳለው የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲገባ እንፈልጋለን ይላሉ።