በጀርመን ራሳቸውን “ቄሮ” በሚል ስም አደራጅተው ሁከት ፈጥረዋል የተባሉ ግለሰቦች በፍራንክፈርት ፍርድ ቤት ተከሰሱ

“ተከሳሾች እራሳቸውን “ቄሮ” ብለው የተደራጁ ግለሰቦች ሲሆኑ ከሳሹ ደግሞ በጀርመን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚቴ ነው:: ስብሰባን ለማወክ እና ጥቃት ለመፈፀም በማቀድ የስብሰባ አዳራሽን ጥሶ በመግባትና በማስፈራራት አውከዋል ክብርን የሚነካ ስድብ ተሳድበዋል የመብት ጥሰትም አድርሰዋል ተብሎአል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ 20 እና 21, 2011 ዓ.ም በፍራንክፈርት እና በበርሊን ከተሞች በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር።  በወቅቱ በተሰብሳቢዎች በአዘጋጆቹና በዕለቱ የክብር እንግዳ ላይ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ጭምር በቪድዮ በተሰራጩ መልዕክቶች ስብሰባውን ለማወክ እና ጥቃት ለመፈፀም ያቀዱ ግለሰቦች ተደራጅተው መጥተዋል።  በር ላይም ሳይፈተሹ የጥበቃ ሰራተኞችን ጥሰው የአዳራሹን በር በቡድን በሃይል በርግደው በመግባት እና በማስፈራራት አውከዋል ክብርን የሚነካ ስድብ ተሳድበዋል የመብት ጥሰትም በአዘጋጆቹ እና በተሰብሳቢዎች ላይ ፈፅመዋል በማለት የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ለፖሊስ በማመልከታቸው የጀርመን ፖሊስ አባላት የአዳራሹን እንቅስቃሴ በሺድዮ በመቅረፅ እና አዘጋጆቹ ሁከት ፈጣሪ ናቸው ያሏቸውን ስም እና አድራሻ በመዝገብ የአንዳንዶቹንም አሻራ በመውሰድ ማሰናበታቸውን በወቅቱ ገልፀን ነበር። ድርጊቱ በተከሰተበት ወቅትም ረብሻ እንደማይፈጥሩ የገለፁት ገብተው በስብሰባው ቢሳተፉም በርካታ አባላቶቻችን አስቀድመው አዳራሹን ስለሞሉት ፈርተው የወሰዱት እርምጃ ነው በኦሮሞ እና ቄሮ ላይ የተዛባ አመለካከት አላቸው አባሎቻችን ከስብሰባው የተባረሩት በብሄር እና ሃይማኖት ተለይተው ነው በማለት ቅሬታ አሰምተው ነበር ፤ በተለያዩ የኦሮሞ ብሄረሰብ አደረጃጀቶች ተሰባስበው ስብሰባውን ለመታደም የመጡት ወጣቶች።

በጉዳዩ ላይ ልዩ ልዩ ማስረጃዎችን ስሰበስብ ቆይቻለው ያለው በጀርመን የኢትዮጵያ የሰብአዊ  መብት ጥበቃ ኮሚቴ በበኩሉ ራሳቸውን “ቄሮ” በሚል ስም አደራጅተው በጀርመን የተለያዩ ከተሞች ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባ ጉዳይ ለመምከር የጠሩትን ስብሰባ በኃይል ለማወክ እንዲሁም አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ለማድረስ ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ድርጊት ፈፅመዋል ባላቸው ግለሰቦች ላይ በፍራንክፈርት ከተማ ፍርድ ቤት ክስ መመስረቱን አስታወቋል። የኮሚቴው ዋና ሊቀመንበር አቶ ስዩም ኃብተማርያም በተለይ ለዶይቼ ቨለ እንዳስረዱት እነዚሁ ግለሰቦች በስብሰባው አዘጋጆች እና በዕለቱ የክብር እንግዳ ላይ የኃይል ጥቃት እንደሚፈፅሙ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሺድዮ ጭምር መልዕክቶችን ከማስተላለፋቸውም ሌላ ዘር እና ሃይማኖት ተኮር ስድቦችን በመሳደብ ተሰብሳቢዎችን በመተናኮል እና በማሸማቀቅ እንዲሁም ፎቶግራፍ እና ቪድዮ እያነሱ በማስፈራራት ከፍተኛ የመብት ጥሰት እና ሽብር ፈፅመዋል ሲሉ ከሰዋል።

