ከሶማሌላንድና የመን የመጣው የአንበጣ መንጋ በተለያዩ አገሪቷ ክፍሎች ውድምት እያስከተለ እንደሆነ ተነገረ


የመረጃ ቲቪን 24/7 የሳተላይት ስርጭት በመደገፍ የኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ እና ትክክለኛ መረጃ በማግኘት እራሱን ከተጋረጠበት አደጋ መከላከል እንዲችል እናግዝ። በአሁኑ ወቅት ከመረጃ ቲቪ በስተቀር ሌሎች ሁሉም በኢትዮጵያ ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመንግስት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ናቸው። ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ የከፈትነው የመረጃ ቲቪ የሳተላይት ስርጭት የአንድ ዓመት ወጪን ለመሸፈን ነው። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ድጋፍዎትን ይለግሱ » https://gofund.me/54405070

BBC Amharic : ከየመንና ከሶማሌላንድ እንደመጣ የተነገረው የአንበጣ መንጋ በተለያዩ አገሪቷ ክፍሎች ውድምት እያስከተለ እንደሆነ እየተነገረ ነው። በአማራ ክልል፣ በአፋር፣ ደቡባዊ ትግራይ፣ ምስራቅ ኦሮሚያና፣ ምስራቅ ሀረርጌ አንዳንድ አካባቢዎች መከሰቱ ይታወቃል። መንጋው ቀደም ሲል ያልገባባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም እየዘመተ ነው።

ከሶማሌላንድና የመን የመጣው አንበጣ በአምስት ክልሎች ተከስቷል

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል በቃሉ ወረዳ ከሁለት ቀናት በፊት የአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ ተሞክሮ በአካባቢው የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን የወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዱ እንድሪስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ አብዱ አክለውም በሰው ኃይል ሰብሉን ለመሰብሰብ ጥረት ቢደረግም ያለጊዜው በመሰብሰቡ ከውድመት እንደማይድን ያክላሉ።

በዚያው ወረዳ ያነጋገርናቸው አርሶ አደር አህመድ ሀሰን “የአንበጣ መንጋው በተለያዩ ፎቶዎች ላይ እንደሚታየው አይደለም ረጅምና ሰፊ ነው” ይላሉ።

ከአንዱ ሥፍራ ሲያባርሩት ወደ አንዱ የሚሰደደው የአንበጣ መንጋ ሦስተኛው ዙር ትናንት እነርሱ ጋር ውሎ አራተኛው ከሌላ ቦታ እንደሚመጣ ተነግሯቸው እየጠበቁ እንደሆነ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

አቶ አህመድ እንደሚሉት በአካባቢው እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች ሰብላቸው ወድሞባቸዋል።

የአንበጣ መንጋው በዚያው ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳም በተለያዩ ቀበሌዎች ተከስቶ ዛሬ ወደ ሰሜን ወሎ ዞን መግባቱን ቢሰሙም አሁንም ስጋቱ እንዳላበቃ እና አሁንም እየመጣ ያለ መንጋ መኖሩን የወረዳው ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሳዳም ሽመልስ ይገልፃሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ በባህላዊ መልኩ በጩሀትና በዛፍ ዝንጣፊ በማባረር ለመከላከል ቢሞከርም ተከታትሎ የሚመጣው መንጋ አሁንም ፈተና እንደሆነ ነው።

በአርጎባ ብሔረሰብ አስተዳደርም ላይ በ6 ቀበሌዎች ተከስቷል። የመከላከል ሥራ ሲሠራ ቢቆዩም አሁንም በሁለት ቀበሌዎች ላይ በስፋት ይገኛል ያሉት የወረዳው ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ጌታቸው ናቸው።

“አርጎባ ተራራማ አካባቢ ነው፤ ዳገት ቆፍረው ነው ሰብል የሚያመርቱት ከዛም ብሶ አንበጣ በላው። ስጋት ላይ ነው ያለነው” ብለዋል።

ከሳምንት በፊት ከወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ያገኙት መረጃን ጠቅሰው እስካሁን በወረዳው 275 ሄክታር ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱን የገለፁት አቶ አህመድ በሚዲያዎች ላይ በሰብል ላይ ጉዳት አለመድረሱን የሚዘገበው ትክክል አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

በዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ዙቤር ሸህ አዩብ ሰብላቸው ከወደመባቸው አንዱ ናቸው።

