መርማሪዎቹም ሆኑ አቃቤ ህጉ ብሎም ዳኞች ያኔ ስንወቅሰው ከነበረው ስርአት እጅግ የከፉና የፍትህ ስርአቱ ከድጡ ወደ ማጡ መሄዱን የሚያሳዩ ሆነዋል – ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በእስር ቤቶች ያለው ስቃይና እንግልት በህወሃት አገዛዝ የነበረውን ስቃይ ያስንቃል።- ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ

ኢትዮ 360 – በእስር ቤቶች ያለው ስቃይና እንግልት በሕወሃት አገዛዝ የነበረውን ሰቆቃ የሚያስንቅ መሆኑን የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራስ ዋና ጸሃፊ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ገለጸ።

መርማሪዎቹም ሆኑ አቃቤ ህጉ ብሎም ዳኞች ያኔ ስንወቅሰው ከነበረው ስርአት እጅግ የከፉና የፍትህ ስርአቱ ከድጡ ወደ ማጡ መሄዱን የሚያሳዩ ሆነዋል ይላል ከኢትዮ 360 ጋር በነበረው ቆይታ።

እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ እንኳን ታሰርን ይላል ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ምክንያቱም አሁን በእስር ቤት ውስጥ ያለውን አሰቃቂ ሁኔታ ከሌላ ሰው ብንሰማው ውሸት ነው ብለን እንከራከር ነበር ብሏል።
የእስር ቤቶቹ ጭለማ፡ከስር ውሃ የሚያስገቡት የእስር ቤቱ ክፍሎች፡ያንን ተከትሎ የሚመጣው ሽታ በቃላት ለመግለጽ በፍጹም አይቻልም ይላል።

በእነዛ እስር ቤቶች እኔ የጆሮዬ ህመም ሰላም ቢነሳኝም የሌሎች ጓደኞቼ ህመምና ራሳቸውን ስተው እስኪወድቁ ያለውን ህመማቸውን ሳስብ የምናገረው ቃል ያጥረኛል ይላል።
በአራት ወራት የእስር ቤት ቆይታዬ ትልቁና አሳዛኙ ጭራሽም ባይመጣ ብዬ የምመኘው ቀን ፍርድ ቤት የምንሄድበት ቀንን ነው።

መርማሪው በቂ ማስረጃ የለው፡ዳኛው ማስረጃህ በቂ አይደለም ብሎ ከማስቆም ይልቅ ከመርማሪው ጎን ሆኖ እኛንው ይከራከራል፡ይሄ ደግሞ ለእኔም ሆነ ለጓደኞቼ ህመም ነው ሲል ይገልጻል።

መጀመሪያ ላይ የለውጥ ጭላንጭል አለ ብዬ አምን ነበር የሚለው ኤልያስ በእስር ቤት ቆይታዬም ሆነ የባላደራውን እንቅስቃሴ ለመግታት የተኬደበትን ርቀት ሳይ ግን ሁሉ ነገር ውሸትና ከህወሃት ስርአት የከፋ አገዛዝ ውስጥ መውደቃችንን ለመረዳት ብዙም ጊዜ አልፈጀብንም ይላል።

በእስር ቤት ይታይ የነበረው በአንድ ብሔር የመሞላት ሒደት አሁን ደግሞ በኦዴፓ በመተካት ላይ ነው።
አሁንም ይላል ኤልያስ ገብሩ ያለምንም ፍትህ በእስር ቤት ውስጥ የእነዚህ አካላት ግፍ እየተቀበሉና በነዛ በቃላት ለመግለጽ በሚያስቸግሩ ክፍሎች ውስጥ ታሽገው የሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን አሉ።-ድምጻቸውም እንዲሰማ ይፈልጋሉ ብሏል።
በሽብርና በመፈንቅለ መንግስት ተከሰን የታሰርንው እኛ በመታወቂያ ዋስ ተፈታችሁ ተብለናል።-

ይሄ ደግሞ ምን አይነት አሳፋሪና አሳዛኝ መንግስት እንዳለን የሚያሳይ ነው ብሏል ዋና ጸሃፊው ኤልያስ ገብሩ።
እርግጠኛ ሆኜ ምናገረው አሁንም እንድንፈታ ሲደረግ ያሰረን አካል አምኖበት ሳይሆን ጫና ስለበዛበትና ከባድ የፖለቲካ ኪሳራ ስለደረሰበት ብቻ ነው ሲል ይገልጻል።

በቀጣም የሚገጥሙን ከባድ ፈተናዎች እንዳሉ እናስባለን፡ነገር ግን እነዚህ ፈተናዎች ትላንት የጀመርናቸውን ትግሎች ወደ ኋላ የሚያስቀሩ አይደሉም ብሏል።

አንድ ሃገር ናት ያለችን የሚለው ኤልያስ ገብሩ ይቺን ሃገር ደግሞ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነን ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ መስራት አለብን ብሏል።

አሁን ላይ ያለው የፖለቲካ ቅኝትን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተረድቶታል ስለዚህ ምላሹ አንድና አንድ ብቻ ይሆናል ማለት ነው።-አንዷን ሃገራችንን ኢትዮጵያን መታደግ፡ በየቀኑ እየተገደለና በቁም እየተሰቃየ ላለው ኢትዮጵያዊ ወገናችን አለንልህ ማለት ብሏል ኤልያስ ከኢትዮ 360 ጋር የነበረውን ቆይታ ሲያጠቃልል።