በጀርመን የወንጀል ህግ መስክ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የአገር ውስጥ ወንጀሎች እና የሽብር ጥቃቶች ሳይንሳዊ ተንታኝ ባለሙያ የሆኑት የሰብአዊ መብት ኮሚቴው የህግ ጠበቃ ስቴፈን ኩን በበኩላቸው ተጠርጣሪዎቹ በጀርመን ህገ መንግስት መሰረታዊ የህግ ድንጋጌ ልዩ ትከረት የተሰጣቸውን መብቶች ጥሰዋል በልዩ ልዩ ወንጀሎችም ክስ መስርተንባቸዋል ሲሉ ነው ያስረዱት።

“ተከሳሾች እራሳቸውን “ቄሮ” ብለው ያደራጁ ግለሰቦች ሲሆኑ ከሳሹ ደግሞ በጀርመን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት  ኮሚቴ ነው:: ግለሰቦቹ ላይ በዛቻ እና ማስፈራራት አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥቃት በመፈፀም የሰውን ቤት ጥሶ በመግባት በተለይም በጀርመን ሕገ መንግሥት መሰረታዊ የህግ ድንጋጌ ልዩ ትኩረት ተሰቶት በመጀመሪያ ምዕራፍ የሰፈረውን የሰዎችን በነጻነት ሃሳብን የመግለፅ እና የመሰብሰብ መብት በሃይል በማፈን በእነዚህ እና በሌሎችም ወደፊት ሊመጡ በሚችሉ የወንጀል ክሶች ፋይል ከፍተናል።” ሲሉ ኩን ገልፀዋል።

በጀርመን በቄሮ ስም ተደራጅተው ኢትዮጵያውያን ያካሄዱትን ስብሰባ የጥበቃ ሰራተኞችን ጥሰው የአዳራሹን በር በቡድን በሃይል በርግደው በመግባት እና በማስፈራራት አውከዋል ክብርን የሚነካ ስድብ ተሳድበዋል የመብት ጥሰትም በአዘጋጆቹ እና በተሰብሳቢዎች ላይ ፈፅመዋል ከዚህ በተረፈ ያለ ብሄር እና ሃይማኖት አድልዖ አስገብተን እንዲወያዩ አድርገናል ቢሉም አዘጋጆቹ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉት ወገኖች ግን ይህን በፍፁም አይቀበሉትም። ስብሰባው “ለኢትዮጵያውያን በሙሉ” ተብሎ የተዘጋጀ ቢሆንም ኦሮሞ እና ሙስሊሞች ተለይተው ወደ ውስጥ እንዳይገቡ አድሎ ተፈፅሞብናል :: ጥቂቶች የገባነውም የምናውቃቸው ሰዎች “እነሱ አይረብሹም” ብለው ስለመሰከሩልን ነው:: ከዚህ በተረፈ የቄሮ ወጣቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በህብረተሰቡ ላይ ምንም ዓይነት የመብት ጥሰት አይፈፅሙም ።በወቅቱ ለተፈፀመውም ችግርም በቂ የምስክር መረጃ ስላለን በሃሰት ክስ ከተመሰረተብን በህግ እንከራከራለን ሲሉ ተወካያቸው አቶ አብዲ አባጀበል መልስ ሰተዋል።
ተከሳሾቹ የክስ መጥሪያ እንደደረሳቸው የፍርድ ሂደቱ በፍራንክፈርት ፍርድቤት እንደሚጀመር በጀርመን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ኮሚቴ ዋና ሊቀመንበር አቶ ስዩም ኃብተማርያም አስረድተዋል።