“አወዳደሙ ከመውደምም በላይ ነው፤ ሰብሉን ለመሰብሰብ በገባንበት ሰዓት ድንገት ከደረሰ ፊትም ጆሮም ይመታል፤ እዚያው እህሉ ውስጥ ነው ቁጭ የምንለው፤ የምናደርገው የለም” ሲሉ እርሳቸው 2 ሄክታር ላይ ያለ ሰብል እንደወደመባቸው ገልፀዋል።

እስካሁን በሰብል ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልቶ ጥያቄ የቀረበላቸው በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶ፤ በተባይ መከላከል ሥርዓት ውስጥ ጉዳት የሚታወቀው መከላከሉ ሲጠናቀቅ ነው ብለዋል።

ከሥር ከሥር ጉዳቱን ለመግለፅ ጊዜ አንደሌላቸው የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ “ጉዳት ማድረሱ ባይካድም የጉዳቱን መጠን ግን ምን ያህል እንደሆነ አናውቀውም፤ ይሄ ነው ብለን አንገልፅም፤ የራሱ ሂደት ስላለው” ብለዋል።

በአብዛኛው በመከላከል ሂደቱ ላይ ትኩረት እንዳደረጉ ገልፀዋል። ይሁን እንጅ በፀጥታ ችግር ምክንያት፣ በቦታዎች የመልክዓ ምድር አቀማመጥ እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች ጫት ላይ ጉዳት ያደርስብናል በሚል ምክንያት የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ተግዳሮት እንደገጠማቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ኬሚካሉ በተጠኑ ቦታዎች ላይ በጥንቃቄ እንደሚረጭም በመግለፅ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አንበጣን በጭስ፣ በጥይት፣ በጩኸት፣ በጅራፍ. . ?

ማህበረሰቡ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ጅራፍ፣ ጥይት፣ ድምፅ የሚፈጥሩ ነገሮችን በማቃጨል፣ በጅራፍ፣ በጩኸት፣ ጨርቅ በማውለብለብ ለመከላከል ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ይህ ልማድ በሳይንስስ ይደገፍ ይሆን?

አንበጣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ አይደለም የሚሉት አቶ ዘብዲዎስ አንበጣን በባህላዊ መንገድ መከላከል በሳይንስም የሚደገፍ ነው ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣ መከላከል አባል የሆነችው በአውሮፓዊያኑ 1940 አካባቢ ነው። ከኤርትራና ከሌሎች አረብ አገራት አንበጣ ይሻገር ስለነበር አንበጣን በባህላዊ መንገድ የመከላከል ልማድ ነበር።

አንበጣው ሰብል ላይ እንዳያርፍ የማባረር ሥራ ይሰራ ነበር። ነገር ግን ከቦታ ቦታ የመረጃ ልውውጥ መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። ወደ ሄደበት አካባቢ ሪፖርት ማድረግ መዘንጋትም የለበትም ይላሉ።

ይሁን እንጂ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች አንበጣን በጥይት ለማባረር የሚደረገው ሙከራ ትክክል አይደለም ሲሉ ነቅፈዋል።

ይህ በጥይት የማባረር ተግባር በአውሮፓዊያኑ 2016 ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለ አስታውሰዋል። ከምስራቅ ኢትዮጵያ መከላከል አምልጦ ወደ አዲስ አበባ የገባው በጥይት ምክንያት ነው፤ ከዚያም ወደ ሰሜን አምርቶ በርካታ ቀበሌዎችን ማድረሱ የቅርብ ጊዜ ትውስታቸው ነው።

በመሆኑም “ብዙ ጭስ ማጨስ ሳያስፈልግ፤ በጭስ ፣ በቆርቆሮ ድምፅ፣ በልጆች ጩኸት ድምፅ፣ በተለይ በጅራፍ ከሰብል ላይ መንጋውን ማባረር ይገባል” ሲሉ ይመክራሉ።

ይሁን እንጅ ከሰብል አቅራቢያ ያሉ የግጦሽ መሬት ላይ፣ ደን አካባቢ እና ሌሎች አካባቢዎች ሄዶ ካረፈ ማደሪያውን ብቻ መከታተል እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

ከዚያም በርካታ ሕዝብ የማይኖርበትና ለመጠጥና ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎች ባሉበት ቦታ ካልሆነ ፀረ ተባይ ኬሚካል መርጨት እንደሚቻል በመግለፅ የመከላከሉን ሥራ ማቅለል እንደሚቻል አቶ ዘብዲዎስ አስገንዝበዋል።

የአንበጣ መንጋው አሁንም በኢትዮጵያ እንደሚቀጥልና ወደ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኦማን፣ የመን፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ አገሮችን ጭምር ሊከሰት እንደሚችል ትንበያ መኖሩን አቶ ዘብዲዎስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።